Get Mystery Box with random crypto!

በቁጫ እና በዛይሴ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ጥሰት እዲቆም ተጠየቀ ሐሙስ ጥር 25 ቀን | 💚💛❤️ ዮቶራዊያን💚💛❤️

በቁጫ እና በዛይሴ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ጥሰት እዲቆም ተጠየቀ

ሐሙስ ጥር 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በቁጫ እና በዛይሴ አካባቢዎች ምርጫ 2013 ውጤትን መነሻ በማድረግ "ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲን መርጣችኋል" በሚል በሁለቱም ምርጫ ክልሎች ሕዝብ ላይ የአስተዳደር በደል እንዲሁም የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እየደረሱ ነው ሲሉ በኢፌድሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ክልል ም/ቤት የቁጫ ምርጫ ክልል ሕዝብ እና የዛይሴ ምርጫ ክልል ተወካዮች አስታወቁ።

ተወካዮቹ ወቅታዊ የአካባቢያቸውን ሁኔታ አስመልክተው ትናንት ጥር 24 ቀን 2015 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በኹለቱ ምርጫ ክልሎች በሚገኙ ሕዝቦች ላይ እየተፈፀመ ያለው ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት እንዲቆም መንግሥት የሕግ የበላይነትን ያስከብር ሲሉ ጠይቀዋል።

መግለጫውን የሰጡት ረ/ኘሮፌሰር ገነነ ገደቡ ከቁጫ ምርጫ ክልል፣ አብርሃም አሞሼ ከዛይሴ ምርጫ ክልል እንዲሁም የመቶአለቃ ማሴቦ ማዳልቾ እና አማኒያስ ጉሽና ሲሆኑ፤ በመግለጫቸውም በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል የቁጫ እና የዛይሴ ሕዝብ ያለፈውን የምርጫ ውጤት ተከትሎ በመንግሥት መዋቅር የታገዘ ጥቃትና ለልዩ ልዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መጋለጡን ተናግረዋል።

በዚህም በአካባቢዎቹ ሰዎችን ያለምክንያት ድብደባ፣ ማሰር፣ ማሳደድ፣ ማዋከብ፣ ንብረት መቀማት፣ ከሥራ ማፈናቀልና ማሳደድ ከመድረሱም በላይ ምክንያታዊ ያልሆኑ የገንዘብ ቅጣቶችን በሕዝቡ ላይ በመጣል በኢኮኖሚ የማዳከም ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት የአካባቢዎቹ ማህበረሰብ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት እንደተደቀነበት ተወካዮቹ አብራርተዋል።

በተጨማሪም፤ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎችን አቅፎ አዲስ ክልል ለመመስረት ሰሞኑን ሊካሄድ የታቀደው ሕዝበ ውሣኔ ላይ እንዳይሳተፉ በርካታ ሰዎች የመራጭነት ካርድ መከልከላቸውን የገለጹት ተወካዮቹ፤ ለምርጫው አማራጭ እየቀረበ አለመሆኑን እና ገለልተኛ ምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ታዛቢዎች በሌሉበት ሁኔታ የሚካሄድ መሆኑን በመጥቀስ ሒደቱ አግባብ አለመሆኑን አስረድተዋል።

ከቁጫ ምርጫ ክልል የህዝብ ተወካዩ ረ/ኘሮፌሰር ገነነ በመግለጫው፤ አብዛኛው የቁጫ ሕዝብ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲን መርጠሃል ተብሎ እንዲፈናቀል፣ እንዲሰደድና እንዲታሰር ተደርጓል ያሉ ሲሆን፤ ጥቃቱ በአዲስአበባ የሚገኙ የአካባቢው ተወላጃች ላይ ጭምር ያነጣጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የዛይሴ ሕዝብ ተወካይ የሆኑት አብረሃም በበኩላቸው፤ በጋሞ ዞን እና በአርባምንጭ ዙርያ ወረዳ የገዥው ፓሪቲ ባለስልጣናት በሚያደርጉት ክልከላና በሚያደርሱት እንግልት ምክንያት፤ ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ተገናኝተው ዉይይት ለማድረጎ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

አክለውም ከ1987 ጀምሮ የዛይሴ ብሔረሰብና ሕዝብ የወረዳ እና የዞን አስተዳደራዊ መዋቅር ይፈቀድልን ጥያቄ በማቅረባቸው ብቻ የአካባቢው ሕዝብ የአገር ሽማግሌ፣ ሕጻናትና ሴቶች ሳይቀር እጅግ አሰቃቂ የጅምላ ድብደባ፣ እስር፣ ማሳደድና ማፈናቀል ወንጀል በአካባቢው የአስተዳደር አካላት ተፈፅሞባቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በጋሞ ዞን ውስጥ የዛይሴ፣ የጊዲቾ እና የጋሞ እና ሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች ባሉበት ሁኔታ ሦስቱንም የማይወክል የዞን ስያሜ መኖሩ የአንድ ብሔረሰብ የበላይ እንዲሆን አድርጓል በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም ሕዝቡ በመረጧቸው ይተዳደሩ ዘንድ በ2015 ሊደረግ የታቀደው የሟሟያ ምርጫ እንዲደረግ የጠየቁ ሲሆን፤ ይህ ባለመሆኑ የዛይሴ ሕዝብ በመረጠው ሳይሆን ባልመረጠውና በማይፈልገው ተወዳድረው በወደቁ ግለሰቦች ያልተገባ እንግልት እየደረሰበት ሊቀጥል እንደማይችል አስረድተዋል።

ተወካዮቹ በመግለጫቸው በቁጫ እና በዛይሴ ሕዝብ ላይ እየደረሰ የሚገኘው የአስተዳደር ፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ በደሎች በአስቸኳይ ይቀረፉ ዘንድ የፌደራል እና የክልሉ መንግሥታት የሕዝባችንን ቅሬታ ይስሙልን ሲሉም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።