Get Mystery Box with random crypto!

ዕርገት ከጌታችን ፱ቱ አበይት በዓላት ውስጥ አንዱ ዕርገት ነው፡፡ “እያዩት ወደሰማይ ዐረገ”(ሉ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ዕርገት

ከጌታችን ፱ቱ አበይት በዓላት ውስጥ አንዱ ዕርገት ነው፡፡

“እያዩት ወደሰማይ ዐረገ”(ሉቃ 24÷50 የሐዋ 1÷9)

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ ለሰላሳ ዘጠኝ ቀናት ያህል ለሐዋርያቱ በተለያየ ጊዜ እየተገለጠ ለአገልግሎት ሲያዘጋጃቸው እና ስለ እግዚአብሔር መንግስት ምስጢር እያስተማራቸው ከቆየ በኋላ በ፵ኛው ቀን በሐዋርያቱ ፊት አርጓል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው የጌታችንንአበይት በዓላት አንዱ ዕርገት ነው።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተነሣ በ፵ኛው ቀን ወደ ሰማይ አረገ ያረገበትም ቦታ ቢታንያ አጠገብ የሚገኘውደብረ ዘይት የሚባለው ተራራ ነው። አሥራ አንዱ ሐዋርያትን እዚያ ድረስ ከወሰዳቸው በኋላ ባርኳቸው እያዩት ዐረገ። ደመና ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቀደመ ክብሩ፤ በመለኮታዊ ክብሩ ወደ ሰማይ አርጎ በአባቱ ቀኝ ተቀመጧል። ጌታችን ያረገውም በለበሰው ሥጋ በመሆኑ እና ለሁለተኛ ጊዜ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ ይህን ክብር እኛም እንድናገኝ ምሳሌ ሲሆነን ነው።

በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣንበክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌ . ፪፡፮ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዕርገቱ አስመልክቶ ከተናገራቸው ሦስት ነገሮች ውስጥ፦

#የመጀመሪያው፤ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ። ዮሐ . ፲፪፡፴፪
#ሁለተኛው ደግሞ፤ ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ዮሐ .፲፬፡፲፰
#ሶስተኛው፤ እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። ዮሐ . ፲፮፡፯


የጌታችን የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ለእኛ ትልቅ ተስፋ ነው ስለዚህም ሐዋርያት ጌታችን ሲያርግ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ይመለከቱት እንደነበር እኛም በታላቅ ተስፋ የጌታን ነገር ልናስብ ይገባል። ነቢዩ ዳንኤል ስለ ጌታችን ዕርገት እና በአብ ቀኝ ስለመቀመጡ እንዲህ ሲል በትንቢት ተናግሮ ነበር፤ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅየሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ
በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም
የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥መንግሥቱም የማይጠፋ ነው። ዳን. ፯፡፲፫ - ፲፬ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በአብ ቀኝ ተቀመጠ ስንል ጌታ ከአብ ጋር እኩል ነው ማለታችን ነው።

ከ፬ቱ ወንጌላት ውስጥ ይህን የዕርገቱን ታሪክ የመዘገቡት የማርቆስ ወንጌልና የሉቃስ ወንጌል ናቸው። ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን ማልዶ በተነሣ ጊዜ፥ አስቀድሞ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ታየ።እርስዋ ሄዳ ከእርሱ ጋር ሆነው ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ አወራችላቸው፤ እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደታያት ሲሰሙ አላመኑም። ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ባላገር ሲሄዱ በመንገድ በሌላ መልክ ተገለጠ፤ እነርሱም ሄደውለሌሎቹ አወሩ፤ እነዚያንም ደግሞ አላመኑአቸውም። ኋላም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ተገለጠ፥ ተነሥቶም ያዩትን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ። እንዲህም አላቸው። ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ። ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። ማር. ፲፮፡፱-፲፱ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ። እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየወደ ሰማይም ዐረገ። ሉቃ. ፳፬፡፵፰-፶፩

ቅዱስ ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን ሲጽፍ ስለ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት አብራርቶ ጽፎታል። እንዲህ ሲል፦ ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖለእነርሱ ራሱን አሳያቸው። ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን። ከእኔ የሰማችሁትንአብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ። እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለውጠየቁት። እርሱም አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግንመንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድርዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎችበአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው። ሐዋ. ፩፡፫-፲፩

ክርስቲያኖች በሰማያት ስፍራ ከጌታችን ከመድሃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረው እንደሚቀመጡ የእርሱ ዕርገት ያረጋግጥልናል። ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ጌታችን እርገት እንዲህ ሲል ይመክረናል፤ እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና። ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበትጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። ቆላ. ፫፡፩-፬

ኖርንም ሞትንም የክርስቶስ ነንና ዘላለማዊ ሕይወትን እንወርስ ዘንድ አምላካችን ይርዳን። ልዑል እግዚአብሔር በኑሮአችን ሁሉ ባርኮን፤ ቀድሶን፤ በእርሱ ፈቃድ እንድንኖር ይርዳን። የምንሻትን መንግስተ ሰማያትን ያወርሰን ዘንድ የእናቱ የድንግል ማርያም አማላጅነት፤ ስለ እርሱ ክብር ሲሉ ሕይወታቸውን ሰውተው ያለፉት ቅዱሳን ሰማዕታት ምልጃ እና ጸሎት አይለየን አሜን።

[በዲያቆን ንጋቱ አበበ]
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox