Get Mystery Box with random crypto!

ጥቅምት ፭ የታላቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (ገብረ ሕይወት) የዕረፍታቸው መታሰቢያ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ጥቅምት ፭

የታላቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (ገብረ ሕይወት) የዕረፍታቸው መታሰቢያ

ጻድቁ የተወለዱት ግብፅ (ንሒሳ አካባቢ) ሲሆን አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ:: አባታችን ገብረ ሕይወት የጻድቃን አለቃ የቅዱሳን የበላይ ተጋድሏቸውና ድንቅ ተአምራቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ቅዱስ ሰው ናቸው። የጻድቁን ክብር መናገር የሚችል ምን አንደበት ይኖራል? እንደ ምንስ ባለ ብራና ይጻፋል? ዜናቸውንስ ለመስማት የታደለ እንደ ምን ዓይነት ሰው ይሆን?

አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለ፭፻፷፪(562) ዓመታት በዚህች ዓለም ሲኖሩ እህል ያልቀመሱ /ምግባቸው ምስጋና ነውና/ ልብስ ያልለበሱ /ጠጉር አካላቸውን ይሸፍን ነበርና/ ሐዋርያዊ ሆነው ከግብፅ እስከ ኢትዮዽያ ብዙ ነፍሳትን ያዳኑ አባት፤ ሃገራችንን አስምረው አስራት እንድትሆናቸውም ተቀብለው ምድረ ከብድ አካባቢ አርፈዋል።

ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስም ገብረ ሕይወትም ይባላሉ። በ፭፻፷፪ ዓመታት ሕይወታቸው እንደ ሐዋርያት ከምድረ ግብፅ እስከ ኢትዮጵያ ወንጌልን ሰብከዋል። በዚህም በሚሊዮን (አእላፍ) ለሚቆጠሩ ነፍሳት የድኅነት ምክንያት ሆነዋል።

ጻድቁ እንደ ሰማዕታትም ከከሃዲ ሰዎች ብዙ መከራን ተቀብለዋል። እንደ ባሕታውያን ለብዙ መቶ ዓመታት ሰው ሳያዩ ቆይተዋል። ለ'የ'ት የሚለው ግን የጽድቅ ሕይወታቸው ነው፤ ከዕልፍ አዕላፍ አጋንንት ጋር ተዋግተው ድል ማድረግ ችለዋልና።

የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቀር አላቸው። ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለ፻(100) ዓመታት በደብረ ዝቋላ መከራን ተቀብለዋል። ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው።

ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ከ፳፻(2,000) በላይ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት። በ፰(8)ኛው ክ.ዘ አካባቢ የተወለዱት አባታችን ያረፉት በ፲፬(14)ኛው መቶ ክ.ዘ አካባቢ ነው። ፍጥረታትን ሁሉ አዝዘው መጋቢት ፭(5) ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል።

ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ። "ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ: ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ: ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ: ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ: ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ።" እንዲል።

ጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እረፍቱ መጋቢት ፭(5) ቀን ነው ይህ ደግሞ በታላቁ ዓብይ ጾም ወቅት ነው። ፍትሃ ነገስት አንቀጽ ፲፭(15) ላይ በዓብይ ጾም በዓል ማክበር ይከለክላል የሀዘን ወቅት ነውና ከበሮ አይመታም እልልታና ጭብጨባ የለም ፍጹም ሀዘን እንጂ :የመጋቢት ፳፯(27) ስቅለት ጥቅምት ፳፯ ቀን እንደሚከበረው ሁሉ የአባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እረፍታቸው ወደ ጥቅምት ፭ ቀን ተዛውሮ እንዲከበር ተደረገ፡፡

የጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድኤት በረከታቸው በእኛ በምናምን ላይ ይደርብን!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox