Get Mystery Box with random crypto!

መጥላት አልወድም፡፡ ስጠላም ለምወደው ነገር ስል ነው፡፡ የምወዳቸው ነገሮች እንዳይጐዱብኝ ጐጂውን | ስብዕናችን #Humanity

መጥላት አልወድም፡፡ ስጠላም ለምወደው ነገር ስል ነው፡፡ የምወዳቸው ነገሮች እንዳይጐዱብኝ ጐጂውን በጥላቻ ማራቅ አለብኝ፡፡ እውነተኛ መውደድ ከብዙ ቅርፊት የተሰራ ነው፡፡ አንደኛው ቅርፊት በወረት ወይንም በጥላቻ ተቀርፎ ሲወድቅ አዲስ የመውደድ ቆዳ ከስር ብቅ ይላል፡፡

ለሰው ልጅ ያለኝ ጥቅል ውዴታ የዚህ ተምሳሌት ነው፡፡ ብዙ አይነት ስም ያላቸውን ግለሰቦች ወድጄ ጠልቻለሁ፡፡ እንደ ቅርፊቱ፡፡ በሰው ልጅ ስም የሚጠራውን ማንነት ግን ልጠላው አልችልም፤ አልፈልግምም፡፡

የጥበብ ስራን እወዳለሁ፤ ስለ ጥበብ ሰሪው ግን ግድ የለኝም፡፡ የጥበብ ስራውን በመውደዴ የጥበብ ሠሪው ተወዳጅ እንዲሆን ሊያደርግልኝ የቻለ ማንም የለም፡፡...ስሪቱ ከሰሪው በላይ ነው፡፡
ከማውቀው ሰው ይልቅ የማላውቀውን ሰው የበለጠ እወዳለሁኝ፡፡ ሰውየውን ሳላውቀው እኔ ነኝ በምናቤ የቀረጽኩት፤ የተጠበብኩበት፡፡ ሰውዬውን ሳውቀው እኔ የሰራሁት መሆኑ አከተመ፡፡

የተፈጥሮው ሰው፦ ሆዳም ነው፣ ራስ ወዳድ ነው፣ ፈሪ ነው፣ ወይንም ሞኝ ነው፣ ሲያወራ ይጮሃል፣ ሲያላምጥ ይንጣጣል፣ ውሃ ካጣ ይግማማል... ማለቂያ የለውም... ወዘተ ወዘተርፈ፡፡ ከሰው ሰው ከስህተት የስህተት አይነት ይለያያል፡፡ ከጥላቻ በራቀበት እና ወደ መውደድ በቀረበበት መጠን የተሻለ ሰው ይባላል እንጂ ትክክል ግን የለም፡፡ የተሻለ ስህተት ትክክል አይደለም፡፡

የማላውቀውን ሰው እንጂ የማላውቀውን ስራ ግን ወድጄ አላውቅም፡፡ ስራውን ለመውደድ ስራውን ከሰራው ሰው ጋር ሳይሆን ከስራው ብቻ ጋር መተዋወቅ አለብኝ፡፡ መዋደድ በእዳ መልክ ግንኙነት በተቆራኙት መሀል ሊፈጥር ይችላል፡፡

የማይነጠል ቁራኛን መጥላት አያዋጣም፡፡ መውደድ ብቻ ከሆነ አማራጩ መዋደዱ የዕዳ ባህርይ የተላበሰ ይሆናል፡፡ የስጋ ዝምድና ወይንም የስጋ ዝምድናን ለመመስረት ሲባል የሚፈጠር የስሜት ቁርኝት፤ ..መውደድ.. በእዳ ...ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ መውደድ በዕዳ እንጂ መጥላት በዕዳ ግን የለም፡፡

ጥበብን መውደድም እዳ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ በተለይ በሚያስጠላ አመት ውስጥ መውደድን ተሸክሞ መጓዝ ግዴታ ሲሆን፡፡

ሰማዩን አሁንም እወደዋለሁ፡፡ (እርግጥ ካየሁት ወደ አንድ አመት ከመንፈቅ አልፎኛል እንጂ፡፡ ቀና ብዬ ሰማዩን ባየው እንደ ድሮው በክዋክብት አበባ እና በፌንጣ ጩኸት እና በልብ ፀጥታ የተሞላ ሳይሆንልኝ ቢቀር፤ እጠላዋለሁ፡፡ ከምጠላው በድሮ ትዝታዬ ሆኜ መውደዴን ብቀጥል ይሻላል) ለውጥን እወዳለሁ፡፡ ግን የምወደው በምኞት ብቻ እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ በጽንሰ ሐሳብ፣ በቲዎሪ ብቻ፡፡ ቲዎሪው ተግባር ሆኖ ለውጥ ሲመጣ ግን ሆዴን ባር ባር ይለኛል (Bar ፈልጌ ፉት እልበታለሁ)

ድሮ ያደኩት ሰፈር መንገዱ እንዴት እንደነበር ማስታወስ ተስኖኛል፡፡ መለወጡን በተስፋ ወድጃለሁ፡፡ ሲለወጥ ባዶ ሆኖ አስጠልቶኛል፡፡
መውደድ እና መጥላት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ወይ? ብዬ ግር እሰኛለሁ፡፡ ምኞትን መውደድ? ምኞቱ ተወልዶ በእግሩ ሲሄድ ለመጥላት ነው እንዴ? በምኞት ደረጃ የተወደደ ምኞቱ የተሳካ ለት ይጠላል፡፡ በምኞት ደረጃ የተጠላ በስኬት ደረጃ ይወደዳል ማለት ነው...ምን አይነት ዲያሌክቲክስ ነው ጃል? ይኼ ማለት እኮ በምኞት ..መልካም አዲስ አመት.. ያልነው ምርቃት መጥፎ አሮጌ አመት ሆኖ በእርግማን ይሸኘናል ማለት ነው፡፡

ለማንኛውም ግን ጥበብን እወዳለሁ፡፡ መጥላት የምወዳቸው ብዙ ሌላ መውደዶች አሉኝ፡፡ ግን ለጥበብ ይሄ አይሰራም፡፡ ጥበብን ስመኘውም እንደ ተግባሩ እወደዋለሁ፡፡ ጥበብን ከእውነታ ጋር ለማቆራኘት መሞከሩን ነው የምጠላው፡፡
.
ጠዋት በእግሬ እያዘገምኩ ማሰብ እወዳለሁ፡፡ የምጠላው ከብዙ ጉዞ በኋላ የሚሰማኝን ድካም ነው፡፡ ፎቶግራፎችን በሙሉ እወዳለሁ፡፡ ዘመናት ባለፉ ቁጥር ጥበብ ይሆናሉ፡፡ ባዶ ክፍል ውስጥ ከሀሳቤ ጋር መቀመጥ እወዳለሁ፡፡ ሌላ ጭንቅላት ሲያንኮራፋ በማልረበሽበት፡፡ የአሮጌ መጽሐፍትን ሽታ እና ክብደት እወዳለሁ፡፡ ቴሌቪዥን እየተመለከትኩ በቴሌቪዢኑ ውስጥ የራሴን ቴሌቪዥን ከፍቼ መመልከት እወዳለሁ፡፡

ትርጉም ያላገኘሁላቸው መውደድ እና ጥላቻዎችም በብዛት አሉ፡፡ እንዴት ልደረድራቸው፣ ወይንም ላስወግዳቸው እንደምችል ፍቺ ያላገኘሁላቸው ነገሮች፡፡ ትርጉም የዋጋ መለኪያ አንዱ መስፈርት ነው፡፡ የሰዎችን (የሰው ልጆችን) ቆራጥነት፣ ታጋይነት፣ ጠንካራነት፣ ቀዳዳ ፈላጊነት ብዙ አዎንታዊ መገለጫዎቹን እወዳለሁ፡፡ ግን አንዳንዴ ደግሞ ቆራጥ፣ ታጋይ፣ ጠንካራ የሆኑለት ነገርን (አላማን) የተሳሳተ እምነት ሲሆን እጠላለሁ፣የምወደውን ነገር ከምጠላ ግን የጠላሁትን ነገር በአዲስ እይታ ተመልክቼ ብወድ ይሻለኛል፣ ምናልባት መውደድ ከመጥላት ይሻል ይሆናል ፣ወዳጅም ደግሞ ከጠላት፡፡

     "መጥላት የማልወዳቸው"
ከሚል መጣጥፍ የተቀነጨበ።
                      ሌሊሳ ግርማ

              ውብ አዳር
@Ethiohumanity
@Ethiohumanity

@EthiohumanityBot