Get Mystery Box with random crypto!

ሰሙነ ሕማማት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዕለተ ትንሣኤ በፊት ያለውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በማለ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ሰሙነ ሕማማት

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዕለተ ትንሣኤ በፊት ያለውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በማለት ታከብረዋለች። "ሕማማት" የሚለው ቃል "ሐመ" ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን የዚህ ስያሜ መነሻም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መከራው፣ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት ከአዳም እስከ ክርስቶስ የነበረው የዓመተ ፍዳ የዓመተ ኩነኔ ወቅትም የሚታሰብበት ስለሆነ "ሰሙነ ሕማማት" ተብሏል።

በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ ሕማማትን መቀበሉ ስለምን ነው ቢሉ፡-
☞ፍቅሩን ለመግለጽ፡- ለፍጥረቱ ይልቁንም ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅሩን ይገልጽ ዘንድ(ዮሐ ፫÷፲፮) ምንም በደል ሳይኖርበት ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ(ዮሐ ፲፭÷፲፫)
☞የኃጢአትን ፍዳ ከባድነት ለማሳየት፡- እርሱ ጻድቅና ንጹህ ሆኖ ሳለ ሰውን ወዶ ይህን ያህል መከራ ከተቀበለ ሰው ኃጢአት በመሥራት ቢመላለስ የኃጢአትን ውጤት ከባድነት ያስተምረናል፡፡ ራሱ ጌታችንም ከጲላጦስ ግቢ እስከ ቀራንዮ አደባባይ መስቀል ተሸክሞ ሲንገላታ ላለቀሱለት የኢየሩሳሌም እናቶች <<በእርጥብ እንጨት የሚያደርጉ ከሆነ በደረቀውስ እንዴት ይሆን>> በማለት ገልጾለታል፡፡ (ሉቃ ፳፫÷፳፪)
☞ቤዛ ለመሆን፡- በኦሪት ዘመን ሰዎች ለሠሩት ኃጢአት ኃጢአታቸውን ለማስተሰርይ ነውር የሌለበትን በግ ቤዛ እንዲሆናቸው መስዋዕት ያቀርቡ ነበር ይህ ግን ከአዳም የተሰወረውን ኃጢአት ማስቀረት ስላልቻሉ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሁኖ መጣ <<እነሆ የእግዚአብሔር በግ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ>>(ዮሐ ፪÷፳፮)
☞እርግማናችንን ለማስቀረት፡- <<በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፏልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን>>(ገላ ፫÷፲፫) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው እርግማናችንን ተሸክሞ ሕማማትን መቀበሉ የቀድሞው ኃጢአት ምንም ያህል ከባድ ቢሆን በታላቅ መስዋዕትነት እንዳስቀረልን ሊያስተምረን ነው፡፡ (ዘዳ ፳፩÷፳፫)
☞የድኅነታችንን ክቡርነት /ውድነት/ ሊያስረዳን ፡- ድኅነታችንን የእግዚአብሔር ልጅ ደሙን እስኪያፈስለት ድረስ እጅግ ውድ መሆኑን ሊያስተምረን፡፡ (ራዕ ፭÷፱)

@Ethiopian_Orthodox

ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት :
-ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም
-በመስቀል መባረክ፣ ኑዛዜ መስጠትና መቀበል፣ እግዚአብሔር ይፍታህ ማለት የለም
- ስብሐተ ነግህ አይደረስም
- ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም
- ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም
- ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም
ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሳዕና ይከናወናሉ፡፡

@Ethiopian_Orthodox

የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች
፩. አለመሳሳም ፡- በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምን የትክሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማግሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ እንሰቀለው ፤እንግለው ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ በዘመነ ፍዳ ወቅት ሠላምና ፍቅር አለመኖሩን የሚገልፅልን በመሆኑ ያንን ለማስታወስ ስላምታ አንለዋወጥም፡፡
፪. ሕፅበተ እግር፡- ጌታ በፍጹም ትህትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ህይወት ማሕተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው ጸሎተ ሐሙስ ሕፅበተ እግር ጌታችን በዚህ እለተ እናንተ ለወንድማችሁ እንዲሁ አድርጎ ለማለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡
፫. ጉልባን እና ቄጠማ ፡- ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጀና የጸሎት ሐመስ እለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብጽ ተሰደው በሚነጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካው ሊጥ እያጋገሩ ቂጣ መብላት ንፎሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓል ይታሰባል፡፡
-ቄጠማ (ቀጤማ)፡- በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱን ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ አዋዲ/ እየመቱ "ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ" የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠ እና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመኑም ለቤተ ክርስቲን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስተውስ ነው፡፡ በዚህ እለት ልብስ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲቆናትን ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲቃጭሉ መታየታቸው እለተ ትንሳኤውን ለምዕመናን ትልቅ ብስራት ነው።
፬. በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዐርብ ስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሰሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱን በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጠባው የሚደረግለት ሰው በህማማቱ ወቅት የፈጸመው በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እያለ እንዲል ያደርጋል፡፡
፭. አክፍሎት፡- በሰሙነ ሕማማት እለተ ዐርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ በዓል/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ከዓርብ እስከ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ማክፈል የብዙዎች ነው፡፡ አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታቸን ያዕቆብ እና ዩሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox