Get Mystery Box with random crypto!

ከትንሣኤ በኋላ ያሉ ዕለታት እሁድ ዳግማይ ትንሣኤ ዳግማይ ትንሣኤ ማለት ጌታችን በተደጋጋሚ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ከትንሣኤ በኋላ ያሉ ዕለታት
እሁድ
ዳግማይ ትንሣኤ

ዳግማይ ትንሣኤ ማለት ጌታችን በተደጋጋሚ ለሐዋርያቱ እና ለተለያዩ ሰዎች በተለያየ ሥፍራ መገለጡን የምናስብበት ሳምንት ነው፡፡
ቤተክርስቲያን ከትንሣኤው እስከ ዳግማይ ትንሣኤው ያለውን ሳምንት እንደ አንድ ቀን ነው የምታየው ክብር ይግባውና የትንሣኤው ጌታ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው ዕለት ጀምሮ ከመግደላዊት በመጀመር ለልዩ ልዩ ሰዎች ተገልጧል፡፡
፩. ለመግደላዊት ማርያም ተገልጧል፡፡(ዮሐ፳፡፲፩)
፪. ለሴቶች ተገልጧል፡፡(ማቴ፳፰፡፱)
፫. ለሐዋርያው ጴጥሮስ ተገልጧል፡፡(ሉቃ፳፬፡፴፬)
፬. ለኤማውስ መንገደኞች ተገልጧል፡፡(ሉቃ፳፬፡፲፫)
፭. ከሐዋርያው ቶማስ በቀር ለሐዋርያት ተገልጧል፡፡(ዮሐ፳፡፲፱)
፮. ሐዋርያው ቶማስ ባለበት ለደቀ መዛሙርቱ በዝግ ቤት ተገልጧል፡፡(ዮሐ፳፡ ፳፮)
፯. በጥብርያዶስ ለሰባቱ ሐዋርያት ( ጴጥሮስ ቶማስ ናትናኤል ሉቃስ ኒቆዲሞስ ይሁዳ ያዕቆብ ) ተገልጧል፡፡
፰. ለአምስት መቶ ሰዎች ተገልጧል፡፡(፩ቆሮ፲፭፡፮)
፱. ለሐዋርያው ያዕቆብ ተገልጧል፡፡(፩ቆሮ፲፭፡፯)
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተገለጠባቸው በእያንዳንዱ መገለጦች ውስጥ ለሐዋርያቱ ሦስት አደራዎችን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህም :-
በመጀመሪያው የትንሣኤ ዕለት የኃጢአት ስርየት የማድረግን ሥልጣን ሰጥቷቸዋል(ዮሐ፳፡፳፫)
በሁለተኛው ደግሞ የማስተማር ጸጋ ሰጥቷቸዋል(ማቴ፳፰፡፲፮-፳)
በሦስተኛው ሕጻናትን ፤ ወጣትን እና ሽማግሌዎችን የመጠበቅና የመምራት ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል፡፡(ዮሐ፳፩፡፲፭-፲፰)
በዚህም ሐዋርያዊት ወይም የሐዋርያትን ፍኖት የተከተለች በሐዋርያት በኩል ይህንን ሁሉ ጸጋ ያገኘች ቅድስት ፣ አንዲት ፣ ኩላዊት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ሁሉንም አደራ እና መመሪያ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች፡፡
ሐዋርያዊት የሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በዚህ ዕለት ልክ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ጋር በነበሩበት ዘመን ይሰማቸው የነበረውን ደስታ በማሰብ ሥርዓተ አምልኮቷን ትፈጽማለች፡፡
በግጻዌው መሰረት በሁሉም አብያተ ክርስቲያናትም ሆነ ገዳማት የሚዘመረው
መዝሙር "ይትፌሳህ ሰማይ ወትትሐሰይ ምድር" ትርጉም "ሰማይ ይደሰታል ምድርም ሐሴት ታደርጋለች" የሚለው ሲሆን ምስባኩ ደግሞ "ይትነሣእ እግዚአብሔር ወይዘረው ጸሩ ወይጎይዩ ጸላእቱ እምቅድመ ገጽ ከመ የሀልቅ ጢስ ከማሁ የሀልቁ" ትርጉም እግዚአብሔር ይነሳ ጠላቶቹ ይበተኑ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ ጢስ እንደሚበን እንዲሁ ይብነኑ" (መዝ፷፯(፷፰)፩-፪)
ቅዳሴው የዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ሲሆን ወንጌሉ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሃያ ከቁጥር አሥራ ዘጠኝ እስከ ፍጻሜ ነው፡፡ በዚህ ወንጌል ላይ ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ ያላቸውን ሐዋርያት እናገኛለን፡፡ "ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው፡፡" (ዮሐ፳፡፳)
ያም ቀን ዕለተ እሑድ ማታ ላይ ነበር፤ የጨለማው መጨለም ፤ የአይሁድ ዛቻና ማስፈራራት ሐዋርያትን እጅጉን አስጨንቋቸዋል ከአሁን አሁን ገደሉን ፤ በቃ ጠፋን፤ይህን እና ይህን ብቻ እያሰቡ በራቸውን እንዳይከፍቱት በጠንካራ ቁልፍ ቆልፈው የጭንቀታቸው መጠን እየጨመረ እየጨመረ... ባለበት በዚህ ጊዜ ምንም እንኳን ከመከራው እና ከጭንቀቱ ብዛት በሩን ዘግተው ሞታቸውን ቢጠባበቁም በሞት ላይ ስልጣን ያለው ተስፋን መቀጠል የሚችል አምላክ "ሰላም ለእናንተ ይሁን" ብሎ መካከላቸው ሲቆም ከመቅጽበት ጌታን ባዩ ጊዜ በሐዘን የጨፈገገው ፊታቸው በደስታ በራ፡፡ ክብር ለአምላካችን ይሁን፡፡ የእኛንም የተዘጋ ቤታችንን ከፍቶ ገብቶ በሐዘን እና በጭንቀት የጨፈገገው ፊታችንን በደስታ አብርቶ ሰላማችንን ይመልስልን፡፡ አሜን!
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox