Get Mystery Box with random crypto!

የኤማሁስ መንገደኞች ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ወደሚርቀው ወደ ኤማሁስ መንደር ጸጥ ባለው አሸዋማ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

የኤማሁስ መንገደኞች

ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ወደሚርቀው ወደ ኤማሁስ መንደር ጸጥ ባለው አሸዋማ በረሃ ረጅሙን መንገድ ተያይዘውታል። የበረሃው ወበቅ ሲያዩት ወደላይ እየተምዘገዘገ ውልብ ውልብ እያለ ሲወጣ ይታያል። ሁለት ሰዎች ከመነሻቸው ጀምሮ እስከ አሁን የመጡበትን ርቀት ባለማስተዋል የልባቸውን ጭንቀት ያወጋሉ። የሚያወሩትም ስለሰሞኑ በምድረ ኢየሩሳሌም ተደርጎ የማያውቅ ወደ ፊትም የማይደረግ ግፍ ተፈጽሟል፣ ፍርድ ተስተጓጉሏል ፣ ድሀ ተበድሏል እያሉ ነበር።

ሰዎቹ የጸሐዩን ግለት፣ የመንገዱን ርቀት፣ ረሃብና ድካሙን ረስተው ስለዚያ በግፍ ስለተገደለው ደግ ሰው ያወራሉ። አብሯቸው በቆየባቸው ሦስት አመታት ውስጥ ያዩትን የተለየ ፍቅር፣ ቸርነት፣ ትህትና፣ ደግነት፣ ተዓምራት እያሰቡ፡ ከአንደበቱ እንደ ማር እያዘነበ ያስተማራቸውን የጣፈጠ ቃል እያውጠነጠኑ ይነጋገራሉ። ፍቅሩ እንደ ልክፍት ተጠናውቷቸው ስለ እርሱ ከማሰብ አልቦዘኑም። ስድሳውን ምዕራፍ እንደተጓዙ ያላስተዋሉት ሦስተኛ ሰው ተቀላቀላቸው።

ይህ ሦስተኛው ሰው ድንገትም፦ “እንዲህ እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ እርስ በርስ የምትነጋገሯቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው?”ሲል ጠየቃቸው። በንግግሩ እጅጉን ተገርመው ከሁለቱ አንዱ ቀለዮጳ ፈጠን በማለት፦ “አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን?” ብሎ ጠየቀው። ሰውየውም ምንም እንዳልሰማ በመሆን፦ “ይህ ነገር ምንድር ነው?” አላቸው። “ከወዴት ሀገር የመጣ እንግዳ ይሆን?” ሲሉ አሰቡና
እንዲህ አሉት፦ “በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት” አንድ በአንድ ከልባቸው በማዘን አወሩለት። ንግግራቸው ቀጠሉና “እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው።” አስቀድሞ እንደሚነሳ የነገራቸው ቢሆንም አሁን ግን ሞቶ ከተቀበረ ሦስት ቀን እንደሞላው ነገሩት። ይህም ሰው ንግግራቸው በጽሞና ያደምጣቸዋል።

በእስራኤል ሁሉ የሞቱ ወሬ ተናፍሶ እነርሱም ተስፋ ቆርጠው ወደ መንደራቸው ኤማሁስ እየተጓዙ ነው። ግን ደግሞ የዛሬው የሴቶቹ ወሬ አጠራጥሯቸዋል። ቀጠል አድርገውም አሁን ደግሞ ያስገረመን አሉ፦ “ከእኛ መካከል ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የሄዱ ሴቶች ሥጋውን ባጡት ጊዜ ተነስቷል በዚያ የለም አሉን” አሉ ግራ በተጋባ በሰከነ ድምጽ።
ደግሞም ሴቶቹ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ፦ “ሕያው ነው እርሱ ተነሥቶአል የሚል የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን” ሲሉ መጥተው ነግረውን ነበር አሉት። “ከእኛም ጋር ከነበሩት እነ ጴጥሮስ ወደ መቃብር ፈጥነው ሄደው ሴቶቹ እንደ ተናገሩት አጥተውታል፥ እርሱን ከመቃብር አላዩትም።” አሉት ድካም በተላበሰ አንደበት።

የልባቸውን መዛል የተመለከው በጸጥታ ታሪኩን ያዳምጥ የነበረው ሰው፦” እናንተ የማታስተውሉ፥ ነብያትም የተናገሩትንም ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፡ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን?” አላቸው።

ከሙሴና ከነብያት ጀምሮ ስለ እርሱ በመጽሐፍ የተነገረውን እየተረጎመላቸው ሲጓዙ ማምሻውን ከመንደራቸው ኤማሁስ ደረሱ። ማንነቱን ያልተረዱት በቃሉ ብርታት የተማረኩት የሩቅ ተጓዥ መንገደኛ ስለመሰላቸው አብሯቸው ያድር ዘንድ ግድ አሉት። “ማታ ቀርቧልና፡ ቀኑም ሊመሽ ጀምሯልና እባክህ ከእኛ ጋር እደር?” አሉት በሚማጽን ንግግር። እሱም ከእነርሱ ጋር ሊያድር ገባ። ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው፤ ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። እርስ በርሳቸውም። በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ።

በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ጨለማ ነውና ከእኛ ጋር እደር እንዳላሉት እነርሱ ግን ፍርሐት ተወግዶላቸዋልና በጨለማ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር ለነበሩትም "ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቷል" እያሉ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው። እነርሱም በመንገድ የሆነውን እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንደ ታወቀላቸው ተረኩላቸው።
~~~~
ቤተክርስቲያናችን በዛሬው በሦሥተኛ የትንሣኤ እሑድ ቅዳሴዋ በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ ፳፬፥፲፫-፴፫ ላይ ስለ ኤማሁስ መንገደኞች የተጻፈውን ምንባብ ታነባለች።

ሁለቱ መንገደኞች ሦሥተኛው ሰው አምላካቸው መሆኑን ካወቁ በኋላ ጨለማን ሳይፈሩ ከኤማሁስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደተመለሱ እኛም ቤተክርስቲያናችን ስለአምላካችን በነገረችን መሰረት አምላካችንን አውቀን ከኤማሁስ(ከዓለም) ወደ ኢየሩሳሌም(ቤተክርስቲያን) እንመለስ ዘንድ የእርሱ ፈቃድ ይሁንልን : አሜን!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox