Get Mystery Box with random crypto!

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው የማዳን ሥራ ክፉዎች | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ

ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው የማዳን ሥራ ክፉዎች አይሁድ ከምሽቱ 3:00 ጌቴሴማኒ ውስጥ ያዙት::

¤ሙሉውን ሌሊት ከቀያፋ ወደ ሐና: ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት: አስረው ሲደበድቡት አድረዋል::

ዝም ቢላቸው ዓይኑን ሸፍነው በጥፊ መቱት::
¤ምራቃቸውን ተፉበት:: ዘበቱበት::
¤ራሱንም በዘንግ መቱት::
¤እርሱ ግን ሁሉን ታገሰ::
¤በጧት ከገዢው ዘንድ ሞት እንዲፈረድበት አቀረቡት::

በሠለስት (3:00 ላይ) አካሉ እስኪያልቅ እየተዘባበቱ 6,666 ገረፉት::

ሊቶስጥሮስ አደባባይ ላይ እርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት:: 6:00 ላይ በረዣዥም ብረቶች 5 ቦታ ላይ ቸንክረው ሰቀሉት::

7 ታላላቅ ተአምራት በምድርና በሰማይ ታዩ:: ዓለም በጨለማ ሳለች ጌታ በመስቀል ላይ 7 ቃላትን
ተናገረ:: ከቀኑ 9:00 አካባቢ በባሕርይ ስልጣኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ::

በዚያች ሰዓትም ወደ ሲዖል ወርዶ የታሠሩትን ሁሉ ፈታ::

11:00 ላይ ደጋጉ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር ቀበሩት:: በዚአች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተቃጠለ:: ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ለቅሶን አለቀሰ:: ቅዱሳት አንስት በዋይታ ዋሉ::

ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለው መጋቢት 27 ቀን ቢሆንም በዓሉ ወደ ጥቅምት እንዲመጣ ያደረጉት አበው ሊቃውንት ናቸው:: ምክንያቱም ብዙ ጊዜ መጋቢት 27 የሚውለው ዓቢይ ጾም ውስጥ በመሆኑና የንግሥ በዓላት በዓቢይ ጾም ስለማይፈቀዱ ነው::

ምንም እንኩዋ በቅርብ ጊዜ በዓቢይ ጾም የሚያነግሡ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም አባቶቻችን ግን እንዲህ ያለውን ሥርዓት አላቆዩልንም:: ከበሮና የቸብቸቦ ዝማሬም በወቅቱ የተፈቀደ አይደለም::

+በዚህም ምክንያት የበዓለ ስቅለት ንግሡ ወደ ጥቅምት 27 ሲመጣ: የመጋቢት 5 ገብረ መንፈስ ቅዱስ ንግሥ ወደ ጥቅምት 5: የመጋቢት 10 መስቀል ወደ መስከረም 17 መጥቶ እንዲከበር ሆኗል::

አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ ይማረን ለሀገራችን ሰላሙን ይላክልን፤ አሜን!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox