Get Mystery Box with random crypto!

ሰኔ ፲፪ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶ ሰባቱ ሰማያትን ካሳየውና በጌታችን ፊት አቅርቦት | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ሰኔ ፲፪
ቅዱስ ገብርኤል ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶ ሰባቱ ሰማያትን ካሳየውና በጌታችን ፊት አቅርቦት ካስባረከው በኋላ ጌታችንም በቅዱስ ቃሉ ‹‹ሕዝቦቼ የመከራና የሥቃዬን ቦታ ለማየት ኢየሩሳሌም በመሄድ በመንገድ እየቀሩ ስለሆነ አሁን ግን አንተ በሀገረ ሮሀ ኢየሩሳሌምን ትሠራለህ›› በማለት የቤተ መቅደሶቹን አሠራር በዝርዝር የነገረው ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ ዕረፍቱ ነው፡፡

ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ፡- ቅዱስ ላሊበላ ጌታችን የጠጣውን መራራ ሐሞት በማሰብ ሁልጊዜ ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጣ ነበር፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ላሊበላን ኢየሩሳሌም ወስዶት በዚያ ያሉ ቅዱሳን መካናትን ሁሉ አሳይቶ አሳልሞታል፡፡ ወደ ሰማይም ነጥቆ ወስዶ ሰባቱ ሰማያትን ያሳየው ሲሆን በጌታችን ፊትም አቅርቦት አስባርኮታል፡፡ ጌታችንም ‹‹ሕዝቦቼ የመከራና የሥቃዬን ቦታ ለማየት ኢየሩሳሌም በመሔድ በመንገድ እየቀሩ ስለሆነ አሁን ግን አንተ በሀገረ ሮሀ ኢየሩሳሌምን ትሠራለህ›› በማለት የቤተ መቅደሶቹን አሠራር በዝርዝር ነግሮታል፡፡ ከነገሠም በኋላ ሱባኤ ገብቶ ቤተመቅደስ የሚሠራበትን ቦታ በጸሎት ሲጠይቅ ዛሬ ቤተ ማርያም ካለችበት ቦታ ላይ የብርሃን አምደ ወርቅ ተተክሎ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ስላየ ቦታው እግዚአብሔር የፈቀደው መሆኑን አውቆ ሥራውን ጀመረ፡፡ ጌታችን ቀድሞ ‹‹እኔ ራሴ ነኝ እንጂ ቤተ መቅደሶቹን የምትሠራቸው አንተ አይደለህም፣ ነገር ግን በአንተ ስም እንዲጠራ ስለፈቀድኩ ሄደህ ሥራ›› ብሎ እንዳዘዘው ቅዱስ ገድሉ ይናገራል፡፡ ላሊበላ ዓሥሩን ቤተመቅደሶች ሲሠራ እርሱ አንድ ስንዝር ሠርቶ እንደሆነ ሌሊቱን ዓሥር ስንዝር ሆኖ ያገኘው ነበር፡፡ ቀንም ሲሠራ ቅዱሳን መላእክት በማይታወቁ ሰዎች አምሳል ሆነው ይራዱት ነበር፡፡ በመጨረሻም ጌታችን በገሃድ ተገልጦለት በቦታው ላይ እጅግ አስገራሚ ቃልኪዳኖችን ሰጥቶታል፡፡

ከ10ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (920-1253 ዓ.ም ድረስ) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ ‹‹የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት›› ወይም ‹‹የላስታ መንግሥት›› በመባል ይታወቃል፡፡

የላስታ ነገሥታት የዘር ሀረጋቸው ከንጉሥ ሰሎሞን ዘር ሲያያዝ የመጣ ነው፡፡ ከላስታ (ከዛጉዌ) ነገሥታት መካከል ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነአኵቶለአብ እነዚህ አራቱ ነገሥታት እንደ መልከጼዴቅ (ዘፍ 14፡18) ክህነትን ከንግሥና፣ ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አንድ አድርገው በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስና አገልግለው አልፈዋል፡፡ በንግሥናቸው ሀገራችንን በመልካም ሥራና በቅድስና ከማስተዳደራቸው በተጨማሪ ቅዱሳን ጻድቃን ሆነው እግዚአብሔርን በብዙ ድካም በመልካም ተጋድሎአቸው ያገለገሉና አገልግሎታቸውም ሆነ ቅድስናቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ስለተመሰከረላቸው ጌታችን የሰጣቸውን ቃልኪዳን መሠረት በማድረግ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን የቅድስና ማዕረግ ሰጥታ፣ በስማቸው ቤተክርስቲያን አንጻ፣ ጽላት ቀርፃ በዓላቸውን እያከበረች መታሰቢያቸው ተጠብቆ ለዘለዓለም እንዲኖር አድርጋለች፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን የቅዱስ ላሊበላን እጅግ ድንቅ የሆኑ ሥራዎቹን ዓለም ከሚመለከትበት የተለየ መንፈሳዊ ዐይን ሊኖረን ይገባል፡፡ ስለዚህም የቅዱስ ላሊበላን የቅድስና ሕይወትና ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበረው ግንኙነት ገድለ ቅዱስ ላሊበላን መነሻ በማድረግ ብዙ ነገሮችን ቀጥሎ እናያለን፡-
1. ቅዱስ ላሊበላ ከአባቱ ዣን ስዩምና ከእናቱ ኪርወርና ጌታችን በተወለደበት ዕለት ታኅሣሥ 29 ቀን 1101 ዓ.ም በላስታ ቡግና ወረዳ ልዩ ስሟ ሮሀ በተባለችው ሥፍራ ተወለደ፡፡ የልደቱን ነገር አስቀድሞ ቅዱስ ሚካኤል ለእናቱ ነግሯት ነበርና በተወለደ ጊዜ ብዙ ነጫጭ ንቦች መጥተው በሰውነቱ ላይ አርፈው እንደ ማር እየላሱት ስለታዩ እናቱ ‹‹ልጄን ንብ ዘበኛ ሆኖ ይጠብቅልኛል›› ስትል ስሙን ‹‹ላል ይበላል›› ብላዋለች፡፡ ላል በአገውኛ ንብ ማለት ነው፡፡ በጊዜ ብዛት በተለምዶ ነው ‹‹ላሊበላ›› ተብሎ መጠራት የተጀመረው፡፡ ንቦቹ ግን ሥጋዊ ንቦች ሳይሆኑ በንብ የተመሰሉ መላእክት ናቸው፡፡ ንጉሥ መሆኑን እያመለከቱ የሃይማኖትና የምግባር ማር ከእርሱ ይቀዳል ሲሉ በንብ ሠራዊት ተመስለው ሰውነቱን ላሱት፡፡ እንደ ዮሐንስና እንደ ኤርምያስም በእናቱ ማኅፀን ሳለ ነው መንፈስ ቅዱስ የሞላበት፡፡

ከዚህ ቀጥሎ በገድሉ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ አስደናቂ ነገሮችን እናያለን፡፡
2. ቅዱስ ላሊበላ ያነጻቸውን አብያተ ክርስቲያናት መመልከት ያለብን በቅርስነታቸውና በቱሪስት መስህብነታቸው ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የተገኙ ብቸኛ መንፈሳዊ ሀብቶቻችን መሆናቸውን ነው፡- ስለ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ከማንሳታችን በፊት በመጀመሪያ እውነተኛ የሕይወት ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መመልከት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀድሞ በሕገ ልቡና ከዚያም በሕገ ኦሪት እግዚአብሔርን ስታመልክ ኖራለች፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያቱ እንኳን ለስብከት ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ ነው በ34 ዓ.ም በራሷ ሐዋርያ በጃንደረባው ባኮስ አማካኝነት በክርስቶስ ማመንንና ጥምቀትን ወደ ሀገሯ ያመጣችው፡፡ የዚህ ደግሞ ምስክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ 1ኛ ነገ 10፡1-13፣ ሐዋ 8፡26-40፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ እስከ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ወደ ኢየሩሳሌም እየሔዱ ሃይማኖታዊ ጉዞ ያድርጉ ነበር፡፡

ከ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ግን ከኢትዮጵያ ተነስቶ በሱዳን በግብፅ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም በእግርና በእንስሳት ጉዞ ለማድረግ የመንገዱ አድካሚነትና በረሃማነት የሚባክነው ጊዜ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ተሻግሮም እስከ ግብፅና ሱዳን ድረስ የእስልምና ሃይማኖት ስለተጠናከረ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ወደ ኢየሩሳሌም ለመጓዝ አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ለሃይማኖታዊ አምልኮና ስግደት ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉት ጉዞ ተቋረጠ፡፡ ይህ ሁኔታም ሲያያዝ እስከ ቅዱስ ላሊበላ ዘመን ደርሷል፡፡

ቅዱስ ላሊበላም የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ወደ ኢየሩሳሌም ያደርጉት የነበረው ጉዞ በመቋረጡ በእጅጉ እያዘነ ተግቶ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ የኢየሩሳሌምንም አምሳያ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትን በሀገሩ ለመሥራት ይመኝ ነበር፡፡ ጥቂት ነገር ሲለምኑት አብዝቶ መስጠት ለእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነውና ላሊበላ ምድራዊ ኢየሩሳሌምን በሀገሩ ለመሥራት ሲያስብ ልዑል እግዚአብሔር በጥበቡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ (2ኛ ቆሮ 12፡1-7) ወደ ሰማይ አሳርጎት ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን አሳይቶታል፡፡ ጌታችንም ‹‹ሕዝቦቼ የመከራና የስቃዬን ቦታ ለማየት ኢየሩሳሌም በመሄድ በመንገድ እየቀሩ ስለሆነ አሁን ግን አንተ በሀገረ ሮሐ ኢየሩሳሌምን ትሠራለህ›› በማለት የቤተ መቅደሶቹን አሠራር ሁሉ በዝርዝር ነግሮታል፡፡ በሰማያዊት ኢየሩሳሌምም ምሳሌ በሀገሩ ላይ ወጥ ከሆኑ የዓለት ድንጋዮች መላእክት እየተራዱት ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያንጽ ነግሮታል፡፡
3. ጠላት ለክፉ ያሰበውን እግዚአብሔር ለበጎ ያደርገዋል፡- ወደኋላ ተመልሰን የቅዱስ ላሊበላን የልጅነት ሕይወቱን እናንሳ፡- ቅዱስ ላሊበላ እናትና አባቱ ከሞቱበት በኋላ ወደ ጎጃም በመሄድ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን፣ ብሉይና ሐዲስን በደንብ ተምሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ደብረ ሮሐ ተመልሶ መጥቶ ነግሦ ከነበረው ከወንድሙ ከገብረ ማርያም ዘንድ ተቀመጠ፡፡ ‹‹ከገብረ ማርያም ቀጥሎ የሚነግሠው ላሊበላ ነው›› ተብሎ ትንቢት ስለተነገ