Get Mystery Box with random crypto!

+++ ‹‹በእግዚአብሔር ፈንታ›› +++ የአእምሮ ሕመም ሕክምና ይሰጥባቸው ከነበሩ ማዕከላት በአን | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

+++ ‹‹በእግዚአብሔር ፈንታ›› +++

የአእምሮ ሕመም ሕክምና ይሰጥባቸው ከነበሩ ማዕከላት በአንዱ እንዲህ ሆነ፡፡ ነርሷ ሕመምተኛውን ‹‹አንተ ማን ነህ?›› ስትል ትጠይቀዋለች፡፡ እርሱም ‹‹ናፖሌዎን›› ነኝ ብሎ ይመልሳል፡፡ ‹‹ናፖሌዎን መሆንህን ማን ነገረህ?›› ብትለው ‹‹እግዚአብሔር ነዋ›› ሲል ፈርጠም ብሎ መለሰ፡፡ ይህን ጊዜ ከአጠገባቸው ሆኖ ምልልሱን ይሰማ የነበረ ሌላ ታካሚ ድንገት ጣልቃ ገብቶ ‹‹ኸረ እኔ አልነገርኩት›› አለ፡፡

  ይህን ታሪክ ስትሰማ ፈገግ አላልህም? ‹ሰው ራሱን ‹‹እንደ እግዚአብሔር›› አድርጎ የሚቆጥረው አእምሮውን ሲታመም ብቻ ነው› ብለህስ አላሰብህም፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ ጤነኛ አእምሮ እንዳለን የምናስብ ብዙዎቻችን ኑሯችን እና እንቅስቃሴያችንን ብንፈትሽ ነገረ ሥራችን ሁሉ ‹‹በአምላክ ፋንታ›› ነው፡፡ አፍ አውጥተን ‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ›› አንበል እንጂ እንዲህ ከማለት የማይተናነስ ሥራ ግን እንሠራለን፡፡

  ፍርድ የእግዚአብሔር ነው፡፡ እኛ ግን ወንድሞቻችን ላይ በመጨከን ስንት ጊዜ በክርስቶስ የፍርዱ ዙፋን ላይ ተቀመጥን፡፡ የሰውን ድካም ሳንረዳ ፈጥነን በመፍረድ ስንት ጊዜ ራሳችንን በእግዚአብሔር ቦታ አስገባን? እስኪ ዮሴፍን እናስበው፡፡ ወደ ግብጽ ባሪያ አድርገው በግፍ የሸጡት ወንድሞቹ ከአባታቸው ሞት በኋላ እርሱ ወደ ተሾመበት ግብጽ መምጣት በፈለጉ ጊዜ፣ የክፋታችንን ብድራት ያስከፍለናል ብለው ስለፈሩ ‹‹በደላችንን ተውልን›› ሲሉ መልእክተኛ ልከውበት ነበር፡፡ የዋሁ ዮሴፍም ይህንን ሲሰማ እያለቀሰ እንዲህ አላቸው ‹‹አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን?››፤ አይደለም ሳታውቀው ዐውቀኸው እንኳን በበደለህ ወገንህ ላይ ለመፍረድ ልብህ በከጀለህ ጊዜ ለራስህ የዮሴፍን ጥያቄ ጠይቀው፡፡ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን?›› (ዘፍ 50፡19)

ራሱን መምራት ያልቻለ ደካማ ሌላው ላይ በፍርድ ለመሠልጠን ሲሞክር ከማየት በላይ እግዚአብሔርን ምን የሚያሳዝን ነገር አለ?

ሁሉን የሚያውቅ እግዚአብሔር ነው፡፡ ነገር ግን የሁሉ ጥበብ መፍለቂያዎች እንደ ሆንን፣ ከእኛ የተሠወረ አንዳች እንደሌለ እያሰብን ‹‹አምላክ አምላክ የምንጫወት›› ጥቂቶች አይደለንም፡፡ የእኛ ጣት ያልገባበት ሁሉ የማይጥመንና ትክክል የማይመስለን፣ እኛ ካልመራን፣ የእኛ ቡራኬ ከሌለበት የምናራክስ፣ ‹‹አላውቅምን›› የማናውቅ፣ ብዙኃኑን እንደ ጨዋ (ምንም የማያውቅ) የምንቆጥር አያሌ ነን፡፡ የሚያሳዝነው ግን ዓለም በአንድ ወይም በጥቂት ሰው ፈቃድ ስላልተገነባች በአንድ ወይም በጥቂቶች ፈቃድ ብቻ ልትመራ አትችልም፡፡ ሁሉን በሁሉ ማድረግ የሚችለው ሁሉን የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

‹‹ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ ዕወቁ›› መዝ 46፡10

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox