Get Mystery Box with random crypto!

+ቅዱስ ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ 'ለሚፈሩሕ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው' እያሉ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

+ቅዱስ ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ "ለሚፈሩሕ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው" እያሉ መስቀሉን ከርቀት ተመልክተዋል:: (መዝ. 59:4)

+በሐዲስ ኪዳን ግን ምሳሌው ገሃድ ሆኖ: ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰበት: ደሙን አፈሰሰበት: ዓለምንም አዳነበት:: ስለዚህም " መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም:  መሠረተ ቤተ ክርስቲያን" ተብሎ የሚመሰገን ሆኗል::

+ ቅዱስ ያሬድ ሊቁ አክሎ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር: ያድኅነነ እምጸር" ብሎ ጠላትን ማሳፈሪያ መሆኑን ይነግረናል::  ብርሃነ ዓለም  ቅዱስ ዻውሎስም ስለ መስቀሉ አምልቶ አጉልቶ አስተምሯል:: መመኪያችን ነውና:: (1ቆሮ. 1:18, ገላ. 6:14)

+አንዳንዶቹ እኛን 'የተሰቀለውን ትታቹሃል' ይሉናል:: የተሰቀለውማ የጌቶች ጌታ: የነገሥታት ንጉሥ: የአማልክት አምላክ: ሁሉ በእጁ የተያዘ: ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ከኦርቶዶክስ በላይ የሚያመልክ በወዴት አለና::

+ነገር ግን መስቀሉን ንቆ የተሰቀለውን ማክበር አይቻልምና እኛ ለመስቀሉ የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን: እናመሰግነዋለን: እናከብረዋለን: ቤዛ: ጽንዕ: መድኃኒት: ኃይል እያልንም እንጠራዋለን:: አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት ማዕበለ ኃጢአትን: ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል::

+በመስቀሉ ቢመኩ አጋንንትን ድል ነስተዋል:: ጠላትንም አሳፍረዋል:: እኛም በመስቀሉ አምነን ከብረን: ገነን እንኖራለን:: ተጠቅመንበታልና ከራሳችን ሕይወት በላይ ምስክርን አንፈልግም::

+"+ በዓለ_መስቀል +"+

    በሃገራችን ኢትዮጵያ መስቀልን በሚመለከት ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ የደመራ መስቀል በዓል /መስከረም 16ና 17/ እንዲሁም መጋቢት 10 የመስቀለ ኢየሱስ በዓል ተያያዥነት ያላቸውና ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ በኋላ በቀራንዮ አደባባይ ጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ጌታችንን የገነዙት #ዮሴፍና #ኒቆዲሞስ ከቀራንዮ ወደ ጎልጎታ (ጌታችን ተቀብሮባት ወደነበረው መካነ መቃብር) ወስደው አኑረውታል፡፡

   አበው ሐዋርያት ወደየሀገረ ስብከታቸው ሲሄዱ የኢየሩሳሌሙ ጳጳስ ሐዋርያው #ያዕቆብ በኃላፊነት እንዲጠብቀው አድርገዋል፤ ከየአህጉረ ስብከታቸው ሲመለሱም በእግረ መስቀሉ ሥር እየተሰበሰቡ ይጸልዩ ነበር፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያምም ጠዋትና ማታ በመስቀሉ ሥር ትጸልይ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ታሪኩንና ቦታውን በክርስቶስ ደም የተቀደሰውን ክቡር መስቀሉን ለማየት ያመኑትም በረከት ለማግኘት ከየአቅጣጫው ይመጡ ነበር፡፡ በመስቀሉ ተዓምራት ብዙዎች ከተለያዩ ደዌ /በሽታ/ ተፈውሰዋል፡፡ ይህም በጣም ብዙ ሰዎች ክርስቶስን ወደ ማመን ስቧቸዋል፡፡ ይህን ድንቅ ሥራ የተመለከቱ የክርስቶስ ሰቃዮች /ሰቃልያነ ክርስቶስ/ በሁኔታው ባለመደሰታቸው ሕይወት የሆነውን የጌታ መስቀሉን ከጎልጎታ አንስተው ቀብረውት #ለ300 ዓመታት ያህል የከተማው ጉድፍና ጥራጊ እየጣሉበት የተቀበረበት ቦታ ኮረብታ እስኪሆን ድረስ ቆይቷል ‹‹በቀራንዮ መካን ዘደፈኑ አይሁድ፤ መስቀልከ ዕፀ ሕይወት፥ ዕፀ መድኀኒት›› እንዲል፡፡ ሆኖም #በ4ኛው መ/ክ/ዘመን ለክርስቲያኖች ነፃነት የሚያስብና የሚያስከብር ንጉሥ በሮም ተነሣ፡፡ የንጉሡም ስም ቈስጠንጢኖስ ይባል ነበር፡፡ ይህ ንጉሥ ክርስቲያኖችን ይበልጥ እንዲወድ ያደረገው በጠላቱ በማክሴንዲዩስ (መክስምያኖስ) ላይ በዘመተበት ጊዜ ገና በጉዞ ላይ እያለ ‹‹በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀርከ (በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን ድል ታደርጋለህ)›› የሚል በመስቀለኛ ቅርፅ የተጻፈ ጽሑፍ በጠፈር ሰማይ አይቶ በመስቀል ምልክት #ድል በማድረጉ ነው፡፡

     የንጉሥ #ቈስጠንጢኖስ እናት ንግሥት #እሌኒ የመስቀሉ ፍቅር ያደረባት፥ ታሪኩ በውስጧ የሰረጸባት ቅድስት እናት ነበረች ቈስጠንጢኖስም በዘመነ መንግሥቱ በትዕምርተ መስቀል ብዙ የድል ሥራ ስለሠራ ለመስቀሉ ታላቅ አክብሮትና አድናቆት ነበረው፡፡ ንግሥት እሌኒም መስቀሉን ለማግኘት ሰው ብትጠይቅ የሚያውቅ አላገኘችም፡፡ በመጨረሻ ግን የመስቀሉ መውጣት የእግዚአብሔር ፈቃድ በመሆኑ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊና መቃርስ የሚባል ኤጲስ ቆጶስ አገኘች፡፡ ከእነዚህም አረጋዊው ኪራኮስ ዕድሜው የሸመገለና በእስራኤል ባህልና ደንብ ያደገ ነበር፡፡ እሌኒም እሱን ጠይቃ መስቀሉን ለማግኘት እንዲተባበራት ጠየቀችው ሆኖም ሊተባበራት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ረሃብና ጽም ስታበዛበት ግን የረሃብና የጽሙን መጽናት ተመልክቶ ከእነዚህ ከሦስት ተራሮች አንዱ እንደሆነ ነገራት፤ ከሦስቱ ተራራ የትኛው እንደሆነ ለማወቅ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሱባኤ እንድትይዝ ነገራት፤ ሱባኤም ያዘች፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር #መልአኩን ልኮ እንዲህ አላት ‹‹አንቺም ሰውም በከንቱ አትድከሙ እንጨት አሰብስበሽ፥ ደመራ አስደምረሽ፥ በእሣት አያይዘሽ፥ በፍሕሙ ላይ ዕጣን አፍስሽ፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ አቅጣጫውን ተመልክተሽ ጢሱ ያረፈበትን ቦታ አስቆፍሪው›› አላት፡፡ እርሷም መልአኩ እንዳላት እንጨት አሰብስባ #ደመራ አስደመረች ዕጣንም አፈሰሰችበት #ጭሱም ሰማይ ደርሶ ቅድመ ሥላሴ ሰገዶ  ወደ ምድር ሲመለስ ቦታውን አመለከታት ይህም የሆነው #መስከረም_16 ቀን ነው፡፡ እኛ ደመራ ብለን የምናከብረው ይህን አብነት በማድረግ ነው፡፡

+"+ ቅዱስ_አውዶኪስ_ቀሲስ +"+

=>ይህ ቅዱስ ሰው ለቅዱስ መስቀሉ ከነበረው ፍቅር የተነሳ በብዙ ድካም ወደ #ኢየሩሳሌም በእግሩ ተጉዞ ነበር:: ከብዙ መንገደኞች ጋር በጐዳና ላይ ሳሉ ታዲያ አንድ አይሁዳዊ (ሰማርያዊ) ተቀላቀላቸው:: በወሬ በወሬ የት እንደሚሔዱ ሲጠይቃቸው "መካነ መስቀሉን ለመሳለም ወደ #ጐልጐታ ነን" አሉት::

+እሱ ግን ከት ብሎ ስቆ "እንዴት እንጨት ትሳለማላችሁ" በሚል አፌዘባቸው:: የፀሐዩ ሐሩር እጅግ ጠንቶ ነበርና ቅዱስ አውዶኪስ ኃይለ መስቀሉን ሊያሳይ ወደደ:: በመንገድም መርዝነት ያለው ውሃ ነበርና ቅዱሱ ቀርቦ ጸልዮ በመስቀሉ ባረከውና ፈጥኖ ወደ ጣፋጭነት ተቀየረ::

+ምዕመናኑ ደስ ብሏቸው ሲጠጡ ያ አይሁዳዊ 'እጠጣለሁ' ብሎ ቢቀርብ ወደ ነበረው ተመለሰበት:: 'በኮዳ የያዝኩትን እማልጠጣ' ብሎ ቢከፍተው ደግሞ ተልቶ አገኘው:: እጅግ ደንግጦ አለቀሰ:: በጣም ጠማው: ግን ምኑን ይጠጣ!

+አማራጭ ሲያጣ ወደ ቅዱስ አውዶኪስ ሒዶ እግሩ ላይ ወድቆ አለቀሰ:: በመስቀሉ ቢማጸን መራራው ጣፈጠለት:: በዚህ ምክንያትም ወደ ክርስትና ተመልሷል:: ቅዱሱ በመልካም ሽምግልና ሲያርፍ ውሃው የተቀየረበት ቦታ ላይ ቤተ መቅደስ ታንጾ በዚህ ቀን ተቀድሷል::

+"+ ቅድስት ታኦግንስጣ +"+

=>በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረችው ሮማዊቷ እናት መንገድ ላይ ቁማ ወንጌል ስታነብ በንጉሥ ወታደሮች ተማርካ ወደ ሕንድ ተወስዳለች:: በዚያም በመስቀል አማትባ ሙት በማስነሳቷ የሃገሩ ሰው ወደ ክርስትና ከነ ንጉሡ ተመልሰዋል:: እርሷም ገዳም አንጻ: ደናግሉን ሰብስባ በንጽሕና ኑራለች:: በዚህ ቀን ዐርፋ ሲቀብሯት የብርሃን መስቀል መቃብሯ ላይ ተተክሏል::

=>አምላከ ቅዱሳን በኃይለ መስቀሉ: በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን:: ከበረከቱ አሳትፎ በዓሉን የሰላም ያድርግልን::

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox