Get Mystery Box with random crypto!

የሰሙነ ሕማማት ሰባተኛ ቀን ቅዳሜ የማይሞተው አምላካችን በፈቃዱ ቅድስት ነፍሱን ከሥጋው ከለየ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

የሰሙነ ሕማማት ሰባተኛ ቀን
ቅዳሜ

የማይሞተው አምላካችን በፈቃዱ ቅድስት ነፍሱን ከሥጋው ከለየ በኋላ ሰማይና ምድር የማይችሉት አምላካችን እኛን ያስነሳ እና ነጻነት ይሰብከን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ነጻ ሲያወጣ በአካለ ሥጋም ያለመለያየት በመቃብር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ሙስና መቃብር ሳያገኘው ቆይቷል።
ይህንን ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል"ነፍሱን በሲኦል አልተወም ሥጋውንም ሙስና መቃብርን አላየም መለኮቱ ከሁለቱም አልተለየም ሁለንተናው ከነፍስ ጋር በሲኦል ነበር በሲኦል ለጻድቃን የምሥራችን አበሰረ ሁለንተናው ከሥጋ ጋር በመቃብር ነበር እንጂ በቦታው ሁሉ ምሉዕ ነውና" (ሃይ. አበ ዘቄርሎስ ፸፩:፲፭-፲፮)
ለሁላችን የማያልፍ ድኅነትን ፣ ሥርየተ ኃጢአትን ፣ ቅድስናን ፣ አሸናፊነትን እና ይቅርታን ይሰጠን ዘንድ ሞታችንን ሞተ የነገረንን ትንቢት ፈጸመ" ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።" እንዲል። (ማቴ፲፪:፵)
ጌታችን ከዐርብ ሠርክ እስከ እሁድ መንፈቀ ሌሊት ድረስ ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት በመቃብር ዐርፏል። እነዚህ ቀንና ሌሊት የራሳቸው ትርጉም አላቸው። የነገረ ክርስቶስ መጽሐፍ ጸሐፊ መጋቤ ሐዲስ ክቡር ዶክተር ሮዳስ ስለ ሶስት ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳሉ:-
፩. ለአዳም ፣ ለሔዋን ፣ ለሕጻናቱ ሊክስ
፪. ለሥጋ ፣ ለነፍስ ፣ ለደመ ነፍስ ሊክስ
፫. ሞትን ፣ ፍዳን ፣ ኃጢአትን ሊያጠፋ ጌታችን ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት በመቃብር ዐርፏል። (ነ.ክርስቶስ ገጽ፻፸፰)
አቆጣጠሩ ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት የሚመጣው ስንል ከላይ እንዳየነው የተቀበረው በሠርክ (፲፩) ሰዓት ነው የተነሳው ደግሞ እሁድ መንፈቅ(፮) ሰዓት ነው።
አንደኛው ቀን ከአርብ ነግህ (ጠዋት) - ስድስት ሰዓት ቀን ሆኗል ፣ ከአርብ ስድስት - ዘጠኝ ሰዓት ጨልሟል ሌሊት ሆኗል ይህ አንድ ቀን ይባላል።
ሁለተኛው ቀን ከአርብ ዘጠኝ ሰዓት-ሠርክ ቀን ሆኗል ፣ የአርብ ሌሊት ሲደመር ይህ ሁለተኛ ቀን ይባላል።
ሦስተኛው ቀን ከቅዳሜ ነግህ እስከ ሠርክ ቀን ሆኗል ፣ የቅዳሜ መንፈቀ ሌሊት ሲደመር ሦስተኛው ቀን ይባላል

ቀዳም ስዑር
ጌታችን ቀድሞ አዳምን ሔዋንን አርብ ፈጥሮ ቅዳሜ እንዳረፈ ሁሉ አሁንም ያጡትን ገነትን ባጡበት አርብ ዕለት ሰጥቶ ቅዳሜ በመቃብር አርፎባታል ስለዚህም የተለየች ቅዳሜ ናት።

አራቱ ስያሜዎች

፩. ቀዳም ስዑር
ስዑር ማለት የግእዝ ግስ ሆኖ በአማረኛ የተሻረ ማለት ሲሆን በአንድ ላይ ሲነበብ የተሻረ ቅዳሜ የሚል ትርጓሜ እናገኛለን። ምክንያቱ እንደ ቀደመቺቱ ሰንበት የማናርፍባት ይልቁንም ደቀመዛሙርቱን አብነት አድርገን በጾም በሀዘን ህማሙን እያሰብንባት የምናሳልፋት ቀን በመሆኗ ቀዳም ስዑር ተብላለች።

፪. ዐባይ ሰንበት
አምላካችን ሃያ ሁለቱን ስነ ፍጥረት ፈጥሮ እንዳረፈባት የማዳኑንም ስራ በመስቀል ላይ ፈጽሞ በአዲስ መቃብር ዐርፎ ውሎባታልና ዐባይ ሰንበት ተብላለች።

፫.ቅዱስ ቅዳሜ
በአካለ ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን አድኖበታል ፣ ሲዖልን በዝብዟል ፣ ምርኮን ለራሱ ጨምሯል ፣ ዲያብሎስን አሳፍሯል ፣ የዕዳ ደብዳቤያችንን ደምስሷል ከሌሎች ቀናት ሁሉ የተለየች በመሆኗ ቅዱስ ቅዳሜ ተብላለች።

፬. ለምለም ቅዳሜ
በዚህ ዕለት በኖኅ ዘመን የጥፋቱ ውኃ ማለቁን የሰላም አብሳሪ እርግብ ለኖኅ ቄጤማ እንዳመጣችለት አሁንም የጥፋቱ ሞት ራቀልን ፣ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋገርን ፣ አንቀጸ ገነት ተከፈተልን ሲሉ ካህናት አባቶቻችን የቅዳሜው የነግህ ጸሎት ከተጠናቀቀ በኋላ ለምዕመኑ ለምለም ቄጤማ ስለሚሰጡ ምዕመናንም በግንባራችን ላይ አድርገን ትንሣኤውን ስለምናከብር ለምለም ቅዳሜ ተብላለች።

"ዲያብሎስ ታሰረ ጌታ ተመረመረ"

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox