Get Mystery Box with random crypto!

የሰሙነ ሕማማት ስድስተኛ ቀን አርብ ዕለተ ዓርብ በቤተክርስቲያን ልዩ ቀን ነው፡፡ የማይ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

የሰሙነ ሕማማት ስድስተኛ ቀን
አርብ

ዕለተ ዓርብ በቤተክርስቲያን ልዩ ቀን ነው፡፡ የማይታመመው ታሞ የዋለበት፣ የወደቁ ከተረሱበት ከትቢያ የሚያነሳ እሱ ሲወድቅ ሲነሳ የዋለበት፣ ሕመምተኞችን የሚፈውስ እሱ ሲያቃስት የዋለበት፣ ከሲኦል የዲያብሎስ ግብር ነፃ የሚያወጣ ሲገረፍ የዋለበት፣ ወልደ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ድኅነት በመስዋዕትነት ሙሽራ የሆነበት የደስታ ቀን፤ አሳዳጅ አሳሪያችን ዲያብሎስ ከነወጥመዱ ድል የተነሳበት ቀን ነው። ከዚህም የተነሳ በቤተክርስቲያን የተለያየ ምስጢራዊ ስያሜዎች ተሰጥቶታል፡፡

የስቅለት ዓርብ ይባላል
የዓለም ሁሉ መድኀኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለ ድኅነት መስዋዕት ሆኖ የዋለበት ዕለት በመሆኑ የስቅለት ዓርብ ተብሏል። (ማቴ 27፡35)

መልካሙ ዓርብ ይባላል
ይህም የሚያስገነዝበን ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት ማንም ሰው ሲያጠፋ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ይደረግ ነበር፡፡ በተለይ በሮማውያንና በፈሪሳውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ነበረ። በዚህ ዕለት ግን ታሪክን የሚቀይር ነገርን የሚገለብጠው አምላክ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል በደሙ ቀድሶ የምህረት ምልክት፣ የሕይወት አርአያ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ፣ የቤተክርስቲያን ጌጥ፣ የገዳማት ዘውድ ስላደረገውና በዕለተ ዓርብ በሞቱ ሕይወትን ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡

13ቱ ሕማማተ መስቀል
1ኛ. ተአስሮ ድኅሪት (ወደኋላ መታሰር)
2ኛ. ተስሕቦ በሐብል (በገመድ መሳብ)
3ኛ. ወዲቅ ውስተ ምድር (በምድር ላይመውደቅ)
4ኛ. ተከይዶ በእግረ አይሁድ (በእግረ አይሁድመረገጥ)
5ኛ. ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ (ከምሶሶ ጋርመላተም)
6ኛ. ተጽፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)
7ኛ. ተቀሰፎ ዘባን (ጀርባን በጅራፍ መገረፍ)
8ኛ. ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዱላ መመታት)
9ኛ. አክሊለ ሦክ (የሾህ አክሊል መድፋት)
10ኛ. ፀዊረ መስቀል (መስቀል መሸከም)
11ኛ. ተቀንዎ በቅንዎት (በችንካር መቸንከር)
12ኛ. ተሰቅሎ በዕፅ (በመስቀል ላይመሰቀል)
13ኛ. ሰሪበ ሐሞት (መራራ ሐሞትንመጠጣት)

† ጌታችን ከ6-9 ሰዓት በመስቀል ላይ ሳለ የተናገራቸው 7ቱ የፍቅር ቃላት
1ኛ.ኤሎሄኤሎሄ ኤልማስላማ ሰበቅታኒ ማቴ.27፤46
2ኛ. እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ፡፡ ሉቃ.23፤43
3ኛ.አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራእሰጣለሁ፡፡ ሉቃ.23፤46
4ኛ.አባት ሆይየሚያደርጉትን አየውቁምና ይቅር በላቸው፤ሉቃ.2334
5ኛ. እናትህ እነኋት፤ እነሆ ልጅሽ፤ዮሐ.19፤26-27
6ኛ. ተጠማሁ፤ ዮሐ.19፤30
7ኛ. ተፈጸመ፤ ዮሐ.19፤30

† ጌታችን በመስቀሉ ከ6-10 ሰዓት በመስቀልላይ ሳለ የተፈጸሙ 7ቱ ተአምራት
1ኛ. ፀሐይ ጨለመች
2ኛ. ጨረቃ ደም ሆነች
3ኛ. ከዋክብት ብርሃናቸውን ነሱ
4ኛ. የቤተመቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተከፈለ
5ኛ. ዐለቶች ተሰነጣጠቁ
6ኛ. መቃብራት ተከፈቱ
7ኛ. የሞቱት ተነሡ፤ ማቴ.27፤45-46

5ቱ ቅንዋተ መስቀል ችንክሮች ሳዶር ፣ አላዶር ፣ ዳናት ፣ አዴራ እና ሮዳስ ይባላሉ።
1. ሳዶር ፦ ማለት ቀኝ እጁ የተቸነከረበት
2. አላዶር፦ ማለት ግራ እጁ የተቸነከረበት
3. ዳናት ፦ ማለት እግሮቹ የተቸነከረበት
4. አዴራ ፦ ማለት ደረቱን የተቸነከረበት
5. ሮዳስ ፦ ማለት ከወገቡ(እብርቱ) አጣብቆ እንዲይዝ የተቸነከረበት
=============================
☞ሞትን ይሽረው ዘንድ የማይሞተው ሞተ መከራን ታገሰ
☞ሁሉን የያዘውን እርሱን ያዙት
☞ሁሉን የሚገዛውን እርሱን የአምላካችንን እጅ አሰሩት
☞ሀጥያትን የሚያስተሰርይ እርሱን ሀጢያት አሉት
☞የማይገረፍ አምላክ እርሱን የሰውን ስጋ በመልበሱ ገረፉት
☞እንደ መብረቅ የሚያንፀባርቀውን ነጭ ልብስ የሚያለብስ አምላክ እርሱን ቀይ ግምጃ አለበሱት።
☞በእሳት በተጋረዱ ዙፋን ላይ የሚቀመጥ እርሱን በመዘባበቻ ወንበር ላይ አስቀመጡት።
☞እንደ ድንኳን ሰማይን የዘረጋ እርሱን በመስቀል ላይ ሰቀሉት
☞የመላእክትን አለቆች በፊቱ በመፍራት የሚቆሙለት እርሱን በጲላጦስ ፊት አቆሙት
☞በህይዋንና በሙታን ላይ የሚፈርድ እርሱን እንደበደለኛ ተፈረደበት
☞አለምን ሁሉ በቅፅበት የፈጠረ እርሱ በስጋው ሞተ በመለኮት ህያው ሆነ
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox