Get Mystery Box with random crypto!

የሰሙነ ሕማማት ሦሥተኛ ቀን ማክሠኞ በዚህ ዕለት አምላካችን ለጥያቄዎች በሙሉ መልስ የሰጠበት | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

የሰሙነ ሕማማት ሦሥተኛ ቀን
ማክሠኞ

በዚህ ዕለት አምላካችን ለጥያቄዎች በሙሉ መልስ የሰጠበት እና በስፋት ያስተማራቸው ትምህርቶች የሚታሰቡበት ዕለት ነው።
፩. የጥያቄ ቀን ትባላለች።
በዚህ ዕለት አምላካችን ስለ ሥልጣኑ በካህናት አለቆችና በሕዝብ አለቆች"በምን ሥልጣንህ እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን የሰጠህ
ማነው?"(ሉቃ፳:፩-፵፩) የሚል ጥያቄ ለፈተና የተጠየቀበት ዕለት በመሆኑ የጥያቄ ቀን ትባላለች፡፡
ጥያቄዎቹ በቁጥር አምስት ናቸው። እነዚህም:-
፩. ሥልጣኑን የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦለታል። (ሉቃ፳:፪) ለክፋት የቀረበ ጥያቄ በመሆኑ ጥያቄውን በጥያቄ መልሶታል።
፪. በወይን አትክልት መስሎ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል። (ሉቃ፳:፱)ይህ ምሳሌ በቀጥታ ከእነርሱ ጋር እንደሚገናኝ ተረድተውም ነበር።
፫. ግብርን የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦለታል። (ሉቃ፳:፳፪) ይህንንም በድንቅ ጥበቡ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ብሎ መልሶላቸዋል።
፬. ትንሣኤ ሙታንን የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦለታል። (ሉቃ፳:፴፫) ከጋብቻ ጋር በተገናኘ ምድራዊ አስተሳሰብ ሰማያዊውን ኑሮ አውርደው ለጠየቁት ለሰዱቃውያን ከሞት በኋላ እንደ መላእክት ያለን ኑሮ የመኖር ዕድል እንዳለው የሰው ልጅ መልሶላቸዋል።
፭. ክርስቶስን የዳዊት ልጅ ለምን ይሉታል የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸዋል።(ሉቃ፳:፵፩)
መልስ ላጡበት ጥያቄ ራሱ በመመለስ እርሱ የዳዊት ጌታ መሆኑን አስተምሯቸዋል።
፪. የትምህርት ቀን ትባላለች
በዚህ ዕለት ደቀ መዛሙርቱን ሰፊ ትምህርትን ስለ መጨረሻው ዘመን ምልክቶች አስተምሯቸዋልና የትምህርት ቀን ተብላ ትጠራለች። (ሉቃ፳:፵፬-፵፯) ያስተማራቸው ትምህርቶች
፩. የአምልኮ መልክ ካላቸውተጠንቀቁ
፪. ታይታን ከሚወዱ ተጠንቀቁ
፫. ለራሳቸው ክብርን ከሚሰጡ ተጠንቀቁ
፬. የባልቴቶችን ገንዘብ ከሚበሉ ተጠንቀቁ
፭. በምክንያት ጸሎት ከሚያረዝሙ ተጠንቀቁ
ሌላው በግብረ ሕማማት ካህናት በዚህች ዕለት ስለሚያከናውኗቸው ስራዎች እንዲህ ተብሎ ተገልጿል:-"ከዚህ በኋላ በከበረች ቤተክርስቲያን ማክሰኞ ከሌሊቱ መጀመሪያው ሰዓት ካህናት ይሰብሰቡ። ተዘከሮ እግዚኦ የሚለውን የዳዊት መዝሙር ወአሰሰልኩ ዕለተ እስከሚለው ድረስ ጸልዩ። ውዳሴ ማርያምም የቀዳሚትን ይድገሙ።" ግብረ ሕማማት (ገጽ፪፻፴፪)
የመዝሙረ ዳዊት ምንባባት
በ፩ ሰዓት (መዝ፴፬:፬-፭)
በ፫ ሰዓት (መዝ፻፲፰:፻፶፬)
በ፮ ሰዓት (መዝ፲፯:፲፯)
በ፱ ሰዓት (መዝ፳፬:፩)
በ፲፩ ሰዓት (መዝ፵፬:፮)

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox