Get Mystery Box with random crypto!

የምትፈልግ አይደለህም፤ ለጠፈራቸው መማገሪያ ገመድ የምትሻ አይደለህም፣ እንጨትንም ለማገር፣ ለምሰሶ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

የምትፈልግ አይደለህም፤ ለጠፈራቸው መማገሪያ ገመድ የምትሻ አይደለህም፣ እንጨትንም ለማገር፣ ለምሰሶዋቸውም ገበታ፣ ለዙሪያቸውም ለማያያዣ ጭቃን የምትፈልግ አይደለህም፡፡ የቤተመቅደሶችን ፈቃድ ሁሉ ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ትፈጽማለህና፡፡ የማሳይህ እኚህ የቤተ መቅደሶች አኗኗር ከምድር ልብ ውስጥ እስከዛሬ አለ፡፡ ከአሁን ጀምሮ በእጅህ እስኪገለጡም ድረስ በምድር ልብ ይኖራሉ፡፡ በሰው ልጅ ጥበብ ያይደለ በእኔ ሥልጣን ከምድር ልብ ውስጥ ታወጣቸው ዘንድ መረጥሁህ፡፡ ሕዝቦቼ ተወልጄ አድጌ ሞቼ ተቀብሬ ከሞትም የተነሳሁባትን ሀገር ለማየት ኢየሩሳሌም በመሄድ ግማሹም በበረሃ ይቀር ነበር አሁን ግን አንተ ኢየሩሳሌምን በሀገርህ ትሠራለህ፡፡ በማንም እጅ ዳግመኛ ሊሠሩ የማይችሉ ቤተ መቅደሶቼን እንዳሳየሁህ ትሠራለህ፡፡ አንተም እንዳሳየሁህ በልብህ ውስጥ አኑራቸው፡፡ ስትሠራቸውም እየልካቸው ይሁን፤ ከእርዝመታቸውም በላይ ቢሆን፣ ከወርዳቸውም በላይ ቢሆን፣ በመወጣጫቸውም ላይ ቢሆን አንዳች እንዳትጨምር፡፡ ያሳየሁህ እሊህ ዐሥሩ መቅደሶች ከአንዲት ቋጥኝ ድንጋይ ሲወጡ አይተሃልና….› እያለ ጌታችን ሲነግረው ጻዲቁ ንጉሥ “ይህ እንዴት ይሆናል?” በማለት ይጠይቃል፡፡ ጌታም እውነት እልሃለሁ እነዚህ ያሳየሁህ መቅደሶች በሰው ኃይል የሚሠሩ ሆነው አይደለም፤ ጀማሪያቸው ሠሪያቸውና ፈጻሚያቸው እኔ ነኝ ነገር ግን ኃይሌ በአንተ እጅ እንዲገለጽ ለምክንያት ተልከሃል፤ አንተ አነጽካቸው እየተባለ እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ ስምህ ይጠራባቸዋል…›› እያለ ይቀጥላል የቅዱስ ላሊበላ ገድል፡፡ ቤተ መቅደሶቹንም ለመሥራት ቦታውን ያውቅ ዘንድ ሱባኤ ገብቶ ሳለ ዛሬ ቤተ ማርያም ካለችበት ቦታ ላይ ቅዱሳን መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ታይተውት በቦታው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መቅደሱን መሥራት ጀመረ፡፡ ዓሥሩን ቤተ መቅደሶች ሲሠራ እርሱ አንድ ክንድ ሠርቶ እንደሆነ ሌሊቱን አድሮ በቀጣዩ ቀን አሥር ክንድ ሆኖ ያገኘው ነበር፣ ቀንም በማይታወቁ ሰዎች አምሳል እየተገለጡ መላእክት ይራዱት ነበር፡፡

5. አንዳንድ ነገሮች ስለ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፡- ቅዱስ ላሊበላ ዓሥሩም ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በጣም በሚያስገርም ሁኔታ በውስጥና በውጭ ያሉት ብዙ ቅርጾች ነገረ ድኅነትን በምሳሌ እንዲወክሉ አድርጎ ነው ያነጻቸው፡፡ የክርስቶስን መከራና በእርሱም የተገኘውን ፍጹም ዘላለማዊ ድኅነት በእያንዳንዱ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዴት አድርጎ በምሳሌ እንዳስቀመጠው እጅግ አስገራሚ ነው፡፡
በላስታ ቅዱስ ላሊበላና አካባቢው የሚገኙ ሌሎች አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፡- ከአሥሩ የቅዱስ ላሊበላ አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ የቅዱስ ነአኵቶለአብና የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም አሸተን ማርያም በዋናነት ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጐበኛቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ በላሊበላና አካባቢው ግን እጅግ ጥንታዊና አስደናቂ የሆኑ በጣም በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሣርዝና ሚካኤል፣ ብልባላ ቂርቆስ፣ ብልባላ ጊዮርጊስ፣ አርባዕቱ እንስሳ፣ ትርኩዛ ኪዳነምሕረት፣ ገነተ ማርያም፣ ቀንቀኒት ሚካኤል እነዚህ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲሆኑ እንዲሁም ዋልድቢት ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም፣ አቡነ ዮሴፍ ገዳም፣ ገብረ ክርስቶስ ዋሻ ቤተክርስቲያን፣ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን፣ ቀደሊት ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እመኪና መድኃኔዓለምና እመኪና ልደታ፣ ማውሬ እስጢፋኖስ፣ የቅዱስ ገብረ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ማይ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ተከዜ ኪዳነምሕረትና መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ ከ485-536 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት የታነጹ ናቸው፡፡ ሌሎቹንና በሰሜን ላስታ ያሉትን ደግሞ እነ ላሊበላና ይምርሃነ ክርስቶስ አንጸዋቸዋል፡፡

ቅዱስ ላሊበላ እኛ ከምናውቃቸው ከድንቅ ሥነ ሕንፃዎቹ ሥራ በተጨማሪ ከሺህ ዓመታት በፊት በሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ፣ በውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙትና በመሳሰሉት ሁሉ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከሺህ ዓመታት በፊት አዳራሾችን፣ ፎቆችን፣ የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያዎችን፣ የእንግዳ መቀበያዎችን፣ የሕፃናት ማሳደጊያዎችን፣ የሕሙማን መፈወሻዎችን፣ የሕንፃ መሳሪያዎችን፣ የትምህርት ማዕከሎችን፣ የመደጎሻ ቦታዎችን ያቋቋመ መሆኑን የብራና ገድሉ እንደሚናገር የደብሩ አባቶች ይገልጣሉ፡፡ ወደፊት ተርጎመው እንሚያቀርቡልን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከዚህ በተጨማሪ የግእዝ ቋንቋን በጽሑፍ አበልፅጎ ያቆየ ባለውለታ ነው፡፡ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ውጭ ሌሎችንም በርካታ ቤተ መቅደሶች ሠርቷል፤ ከሀገራቸንም አልፎ በሱማሌ ሞቃዲሾ ላይ መቅደሰ ማርያም የተባለች ቤተክርስቲያን ሠርቷል፡፡ ክርስትናን ከግብፅ ምድር ጨርሰው ለማጥፋት ተንባላት በተነሡ ጊዜ ዓባይን ሊያግድባቸው ሲነሣ በብዙ ምልጃና ልመና ስለማራቸው በሀገሪቱ ውስጥ ክርስትና እስካሁን እንዲቆይ የራሱን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ላሊበላ ነቢይም ሆኖ፣ ሐዋርያም፣ ጻዲቅም፣ ሰማዕትም ሆኖ ጥበብ መንፈሳዊንና ጥበብ ሥጋዊን ከእግዚአብሔር ተሰጥቶት ንግሥናንና ክህነትን፣ ቅድስናንና ንጽሕናን በሚገባ አስተባብሮ በማያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅንነት ሲያገለግል ኖሮ ሰኔ 12 ቀን 1197 ዓ.ም ከፈጣሪው ታላቅ ቃልኪዳን ተቀብሎ በዝማሬ መላእክት፣ በመዝሙረ ዳዊት ቅድስት ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ ሰማያዊ ክብርን ወርሷል፡፡ ክቡር ሥጋውም ራሱ ባነጸው ቤተ ሚካኤል መቅደስ ሥር በክብር ዐርፏል፡፡

(ምንጭ፡- ገድለ ቅዱስ ላሊበላ፡- የቅዱስ ላሊበላ ደብር በ2003 ዓ.ም ያሳተመው፣ ስንክሳር ዘወርሃ ሰኔ)
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox