Get Mystery Box with random crypto!

#ጉልባን ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

#ጉልባን
ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡
❖ ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ዅሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡ ባቄላው ይከካል ቅርፊቱ ይላጣል ምሳሌውም የጌታችንን መከራ እና አይሁዳውያን ልብሱን አውልቀውት ነበር የዚያ መታሰቢያ ነው።
❖ በሊቃውንቱ ትምህርት ጉልባን ከስንዴ እና ከባቄላ ይዘጋጃል፤ ባቄላው ይታመሳል፣ ይፈተጋል፣ይከካል ስንዴው ግን አይከካም ፣ አይፈተግም፣ አይታመስምም ይኸውም ምሳሌነቱ ስለእኛ በተዋህዶ ለከበረው አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መታሰቢያ ነው። ማለትም ባቄላው የስጋ ስንዴው ደግሞ የመለኮት ምሳሌ ነው። ምንም እንኳን መለኮት ከሥጋው ያልተለየው አምላክ ቢሆንም ሕማሙ ግን መለኮትን አላገኘውም። የተዋህዶ
መዶሻ የተባለ ቅዱስ ቄርሎስ እንዳስተማረው ነገረ ተዋህዶን በጋለ ብረት እንዳስተማረው ብረን ከእሳቱ ውስጥ ቢጨምሩት ብረቱ እሳቱን ይመስላል እሳቱም የብረቱን ቅርፅ ይይዛል ብረቱን ቢመቱት ይለዝባል የማይጨበጠው እሳትም ከብረት ስለተዋሀደ አንጥረኛው ይመተዋል እሳቱን ግን አያገኘውም።
መለኮት የተዋሀደው ሥጋ መከራን ተቀበለ በሥጋም ሞተ ፤ ለመለኮት ግን ሕማም ድካም ሞት አይስማማውም፤ ይኸውም መለኮት ከሥጋው አንደተዋሀደ በነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ምርኮን ማረከ ነፍሳትን ነፃ አወጣ ገነትም አስገባቸው ፤መለኮተ የተዋሀደው ሥጋ ወደ መቃብር ቢወርድም በሦሥተኛውም ቀን በታላቅ ኃይል በስልጣን ክርስቶስ ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ።
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox