Get Mystery Box with random crypto!

ጥቅምት ፲፬ ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ጥቅምት ዐሥራ አራት በዚህችም ቀን ታላቁና የከበረው አባታችን አ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ጥቅምት ፲፬
ጻድቁ አቡነ አረጋዊ


ጥቅምት ዐሥራ አራት በዚህችም ቀን ታላቁና የከበረው አባታችን አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) የተሰወሩበት ነው።

እኚህ አባት ከ፱(9) ቅዱሳን አባቶች አንዱ ሲሆኑ
አባታቸው ይስሐቅ የሮም ንጉስ ነበሩ፡፡ እናታቸው ንግስት እደና ይባሉ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ስማቸው ዘሚካኤል ነው፡፡ ጥበብ መንፈሳ ሲማሩ አድገው ወደ እስክንድርያ ገዳም ገቡ፡፡ አበምኔቱ አባ ጳኩሚስ በፈቃደ እግዚአብሔር የመጡ መሆናቸውን አውቀው መዓረገ ምንኩስና ሰጥተዋቸዋል፡፡

የንጉሳዊ የቅንጦት ኑሮ ንቀው ትተው ገዳም ገብተው በምንኩስና ተወስነዋል፡፡ አባታችን በተጋድሏቸውም ከአባ እንጦንስ፣ ከአባ ጳውሊ እና ከአባ መቃርስ ቀጥሎ በአራተኛ ማዕረግ አበ መነኮሳት ሆነው ተመርጠዋል።

በገዳመ ዳውናስ ፯ ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ ሮም ተመልሰው ሲያስተምሩ የሀገራችን ኢትዮጵያን ዜና ሰምተው ለመምጣት በ፬፻፹ ዓ.ም ከአባ ፍሬምናጦስ በኋላ መንገድ ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም በክንፉ ተሸክሞ አክሱም አድርሷቸዋል፡፡

ተመልሰውም ሄደው ስለ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መስክረዋል፡፡ ሐዋርያ ሳይላክላት በሃይማኖት በምግባር ጸንታ ትኖራለች ብለው ለሰባቱ ዘመዶቻቸው አበው መነኮሳት ነገሯቸው፡፡ ስምንቱም ጓዛቸውን ጠቅልለው በሮም ነግሶ የነበሩ ይስሐቅን (አባ ገሪማን) ጨምረው ንጉስ አልአሜዳ በነገሰ በአምስተኛ ዓመት ማለትም በ፬፻፹ ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ሆነው መጥተዋል፡፡

አባ አረጋዊ እናታቸው ቅድስት እድናን ደቀ መዝሙራቸውን ማትያስን አስከትለው እግረ መንገዳቸውን እያስተማሩና ድውያንን እየፈወሱ ደብረ ዳሞ ደርሰዋል፡፡

ከእግረ ደብር ሆነው አሁን ይህን ተራራ በምን ልወጣው እችላለሁ እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ በንግግሩ ሐሰት የሌለበት አምላካችን በነቢዩ ዳዊት ላይ አድሮ በመዝሙር ፺/፺፩፥፲፩-፲፮ ላይ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። እንዳለው የታዘዘ ዘንዶ መጥቶ ስደሳ ክንድ በሚያህል ጅራቱ ጠምጥሞ ቅዱስ ሚካኤል ሰይፈ እሳት ይዞ እየጠበቃቸው ከተራራው አናት አድርሷቸዋል፡፡

ወዲያው ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ብለው አመስግነዋል፡፡ ቦታውም ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሏል፡፡ በዚያ ዕለት ግማሽ ህብስት በልተው ጠገቡ፤ ከዚያ በኋላ ግን ምድራዊ ሕብስት አልተመገቡም፡፡ በሰንበተ ክርስታያን ከቅዳሴ በኋላ ሕብስተ ሰማያዊ እያመጡላቸው ይመገቡ ነበር እንጂ፡፡ ኋላም ዜና ጽድቃቸውን ሰምተው ከስድስት ሺህ ያላነሱ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበውላቸዋል፡፡

ዘጠና ዘጠኝ አመት ሲሞላቸው ጌታ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ ምድራዊ መንግስትህን ትተህ ስላገለገልከኝ ህልፈት ሽረት የሌለባት ሰማያዊ መንግስቴን አወርሰሃለሁ ብሎ ቃልኪዳን ሰጣቸው፡፡ በስምህ የተማጸነውን እስከ አስራ አምስት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ አንተም ከሞት ገጽ ትሰወራለህ ብሎ ተስፋቸውን ነገራቸው፡፡ እሳቸው መነኮሳቱን ሰብስበው ከእንግዲህ በሥጋ አታዩኝም ብለው ነግረዋቸው አበምኔት ሾመውላቸው በዚህች ዕለት በዚያው በደብረ ዳሞ ተራራ በስተምስራቅ አቅጣጫ ተሰውረዋል፡፡

በረከታቸው ይድረሰን!

ስንክሳር

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox