Get Mystery Box with random crypto!

ሠኔ ፳ እና ፳፩ በእመቤታችን ስም የተሠራች የመጀመሪያዋ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ቅዳሴ ቤት የእመቤ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ሠኔ ፳ እና ፳፩ በእመቤታችን ስም የተሠራች የመጀመሪያዋ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ቅዳሴ ቤት የእመቤታችን ፪ኤቱ ክብረ በዓላት ታሪክ

በሠኔ ፳ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በፊልጵስዩስ የተሠራችው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ትታሰባለች፤ ይኸውም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚያስረዳን ጳውሎስና በርናባስ ወደ ፊልጵስዩስ ከተማ ገብተው ባስተማሩ ጊዜ ሕዝቡ “መካነ ጸሎት ለዩልን” ብለዋቸዋል፤ ይኽነንም ለጴጥሮስ በነገሩት ጊዜ ጌታችን የሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን አሠራር እንዲገልጽላቸው ሱባዔ ገቡ፤ ሱባዔውም ሲፈጸም ጌታ ሐዋርያትን የሞቱትን አስነሥቶ ያሉትን ጠርቶ በሕይወተ ሥጋ በፊልጵስዩስ ሰበሰባቸው፨

“በናቴ ስም አብያተ ክርስቲያናት ሊታነጹ ፈቃዴ ነውና ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ላሳያችኊ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናትን ላስተምራችኊ ሰብስቤያችኋለኊ” ብሏቸው፤ ወደ ምሥራቅ አገር ይዟቸው ወጣ፤ በዚያ በምሥራቅ ሀገር ሦስት ደንጊያዎች ነበሩ ተራርቀው የነበሩትን አቀራረባቸው፤ ጥቃቅን የነበሩትን ታላላቅ አደረጋቸው፤ ቁመቱን ወርዱን ለክቶ ሰጣቸው፤ ቁመቱ 24 ወርዱ 12 ክንድ ነው፡፡

፳፬ቱ የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ አምሳል ነው፤ ፲፪ቱ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፤ ከዚኽ በኋላ ሥራ ጀመሩ፤ ሲሠሩትም ሰም እሳት ሲያሳዩት እንዲለመልም በእጃቸው ላይ እየተሳበ ሠርተው ፈጽመውታል፤ ይኽ የኾነ እመቤታችን ባረገች በአራተኛው ዓመት በሠኔ ፳ ቀን ነው፨

በሠኔ ፳፩ኛው ቀን ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ መጣ፤ እመቤታችንን ታቦት፤ ሐዋያትን ልኡካን አድርጎ፤ ጌታ ዐቢይ ካህን ኾኖ ቀድሶ አቊርቧቸዋል፤ ከዚያም “እምይእዜሰ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ” (ከእንግዲኽ ወዲኽ እናንተ እንዲኽ ሥሩ) ብሎ አዝዟቸው ዐርጓል፤ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የተጀመረ በቅድስት ድንግል ስም ነው፡፡

ሦስቱ ደንጊያዎች የሥላሴ አምሳል ናቸው፤ ከታች አቀማመጣቸው ፫ ከላይ ሕንፃቸው ፩ ነው ይኽም የአንድነታቸው የሦስትነተኛው አምሳል ነው፤

አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታም በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ፡-

“በሠላስ አእባን ገጸ ሥላሴሁ ለአምሮ
ሐኒጸ ቤትኪ ድንግል ድኅረ ፈጸመ ሣርሮ
አመ ወረደ ለበዓል ምስሌኪ በአማኅብሮ
እንዘ ይብላ ቃለ ለዘምሮ
ልዑል ቀደሰ ማኅደሮ
ደናግል ለጽጌኪ ዘበጣ ከበሮ”

(ድንግል በአካል ሦስት መኾኑን ለመግለጽ በሦስት ድንጋዮች ቤትሽን መሥራት ከፈጸመ በኋላ፤ ከአንቺ ጋር ለበዓል በተገለጸ ጊዜ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ እያሉ ልጅሽን ለማመስገን ደናግል በከበሮ ምስጋናን አቀረቡ) በማለት ገልጸዋል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሠራሯ በሰማያት አምሳል እንደኾነ ሊቃውንት ይተነትናሉ፤ ይኸውም የመጀመሪያዋ ሰማይ “ጽርሐ አርያም” ስትባል ከእሳት ብርሃኗን ነሥቶ ከብርሃን ብርሃንን ጠምቆ አጥርቶ፤ ኹለንተናዋን በብርሃን ቀለም ሸልሟታል “አልቦ ሰማይ ዘይጼልል ላዕሌሃ እስመ መልዕልታዊት ወጽንፋዊት ይእቲ ወኲለንታሃ ብርሃን ፍጹም ዘኢይትነገር በልሳነ ኲሉ ፍጡር ወኲሎሙ ብርሃናት አምሳለ ቀለምጺጸ እሳት በኀቤሃ” ይላል ፤ ብርሃኗን ማንም ከቶ ሊገልጸው አይችልም፤ ከርሷ ብርሃን አንጻር ሲታዩ ሌሎቹ ብርሃናት የእሳት ፍንጣሪ ያኽላሉ፤ ከሰማይ ኹሉ በላይ ስትኾን ከርሷ በላይ ምንም ሰማይ የለም፤ ከዚኽ የተነሣ “ሰማየ ሰማያት” ትባላለች (ዘዳ ፲፥፲፬፤ ፩ነገ ፰፥፳፯)፡፡
ምሳሌነቷን ሊቃውንት በመጽሐፈ ቅዳሴ መቅድም ላይ የሰማይ ሥርዓት በምድር ላይ ስለመሠራቱ ሲተነትኑ በጽርሐ አርያም ውስጥ መንበረ ብርሃን፣ ታቦተ ብርሃን፣ መንጦላዕተ ብርሃን፣ አራቱ ጸወርተ መንበር፣ ኻያ አራቱ ዐጠንተ መንበር ይኖራሉ፤ ጽርሐ አርያም የመቅደስ፤ መንበረ ብርሃን የመንበር፤ ታቦተ ብርሃን የታቦት፤ መንጦላዕተ ብርሃን የመንጦላዕት፤ አራቱ ጸወርተ መንበር የአራቱ ሊቃነ ጳጳሳት፤ ፳፬ቱ ዐጠንተ መንበር የጳጳሳት የኤጲስ ቆጶሳት አምሳል ናቸው፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ሰዓታቱ ላይም “ወኊልቈሙ ለእሙንቱ መላእክት ወሊቃነ መላእክት... ወቡርክት ዛቲ ቤተ ክርስቲያን እንተ አሕዛብ ትመስል ኀይለ ሰማያት” (የእነዚኽ መላእክት የመላእክት አለቆች ቊጥርም መናብርትና ሥልጣናት፣ አጋዕዝትና ኀይላት፣ ሊቃናት፣ ኪሩቤልና ሱራፌል ነው፤ እየጮኹም እንዲኽ ይላሉ የእስራኤል አምላክ ይመስገን የሕዝቡ የአሕዛቡ የምትኾን የተባረከች ቤተ ክርስቲያን የሰማያት ኀይልን ትመስላለች) ይላል፡፡
ሊቁ ሰራዊተ መላእክትን በሚያመሰግንበት በዚኽ ክፍል ላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሠራሯና እና አከፋፈሏ በመላእክት ከተማ እና በአሰፋፈራቸው ልክ የተመሰለች መኾኗን አስረግጦ አስተምሯል፡- ይኸውም ሦስቱ የቤተ ክርስቲያን ክፍሎች (መቅደስ፣ ቅድስት፣ ቅኔ ማሕሌት) የሦስቱ ዓለመ መላእክት ምሳሌ ሲኾን ይኸውም መቅደስ የኢዮር፤ ቅድስት የራማ፤ ቅኔ ማሕሌት የኤረር ምሳሌ ናቸው፡፡
ኢዮር በተባለችው ሰማይ ኪሩቤል፣ ሱራፌል፣ ኀይላት ይኖራሉ፡፡ ራማ በተባለችው ሰማይ አርባብ፣ መናብርት፣ ሥልጣናት ይኖራሉ፡፡ ኤረር በተባለችው ሰማይ ሊቃናት፣ መኳንንት፣ መላእክት ይኖራሉ፡፡ እነዚኽ 9ኙ ነገድ የ፱ቱ መዓርጋተ ቤተ ክርስቲያን አምሳል ናቸው፡፡
ይኸውም በኢዮር ከሚኖሩት መላእክት ውስጥ ኪሩቤል የሊቃነ ጳጳሳት፤ ሱራፌል የጳጳሳት፤ ኀይላት የኤጲስ ቆጶሳት አምሳል፡፡
በራማ ሰማይ ከሚኖሩት ነገደ መላእክት ውስጥ አርባብ የቆሞሳት፤ መናብርት የቀሳውስት፤ ሥልጣናት የዲያቆናት አምሳል፡፡
በኤረር ሰማይ ከሚኖሩት ነገደ መላእክት ውስጥ ሊቃናት የንፍቀ ዲያቆናት፤ መኳንንት የአናጒንስጢሳውያን፤ መላእክት የመዘምራን አምሳል ናቸው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በድጓው ላይ ስለ ክብረ ቤተ ክርስቲያን፦
“እንተ ተሐንጸት በስሙ፤ ወተቀደሰት በደሙ ወተዐትበት በዕፀ መስቀሉ ጊሡ ኀቤሃ እስመ ኀይለ እግዚአብሔር ላዕሌሃ” (በስሙ ታነጸች፤ በደሙም ከበረች፤ በዕፀ መስቀሉም ተባረከች፤ ወደ ርሷ (ቤተ ክርስቲያን) ኺዱ የእግዚአብሔር ኀይል በርሷ ላይ ነውና) ይላል፡፡

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ተአምኆ ቅዱሳን በሚባለው ታላቅ መጽሐፉ ላይ፡-
“ሰላም ለቤተ ክርስቲያን ቅድስት ማኅደረ ስብሐት ምዕዋደ መላእክት እመ ኲሉ ሕዝብ” (የሕዝብ ኹሉ እናት የመላእክት መዘዋወሪያ (ቦታ) የምስጋና ማደሪያ ለኾነችው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ይገባል) ብሏታል፡፡

ይኸው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ መልኩ እናትነቷን በሰባቱ ጊዜያት የሕማማት ሰላምታው ላይ፡-
“ሰላም ለኪ ቤተ ክርስቲያን እምየ ዘትጼንዊ መጽርየ ብኪ ጸናዕኩ እምከርሠ እምየ
ቤተ ክርስቲያን አክሊለ ርእስየ ሰላም ለኪ”
(እንደ ቀጋ የምትሸትቺ ቤተ ክርስቲያን እናቴ ሰላምታ ለአንቺ ይገባል፤ ከእናቴ ማሕፀን ዠምሮ በአንቺ ጸናኊ፤ የራሴ አክሊል የምትኾኚ ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ለአንቺ ይገባሻል)

“በሐኪ በሐኪ ቤተ ክርስቲያን እምነ
ግበሪ ሰላመ ማእከሌነ እምኀይለ ጸላኢ ወፀር ዕቀቢ ኪያነ ትንብልናኪ የሀሉ ምስሌነ፤ ሰላም ለኪ”
(ሰላምታ የተገባሽ እናታችን ቤተ ክርስቲያን ሰላም ሰላም እንልሻለን፤ በመኻከላችን ሰላምን አድርጊ፤ ከፍጹም ጠላት እኛን ጠብቂ፤ ልመናሽም ከእኛ ጋራ ይኹን) በማለት እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አወድሷል፡፡
በተጨማሪም ሠኔ ፳፩ ቀን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎልጎታ ቃል ኪዳን መቀበሏም ይታሰባል።
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን በረከት ይደርብን፡፡
በመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ
@Ethiopian_Orthodox