Get Mystery Box with random crypto!

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በከንቲባዋ ንግግር ዙሪያ የሰጡት አስተያየት ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን 2 | 💚💛❤️ ዮቶራዊያን💚💛❤️

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በከንቲባዋ ንግግር ዙሪያ የሰጡት አስተያየት

ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ ባሳለፍነው ማክሰኞ መጋቢት 5/2015 ለከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት "ከአንዳንድ ክልሎች የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት መንግስትን በመጣል በኃይል ስልጣን ለመቆጣጠር ያለመ ነው" ማለታቸውን ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ላይ ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡

እናት ፓርቲ የከንቲባዋን ንግግር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እና ግጭት ሊያነሳሳ የሚችል ነው ብሎታል፡፡

“የሚያጠፋ አካል ካለ ኹሌም በሕግ መጠየቅ አለበት።” ያለው ፓርቲው፣ ከዚህ ባለፈ ግን ሰበብ እየፈለጉ የዜጎችን የመንቀሳቀስ ተፈጥሯዊ መብት መጣስ አይገባም ሲል ገልጿል፡፡

እንዲህ አይነት ስህተት የሚፈጽሙ አመራሮች ይስተካከላሉ የሚል ተስፋ ነበር ነገር ግን፣ ስህተቶች እየተደጋገሙ በአዲስ አበባ ዙሪያም በርካታ ቤቶች እየፈረሱ ብዙዎች ተፈናቅለዋል፣ ይህም ቆይቶ ለከተማዋና ለአገር ከፍተኛ አደጋ ያመጣል ነው ያለው፡፡

የእናት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ያየህ አስማረ፣ “መንግሥት ያለው አራት ኪሎ ብቻ አይደለም።” ሲሉ ገልጸው፣ የመንግሥት መዋቅር እስከ ቀበሌ ድረስ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተዘረጋ በመሆኑ መንግሥትን በኃይል የመጣል ፍላጎት ያለው አካል አዲስ አበባ አይመጣም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

አክለውም፣ ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት የሚያሳየው በክልሎች ያለውን አለመረጋጋት እና የሥራ እድል አለመኖር ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም ዛሬ አንድን አካል ለማጥቃት የተደረገ እንቅስቃሴ ነገ ኹሉንም ዜጋ የሚያጠቃ በመሆኑ ማንኛውም አካል ሊታገለው የሚገባ ሀሳብ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር ተክሌ ቦረና፣ “ከንቲባዋ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ ግለሰብ ስለሆኑ ንግግራቸው እንደ ተራ የሚታይ አይደለም፣ “ወደ አዲስ አበባ መንግሥትን ለመጣል የሚገባ አካል አለ” ከተባለ እንዴትና በምን መልኩ የሚለው በግልጽ ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ይህ እስካልሆነ ድረስ ግን የከንቲባዋ ንግግር በእውነት ላይ ያልተመሰረተ ተራ ሀሜት ነው በማለት አክለዋል፡፡

የአገሪቱ ሕዝብ ወደ አዲስ አበባ በብዛት እንዲጓዝ የሚያስገድዱት በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ሌሎች ክልሎች የመዲናዋን ያህል መልማት አለመቻላቸው ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያለቪዛ ነጻ የሰዎች እንቅስቃሴ እንዲኖር ጥረት እያደረገች ባለችበት ወቅት ከንቲባዋ ይህን መናገራቸው፣ ዜጎች በአገራቸው ያላቸውን የመንቀሳቀስ መብት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን ያሳያል ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የከንቲባዋ ንግግር ከአንድ ትልቅ ኃላፊነት ላይ ከተቀመጠ የመንግሥት አመራር የማይጠበቅ፣ ጥሩ እና ሚዛናዊ ያልሆነ፣ በእውነት ላይ ያልተመሰረተ ነው ሲል ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ከንቲባዋ ለምክር ቤቱ ያደረጉት ይህ ንግግር አደገኛ ከፋፋይ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ መሆኑን ገልጾ፣ አገረ መንግሥቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና በማናቸውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ዓለም አቀፍ የወንጀል ጥሪ ነው ብሎታል፡፡

ፓርቲው አክሎም “ዓለም አቀፍ ከተማን በከንቲባነት እመራለሁ ከሚል የመንግሥት ባለስልጣን እንዲህ ዓይነት አደገኛ ቅስቀሳ የማይጠበቅ ነው።” ካለ በኋላ፣ መንግሥት ይኼንን አደገኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ያደረጉትን ግለሰብ ከስልጣን እንዲያነሳና ለፍርድ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርቧል፡፡

አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) እና የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ  በከንቲባዋ ንግግር ላይ ሀሳብ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በሳሙኤል ታዴ
----------------------------