Get Mystery Box with random crypto!

#ሐምሌ_፯ ሐምሌ ሰባት በዚች ቀን #ሥሉስ_ቅዱስ በአብርሃም ቤት የተገለጡበት ነው፣ ኢትዮጵያዊው | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

#ሐምሌ_፯

ሐምሌ ሰባት በዚች ቀን #ሥሉስ_ቅዱስ በአብርሃም ቤት የተገለጡበት ነው፣ ኢትዮጵያዊው ሊቅ #ቅዱስ_የአባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ ልደቱና ዕረፍቱ ነው።

#ቅድስት_ሥላሴ

ሐምሌ ሰባት በዚች ቀን ሥሉስ ቅዱስ በአብርሃም ቤት የተገለጡበት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም በአካል በግብር ሦስትነት በባሕርይ በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ተገኙ፣ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና፡፡ ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት ‹‹ቅድስት ሥላሴ›› እንላቸዋለን፡፡ የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም፡፡ የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል፣ በቤቱም መጥተው ያድራሉ፡፡ ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም፡፡ አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል፡፡

አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ፡፡ አብርሃም እግራቸውን አጠበ፡፡ በጀርባውም አዘላቸው፡፡ ምሳቸውንም አቀረበላቸው፡፡ እነርሱም እንደሚበሉ ሆኑለት፡፡ በዚያው ዕለትም የይስሃቅን መወለድ አበሠሩት፡፡ አብርሃም ከደግነቱና እንግዳ ከመውደዱ የተነሣ በተመሳቀለ ጎዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ የወጣ የመረደውን፣ የመጣ የሄደውን ሁሉ እየተቀበለ እግዚአብሔርን እያገለገለ የሚኖር ጻድቅ ነበር፡፡ ለዚህም ነው አብርሃም በወይራ ግራር (በመምሬ) ዛፍ ሥር ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር አንድነቱን ሦስትነቱን የገለጠለት፡፡ ዘፍ 18፡1-25፣ ሮሜ 4፡-3፡፡ ቀትር ሰዓት ላይ በድንኳኑ ደጅ ተቀምጦ እንግዳ ሲጠብቅ እግዚአብሔር ታየው ተነጋገረው፡፡ አንገቱን ቀና አድርጎ ዐይኑን አራምዶ በተመለከተ ጊዜ እነሆ ሦስት ሰዎች ከበላዩ ባለ ተራራ ላይ ቆመው አያቸው፣ ወደ እርሱም ሲወርዱ አይቶ ፈጥኖ ሄዶ ከሰግደላቸው በኋላ ‹‹አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ…›› እያለ በትሕትና በመጋበዝ ወደ ድንኳኑ አስገብቶ በሚገባ ጋበዛቸው፡፡ ‹‹በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ›› ብሎ አንድነታቸውን፣ ‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ›› ብሎ የሦስትነታቸውን ምስጢር ገልጾአል፡፡

ያች ሥላሴ የገቡባት የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡፡ ሥላሴ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደገቡ ሁሉ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምም አብ ለአጽንዖ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋዋን ለመዋሐድ የማደራቸው ምሳሌ በመሆኑ አማናዊቷ የሥላሴ ማደሪያ የአብርሃም ድንኳን እመቤታችን ናት፡፡ ሉቃ 1፡35፡፡

እግዚአብሔርም አብርሃምን የዛሬ ዓመት ልጅ እንደሚወልድ ነግሮት በዓመቱ ይስሐቅን ወልዷል፡፡ ሁለቱ ሰዎች ከአብርሃም ድንኳን ወጥተው ወደ ሰዶም ወደ ገሞራ ሄዱ፣ አብርሃምም ይሸኛቸው ዘንድ አብሯቸው ሄደ፡፡ የሄዱትም ሁለቱ ሰዎች አብና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዱ ወልድ በአብርሃም ቤት ቀርቷል ይኸውም ከቤተ አብርሃም ሰው እንደሚሆን ለማጠየቅ ነው፡፡ አብርሃምም ተመልሶ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ፡፡ እግዚአብሔርም የሚሠራውን ሁሉ ከአብርሃም አይሠውርም ነበርና የሰዶምን የገሞራን ጥፋት ነገረው፡፡ አብርሃምም ይቅር እንዲላቸው አብዝቶ ለመነላቸው፡፡ ሥሉስ ቅዱስን የአብርሃሙ ሥላሴን በምግባር በሃይማኖት ሆነን እናገለግል ዘንድ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን!

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ

በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ልደቱና ዕረፍቱ ነው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ዘትግራይ እናቱ አምኃ ጽዮን ዘወለቃ ይባላሉ፡፡ ስለሆነም ሀገሩ ትግራይና ወሎ ቦረና ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ በመባል የሚታወቀው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በድርሰቱ ከቅዱስ ያሬድ ቀጥሎ ስሙ የሚነሣ ታላቅ መመኪያችን የሆነ ጻድቅ አባታችን ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከመናኝ ጻድቅነቱ በተጨማሪ በመላእክትም ዘንድ የተመሰከረለት ታላቅ ፈላስፋና ደራሲም ነው፡፡ በድርሰቱ ላይ ስለ ሰማይ፣ ስለ መብረቅ፣ ስለ ደመና፣ ስለ ዝናብ አፈጣጠር፣ ስለ አራቱ ዓለማትና ስለ ሰባቱ ሰማያት… በእነዚህና በመሳሰሉት በመንፈሳዊው በሚገባና እጅግ በሚያስደንቅ መንገድ ተፈላስፎባቸዋል፡፡

ጻድቁ ድርሰቶቹን እርሱ ካለበት ወደ ሌላ ቦታ ለመላክ ንፋስ ይታዘዝለት ነበር፡፡ ስለ ጾምና ስለ በዓላት የደረሰውን ድርሰቱን ለሸዋው ንጉሥ ደብዳቤ ጽፎ በነፋስ ጭኖ ልኮለታል፡፡ አስደናቂ ገደሙ ወሎ ቦረና ውስጥ ይገኛል፡፡ ጋስጫ በድሮ ስሟ ደብረ ባሕርይ ትባላለች፡፡ በአጠገቡም ራሱ አባ ጊዮርጊስ የፈለፈላቸው ብዙ ዋሻዎች አሉ፡፡ ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር ለመገናኘት እንዲያመቻቸው ብለው የሠሩት ድልድይ ‹‹የእግዜር ድልድይ›› ይባላል፡፡ በእግር 5 ሰዓት የሚያስኬድ መንገድ ነው፡፡ የአባ ጊዮርጊስ ጋሥጫ ገዳም የአውሬ ሰጋጅና ባሕታዊ ያለበት አስደናቂ ገዳም ነው፡፡ በየዓመቱ የስቅለት ዕለት ቁመቱ 60 ክንድ የሆነ ዘንዶ ከመቅደሱ ወጥቶ ግብረ ሕመማት ከሚነበብበት ከአትሮንሱ ሥር ሆኖ ተጠምጥሞ እራሱን ቀና አድርጎ ሲሰግድ ውሎ ካህኑ ሲያሰናብት ማታ ተመልሶ ወደ መቅደሱ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ የተሰኘውን የዚህን ድንቅ አባታችንን ዜና ሕየወቱን በደንብ መመልከቱ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡

የተወለደው በ1357 ዓ.ም በወሎ ክፍለ ሀገር በቦረና ወረዳ ሰግላ በተሰኘች ቦታ ነው፡፡ የተወለደው በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት ነው፡፡ ወላጆቹ አስቀድሞ ልጅ አልነበራቸውምና በስለት ነው ያገኙት፡፡ አባ ጊዮርጊስ በመጀመርያ እናቱ ፈሪሐ እግዚአብሔርን እያስተማረች በጥበብና በዕውቀት አሳደገችው፡፡ ቀጥሎም የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማረው ከአባቱ ነበር፡፡ ሊቅ የነበረው አባቱ ካስተማረው በኋላ በ1341 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡትና እስከ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ጳጳስ የነበሩት ከአቡነ ሰላማ መተርጕም ዘንድ ወስዶ ዲቁና አሹሞታል፡፡

ዲቁና ከተቀበለ በኋላ ለትምህርት ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ወሰደው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች ‹‹ይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?›› ይሉት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ ‹‹ልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረው›› ብሎ መለሰው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግን ‹‹አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ እዚያው ገዳሙን ያገልግል›› ብሎ እንደ ገና ወደ ሐይቅ ላከው፡፡ አባ ጊየርጊስ ከቀለም ትምህርቱ ይልቅ በሥራ እየደከመ የገዳሙን አባቶች ይረዳ ጀመር፡፡ በገዳሙ እንጨት ይሰብር ውኃ ይቀዳ ይልቁንም ደግሞ አብዝቶ እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ እህል ይፈጭበት የነበረውን የድንጋይ ወፍጮና ንፍሮ ይቀቅልበት የነበረው የድንጋይ ትልቅ ማሰሮ አሁንም ድረስ በሐይቅ ገዳም በክብር ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ ጊዮርጊስ ግን ትምህርቱን ለመረዳት የዘገየ ሆነ፣የእግዚአብሔር ቃልም አልገባውም ነበር፡፡ ይህም ስለ ኃጢአቱ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ሥራና ጌትነቱ በእርሱ ላይ ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ጸጋ ያለመ