Get Mystery Box with random crypto!

እንደሚመጡና ‘ሰማይና ምድር ያልፋል፤ ጌታ ይመጣል፤ ትንሣኤ ሙታን ይደረጋል፤ ያላችሁት የት አለ?’ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

እንደሚመጡና ‘ሰማይና ምድር ያልፋል፤ ጌታ ይመጣል፤ ትንሣኤ ሙታን ይደረጋል፤ ያላችሁት የት አለ?’ እያሉ የሚክዱና የሚያስክዱ ሰዎች እንደሚመጡ አስቀድሞ ነግሮናል። (2ኛ ጴጥ 3፥1-18)።  እንዲሁም ጌታችን በወንጌሉ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ”(ዮሐ 11፥25)። ብሎ የሰበከውን ህያው ቃል ያልተገነዘቡ የቅዱስ ጴጥሮስንና የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት እንዳቃለሉና እንዳፌዙ ሁሉ ዛሬም በዘመናችን ስለትንሣኤ ሙታን፣ ስለ ዘላለማዊ ህይወት ሲነገራቸውና ሲሰበክላቸው የማያምኑ ብዙ ሰዎች መኖራቸው እንግዳ ነገር እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባናል። እኛ ግን ይልቁንም ቅዱሳት መጻፍትን በማንበብና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን በመጠየቅ ይበልጥ ስለትንሣኤ ልንረዳና በመጨረሻው ስዓት የክብር ትንሣኤ ባለቤት እንድንሆን መትጋት ይኖርብናል። በትንሣኤ የምናምንም የማያምኑም ለፍርድ መነሣታችን አይቀርምና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ በሚገባ ቋንቋ አብራርቶ በምሳሌ ሲያስተምር «ነገር ግን ሰው፥ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል፡፡» ብሎ ከጠየቀ በኋላ፥ «አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፡፡» ብሏል፡፡ ከዚህም አያይዞ «የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል÷ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል÷ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል÷ መንፈሳዊ አካል ይነሣል ፤ ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ፡፡ እንዲሁ ደግሞ፡- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም (ክርስቶስ) ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው። ሁለተኛው ሰው ( ክርስቶስ ) ከሰማይ ነው፡፡ መሬታዊው እንደሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲህ ናቸው÷ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው ፡፡ የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን፡፡» ብሏል። ፩ኛቆሮ ፲፭÷፴፭-፵፱፡፡  በአጠቃላይ መድኃኔዓለም ክርስቶስ እኛን የወደደበት ሕይወቱን እስከ መስጠት ደርሶ ቤዛ የሆነበትን ምሥጢር የሰው ሕሊና መርምሮ ሊደርስበት የሚችል አይደለም፡፡ ተነጻጻሪ ተወዳዳሪ አቻ ወይም አምሳያ የሌለው ልዩ ነውና፡፡ ስለሆነም የትንሣኤ ሙታንን ምሥጢር ተረድተን በክርስቲያናዊ ምግባር መኖር አለብን። በትንሳኤ ሙታን ጊዜ ስንነሣ በጌታችን ፊት እንዳናፍር በትዕዛዙና በሕጉ ጸንተን ጌታችን "ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ" (ዮሐ 6፥54)፤ እንዳለ የክብር ትንሣኤ አግኝተን ከምርጦቹ ጋር በቀኙ እንዲያቆመን የጌታችንን ትንሣኤ ስናከብር ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን በመቀበል ለክብር ትንሣኤ ተዘጋጅተን ሊሆን ይገባል። ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች እንደጻፈልን በ፩ኛቆሮ ፲፭÷፳-፳፫፡፡«አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ሞት በሰው (በቀዳማዊ አዳም) በኵል ስለመጣ፥ ትንሣኤ ሙታን በሰው (በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ዳግማዊ አዳም በተባለ በክርስቶስ) በኩል ሆኗልና፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኵራት ነው፤»  እንዲል የትንሣኤያቸን በኩር ክርስቶስን አብነት አድርገን፣ ቃሉን ሰምተን፣ ሕጉን ጠብቀን፣ ትዕዛዙን አክብረን፣ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን፣ ሥጋውን በልተን፣ ደሙን ጠጥተን፣ በንስሐ ተሸልመን፣ በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢፅ (ወንድምን በመውደድ) ጸንተን ብንኖር የትንሣኤውን ትርጉም አውቀነዋል፣ ገብቶናል ማለት ነው፡፡ ከትንሣኤ ሥጋ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን፣ በንስሐ ታጥበን ሥጋውና ደሙን ተቀብለን፣ ተዘጋጅተን እንድንኖር የአምላካችን ቸርነት የወላዲተ አምላክ የድንግል ማርያም፣ የቅዱሳንና የቅዱሳን መላእክት አማልጅነትና ተራዳኢነት አይለየን። አሜን!

መልካም በዓል!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox