Get Mystery Box with random crypto!

ዘመነ ክረምት በኢትዮጵያ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ዘመነ ክረምት በኢትዮጵያ

በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሥርዓተ አስተምህሮ በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት እና በመጽሐፈ ግጻዌ መሠረት፣እንዲሁም በሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ስሌት መሠረት ወቅቶች በአራት ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም ወቅቶች ዘመነ መጸው (መከር)፣ ዘመነ ሐጋይ (በጋ)፣ ዘመነ ጸደይ (በልግ) እና ዘመነ ክረምት ይባላሉ፡፡

ከአራቱ ወቅቶች መካከልም ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ (አሁን የምንገኝበት ወቅት) ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል፤ ቃሉን ለማብራራት ያኽል፣ "ክረምት" የሚለው ቃል ‹ከረመ – ከረመ› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፣ እንደዚሁም ዕፀዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት እንደሆነ የአማርኛ መዝገበ ቃላትና ልዩ ልዩ ድርሳናት ያስረዳሉ።

በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት አራቱ ወቅቶች የጌታችንና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ወንጌል በጻፉት በአራቱ ወንጌላውያን እንደሚመሰሉ ማለትም: ዘመነ ክረምት - በወንጌላዊው ማርቆስ፣ ዘመነ ፀደይ - በወንጌላዊው ማቴዎስ፣ ዘመነ ሀጋይ - በወንጌላዊው ዮሐንስ እና ዘመነ መፀው - በወንጌላዊው ሉቃስ እንደሆነ ሊቃውንት ያስተምራሉ።

ከአራቱ ወቅቶች መካከል ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ (አሁን የምንገኝበት ወቅት) በወንጌላዊው ማርቆስ የተመሰለው ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል፡፡

በዓተ ክረምት (የክረምት መግብያ)

ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው የመጀመሪያው የክረምት ክፍለ ጊዜ "በዓተ ክረምት" ወይም ‹ዘርዕ፣ ደመና› ይባላል፡፡ ‹በዓተ ክረምት› ማለት <የክረምት መግቢያ፣ መጀመሪያ› ማለት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተክርስቲያናችን ስለክረምት መግባት፣ ስለዘርዕ፣ ስለደመና እና ስለዝናም የሚያዘክሩ መዝሙራትና ምንባባት ይዘመራሉ፣ ይነበባሉ፡፡ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፣ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ ነውና፡፡

በዘመነ ክረምት መጀመርያ (መግቢያ) ሳምንት በቤተክርስቲያናችን የሚቀርበው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር የሚከተለው ነው፤ ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይጸግቡ ርኁባን ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ደምፀ እገሪሁ ለዝናም›› የመዝሙሩ ቀጥተኛ ትርጕም፡-‹‹የዝናም ኮቴው ተሰማ፣ ዝናም በሚዘንም ጊዜ የተራቡ ይጠግባሉ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ ዝናም በሚዘንም ጊዜ ድሆች ይደሰታሉ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፣ አምላካችን ለሰው ልጅ ዕረፍት ሰንበትን ፈጠረ፤ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡>>

ይህ መዝሙር ከሰኔ ፳፮ ጀምሮ ያለው ወቅት ክረምቱ የሚገባበት እና ዝናም በብዛት የሚጥልበት ጊዜ መኾኑን የሚያበሥር ሲኾን፣ በተጨማሪም ዝናም በሚዘንብበት ጊዜ የሚበቅለውን እኽልና የምንጮችን መብዛት ተስፋ በማድረግ የተራቡ እንደሚጠግቡ፤ የተጠሙም እንደሚረኩ የሚያትት ምሥጢር ይዟል፡፡ እንደዚሁም ጊዜ ለበጋ፣ጊዜ ለክረምት የሚሰጥ አምላክ ለሰው ልጅ ማረፊያ ትኾን ዘንድ ዕለተ ሰንበትን መፍጠሩንም ያስረዳል፡፡

አያይዞም ቅዱስ ዳዊት "ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቍል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡››መዝ ፻፵፮፥፰ ትርጕም፡- ‹‹ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፣ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ የሚያበቅል እርሱ ነው፡፡>> እግዚአብሔር ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፤ ዝናምንም (ክረምትን) ለምድር (ለሰው ልጅ) የሚያዘጋጅ፤ እንደዚሁም በተራሮች ላይ ሣርን (ዕፀዋትን) የሚያበቅል አምላክ መኾኑን ያስገነዝባል። ዘመነ ክረምት በየትኛውም ክፍለ አኅጉር ወቅቶችን እየቀያየረ ምድርን ሲያድስ የሰው ልጆችንም ሕልውና አብሮ በማደስ ሰውና ክረምት ያለውን ቁርኝት ዘላለማዊ አድርጎታል።

ስለሆነም ክረምት እና በጋውን በማፈራረቅ ምድርን በልምላሜ እና አበባ የሚያሸበርቀውን ፤ በዘመናት መካከል በፀጋና በረከት የሚያኖረውን የዘመን ባለቤት አምላካችን እግዚአብሔርን ከልባችን እያመሰገንን ለዘላለማዊ ክብሩ በመገዛት እንኑር። በክረምት የሚሠሩትን ሥራዎች በሙሉ በመከወን ለፍሬያማው ወቅት እግዚአብሔር ያደርሰን ዘንድ አብዝተን እንጸልይ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!

በመ/ር ሽፈራው እንደሻው

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox