Get Mystery Box with random crypto!

መስከረም ፳፱ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ የቅድስት አርሴማ አባቷ ቴዎድሮስ ከሌዋውያንና ከኃያላን ነገ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

መስከረም ፳፱
ሰማዕት ቅድስት አርሴማ

የቅድስት አርሴማ አባቷ ቴዎድሮስ ከሌዋውያንና ከኃያላን ነገሥታት ወገን ሲሆን እናቷ አትኖስያ ደግሞ ከጳጳሳት አለቆች ወገን ናት፡፡ ወላጆቿ በሃይማኖት በምግባር ያጌጡ በበጎ ትሩፋት የተመሰገኑ ደጋግ ቅዱሳን ናቸው፡፡ በጾም፣ በጾሎት፣ በምጽዋትና ዓሥራት በኩራትን በማውጣት በመንፈሳዊ ሥራ ሁሉ እየተጉ ቢኖሩም ነገር ግን እስክ እርጅናቸው ዘመን ድረስ ልጅ ስላልነበራቸው ያዝኑ ነበር፡፡ እናቷ ቅድስት አትኖስያ እንደ ነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና ጠዋት ማታ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በእግዚአብሔር ፊት ታለቅስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የልቧን ፈቃድ ይፈጽምላት ዘንድ ወደደና የቂሣርያውን ሊቀ ጳጳሳት ልድዮስን ስለ እርሷ ይጸልይላት ዘንድ አዘዘው፡፡
ሊቀ ጳጳሳቱም ስለ ቅድስት አትኖስያ ጸለየላት፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የሊቀ ጳጳሳቱንና የቅድስት አትኖስያን ጸሎት ሰምቶ መልኳ እጅግ ያማረችን ሴት ልጅ ቅድስት አርሴማን ሰጣት፡፡ እናቷም እየተንከባከበች አሳድጋት ዕድሜዋ ከፍ ሲል አምላክን በወለደች በእመቤታችን ስም ወደተሠራች ቤተ ክርስቲያን ታገለግል ዘንድ ሰጠቻት፡፡ ቅድስት አርሴማ ወጣት በሆነች ጊዜ ወላጆቿ ባል ያጋቧት ዘንድ ወደዱ ነገር እርሷ ይህንን ፈጽሞ አልወደደችምና ወላጆቿን ‹‹እኔ የሰማያዊው የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ እንጂ ምድራዊ ሙሽራ አይደለሁም›› አለቻቸው፡፡
ቅድስት አርሴማ ከእርሷ በፊትም ሆነ ከእርሷ በኋላ በመልክና በውበት የሚመስላት የለም፡፡ ይህን ዓለም እንደትቢያ በመቁጠርና ፍጹም በመናቅ ጌታችንን ከተከተሉት ቅዱሳት ደናግል አንስት ውስጥ በመልክና በውበት ቅድስት አርሴማን የሚመስል የለም፡፡ አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን በቀር የሚበልጣት ማንም የለም፡፡ እርሷም በምግባር በሃይማኖት ያጌጠች በመንፈሳዊ ተጋድሎ የበረታች በትሩፋት የበለጸገች ናት፡፡ ብሉይን ከሐዲስ አጠናቃ ተማረች፡፡ የአገሮችንም (የሮምያን፣ የጽርዕን፣ የሶርያን፣ የኪልቅያን) ቋንቋዎች ታውቅ ስለነበር ቅዱሳት መጻሕፍትንም ወደ ተለያዩ አገራት ቋንቋዎች ትተረጉማለች፡፡

ቅድስት አርሴማ 15 ዓመት በሆናት ጊዜ ከሃዲውን ዲዮቅልጥያኖስን ሰይጣን አስነሥቶት ነገሠ፡፡ ይኸውም ከሃዲ ንጉሥ ሚስት ያባ ዘንድ በመልኳ ውብ የሆነች ሴት ልጅን ይመርጡለት ዘንድ በሀገሩ ሁሉ እንዲሄዱ ጭፍሮቹን አዘዘ፡፡ ያገኟትንም ውብ የሆነችን ሴት መልኳን ሥለው ያመጡለት ዘንድ ሠዓሊዎችንም አብሮ ላከ፡፡ የተላኩትም ሰዎች ወደ ሮሜ አገር በደረሱ ጊዜ ቅድስት አርሴማ ያለችበትን የደናግል ገዳም አገኙ፡፡ ወደ ገዳሙም ገብተው ቅድስት አርሴማን አይተዋት በመልኳ ማማር እጅግ ተደስተው ‹‹ለንጉሡ ሚስት የምትሆነው ይህች ናት›› ብለው መልኳን በሥዕል ቀርጸው ለንጉሡ ላኩለት፡፡ ንጉሡም ሥዕሏን በተመለከተ ጊዜ ፈጽሞ ተደሰተ፡፡ ስለ ሠርጉ ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ ሕዝቡን ይጠሩአቸው ዘንድ ወደ ነገሥታቱና ወደ መኳንንቱ ሁሉ ላከ፡፡

እሊያ ደናግልም ይህን ነገር በአወቁ ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ ድንግልናቸውንም ይጠብቅ ዘንድ አልቅሰው ወደ እግዚአብሔር ለመኑ። ከዚህም በኋላ ተነሥተው በሥውር ሸሹ የንጉሥ ድርጣድስ ግዛት ወደ ሆነ ወደ አርማንያ ሀገርም ደርሰው በአንድ ቦታ ተቀመጡ ከእርሳቸውም ጋር የተሰደዱ ቁጥራቸው ሰባ አምስት የሆነ ወንዶች፣ ሴቶችም ሠላሳ ዘጠኝ የሆኑ ከእርሳቸው ጋራ አሉ። ምግባቸውን አያገኙም ነበርና በታላቅ ችግር ውስጥ ኖሩ ከእነርሱም መብራት የምትሠራ አንዲት ሴት ነበረች ከእርሷም የእጅ ሥራ ከሚገኘው በየጥቂቱ ይመገባሉ።

ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም የከበረች አርሴማን በፈለጋት ጊዜ አላገኛትም ግን በአርማንያ አገር እንዳለች ስለርሷ ሰማ። ደግሞ ለአርማንያ ንጉሥ ለድርጣድስ ስለርሷ ከዲዮቅልጥያኖስ ሸሽታ እንደ መጣች የአርሴማን ሥራ ነገሩት እርሱም አንዱን የአርማንያ መኰንን ለእኔ ጠብቃት ወደ እኔም ላካት ብሎ አዘዘው።

ደናግሉም ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ ሌላ ቦታ ተሠወሩ ወደ ንጉሥም ወነጀሉአቸው ንጉሡም ቅዱስት አርሴማን በክብር አድርገው ያመጧት ዘንድ አዘዘ እርሷም ወደ እርሱ መምጣትን እምቢ በአለች ጊዜ እየጎተቱ ወስደው ወደርሱ አደረሷት።

የቅድስት አርሴማንም ላህይና ደም ግባቷን በአየ ጊዜ ድንግልናዋን ሊያረክስ ሽቶ እናቷ አጋታን አባብላ እሺ ታሰኝለት ዘንድ አዘዛት አጋታም ወደርሷ ሒዳ ልቧን አስጨከነች እንዲህም አለቻት። ዕወቂ ይህ ርኲስ አረሚ እንዳያረክስሽና ሰማያዊ ሙሽራሽን እንዳትተዪ እርሱም ክብር ይግባውና የእግዚአብሔር ልጅ ሕያው ክርስቶስ ነው።

ንጉሡም ይዞ ወደ እልፍኙ ሊአስገባት ከአደባባይ መካከል ተነሥቶ ድንግል አርሴማን ያዛት። በዚያንም ጊዜ በቅድስት አርሴማ ላይ የእግዚአብሔር ኃይል አደረባትና በምድር ላይ ጣለችው እርሱ ግን በጦርነት እጅግ የጸና አርበኛ ስለ ነበር በታናሽ ሴት ብላቴና ስለተሸነፈ ያን ጊዜ አፈረ። ራሷንም በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጧት ከዚህም በኋላ ደናግሉን ሁሉ ከእናታቸው አጋታ ጋር ይገድሏቸው ዘንድ አዘዘ።

አንዲት የታመመች ድንግል ነበረች በዐልጋዋ ላይም እንደተኛች ወደ ወታደሮች ጮኸች መጥተውም እንደ እኅቶቿ ራሷን ቆረጡ ሁሉም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ እነዚያንም ከሮሜ አገር አብረው የመጡ ወንዶችን ገደሏቸው ቁጥራቸውም ሰባ አምስት ናቸው ሥጋቸውም በተራራ ላይ የተጣለ ሁኖ ቀረ።

ሰማዕታትም ከተገደሉ በኋላ በንጉሡ ላይ ጋኔን ተጫነበት መልኩም ተለውጦ እንደ እርያ ሆነ። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ወደርሱ መጥቶ በላዩ ጸልዮ እስከ አዳነው ድረስ ስለዚህም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ። የቅዱሳን ሰማዕታትንም ሥጋቸውን ከተጣለበት ሰብስበው በአማረ ቦታ አኖሩአቸው ያማረች ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም ተሠራችላቸው። ከእነርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

የእናታችን ቅድስት አርሴማ ምልጃዋ ይጠብቀን!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox