Get Mystery Box with random crypto!

ቅንነት ከልምምድ፣ ልምምድም ከዕውቀት፣ ዕውቀትም ከጥረት ይገኛል፡፡ ቅንነት ኮሌጅ በመበጠስ፣ ዲግሪ | ስብዕናችን #Humanity

ቅንነት ከልምምድ፣ ልምምድም ከዕውቀት፣ ዕውቀትም ከጥረት ይገኛል፡፡ ቅንነት ኮሌጅ በመበጠስ፣ ዲግሪ በማብዛት እውን የሚሆን አይደለም፡፡ አባቶቻችን ዘመናዊውን ትምህርት ሳይማሩ በቅንነት ተዋደውና ተፋቅረው የሐገራቸውን ጥበብና አንድነት አስጠብቀው ኖረዋል፡፡ የእኛ ዘመን ትውልድ ግን በአውቃለሁ ትርክት ጠፍቶ አባቶቻችን ያቆዩልንን ታሪክና ጥበብ ከመጠቀም ይልቅ ለመለያያት ሴራ እንጎነጉንበታለን፡፡ ቅንነት በየደቂቃውና በየሠዓቱ ሌሎችን በበጎ ዓይን ማየትና ሕመማቸውን የራስ ሕመም አድርጎ በመውሰድና የሌላውን ሠቆቃ በመካፈል የሚገኝ ነው፡፡

ብዙ ቅን ምሁራን አሉ፡፡ እልፍ ቅን ሃይማኖተኞች አሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ኢአማኝ በጎ ሠዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ቅን ሁሉ አዋቂ እንዳልሆነው ሁሉ፤ አዋቂ ሁሉ ቅን አይደለም፡፡ ሃይማኖተኛ ሁሉ መልካም አሳቢና አድራጊ አይደለም፡፡ ኢአማኝ ሁሉ ደግ ነው አይባልም፡፡ አዋቂዎች በሙሉ፣ አማኙም ኢአማኙም ሁሉ ቅን ቢሆኑ ዓለማችን የት በደረሠች ነበር፡፡

ቅንነት በአስተሳሰብ ብቻ የሚገለፅ ሳይሆን በተግባር መሬት ወርዶ የሚታይ ካልሆነ፤ እንዲሁም ቅን አሳቢ ቅን አድራጊ መሆን ካልቻለ ማሠቡ ብቻ ቅን አያስብለውም፡፡ ብዙ ጊዜ በአብዛኞቻችን ላይ የሚታየው ባህሪ ይሄ ይመስለኛል፡፡ በሃሳብ ቅን በተግባር ግን ሌሎች ነን፡፡ ‹‹ጧት ጧት ቅዱስ፤ ማታ ማታ እርኩስ!›› እንዲል ብሒሉ፡፡

ከፈላስፎች አንዱ፡- ‹‹ሥራው መልካም ካልሆነ ጥበቡም መልካም አይደለም፡፡ ጥበበኛው ሠውዬ ቅን ካልሆነ ጥበቡም ቅን ሊሆን አይችልም፡፡ ለክፉም ለበጎም ጥበብ አለና፡፡›› በማለት ተግባሩ ሃሳቡን፣ ምግባሩ ጥበቡን መግለፅ ካልቻለ ጥበበኛ ሁሉ ቅን አይደለም ይለናል፡፡ እውነት ነው ቅንነት በጎነት የሌለው ጥበበኛ ጥበቡ ለክፉ እንጂ ለመልካም አይውልም፡፡

ፈላስፋው ዲዮጋንስ፡- ‹‹ከንጉስ ይልቅ በሃብት እኔ እበልጣለሁ›› ሲል ‹‹አንተ በሃብት ከንጉሱ የበለጥከው በምንድነው?›› ብለው ሲጠይቁት ዲዮጋንስም፡-

‹‹በንጉሱ ዘንድ ካለ ብዙ፤ በእኔ ዘንድ ያለ ጥቂት ይበቃልና ነው›› አለ፡፡ ይህ ፈላስፋ ካንዲት ቀፎ መሣይ ማደሪያ ቤት፣ ከአንድ ውሻ፣ ውሃ ከሚጠጣበት ቅል፣ ከአንድ ምርኩዝ ወይም በትር በስተቀር ሌላ ሃብት አልነበረውም፡፡ ቅሊቱንም እንኳ አንድ ትንሽ ልጅ በእጁ እፍኝ ውሃ ሲጠጣ አይቶ ‹‹ለካስ ቅልም ትርፍ ነገር ኖሯል›› ብሎ ጥሏታል፡፡

ወዳጆች ብዙዎቻችን ትርፍ ስናስብ ዋናውን ነገር ጥለናል፡፡ ፈላስፋው ዲዮጋንስ ትርፉን ጥሎ ዋናውን ነው የያዘው እኛ ግን ዋናውን ጥለን በትርፉ እንባክናለን፡፡

በመጀመሪያ ሠብዓዊ ማንነታችን አሽቀንጥረን ጥለናል፡፡ ታሪካችንን፣ ወግና ባህላችንን ንቀን የፈረንጁን አንጠልጥለናል፡፡ አብሮነታችንን፣ አንድነታችንን በዘመን አመጣሽ ቀሽም የዘረኛ ፖለቲካ አደጋ ላይ አውለነዋል፡፡ ዋናውን ጥለን ትርፉ ላይ እንተራመሳለን፣ እርስበርስ እንበላላለን፡፡ ትርፍ ነገሩ ውስጣዊ ሕይወታችን ላይ የሚጨምረው አንዳች ነገር የለውም፡፡ ልባችንን የሚያሞቅ፣ ሕሊናችንን የሚያጠግብ፣ ሠብዓዊነታችንን የሚያረጋግጥ ቅንነት፣ ፍቅርና አንድነት ብቻ ነው፡፡

ፍቅር ካለ አንድ ቂጣ ለዘጠኝ ሠው ይበቃል እንዲል ብሂሉ ባይኖረን እንኳን ቅን ከሆንን ክፉ ጊዜን ማለፍ እንችላለን፡፡ የሐገራችን ችግር የቅንነት ችግር ነው፡፡ የሐገራችን መከራ የዕውቀት ዕጦትም ብቻ አይደለም፡፡ የአዙሪታችን ጉዳይ የአመለካከትም ኋላቀርነት ነው፡፡ ቅን ከሆንን ግን ዕውቀቱንም፣ ክህሎቱንም፣ ቁሱንም ማግኘት እንችላለን፡፡ ዕውቀት፣ ሐብት፣ ክህሎት፣ ወዘተ ኖሮን ቅንነት፣ ፍቅር፣ በጎነት፣ ሌላውን እንደራስ ማየት የሚያስችል አመለካከትና ሕሊና ከሌለን ሁሉም ከንቱ ነው፡፡

ሕይወት ትርጉም የሚኖረው ቅን ሆኖ በፍቅር ተስማምቶ መኖር ሲቻል ነው፡፡ ተስፋም ሆነ ትዝታው ጣፋጭ የሚሆነው የወደፊቱን ጊዜ በበጎ አስተሳሰብ ዋጅተን ስንጠብቀው ነው፣ ያለፈውን ደግሞ በመልካም ትዝታ መለስ ብለን ስንጎበኘው ነው፡፡ ዛሬ ያልኖርበት ቅንነት ነገ መልካም ትዝታ ይዞ አይመጣም፣ ነገም የተሻለ የቅኖች ቀን አይሆንም፡፡

ለዚህ ነው መቼም ቢሆን ‹‹አሉታዊ አዕምሮ አዎንታዊ ሕይወትን አይሠጠንም›› የሚባለው፣ቅን እንሁን! ፍቅር ይኑረን! በዘረኝነት አስተሳሰብ እርስበርስ አንጠላላ፣ አንገፋፋ! አንድ እንሁን! ኢትዮጵያዊነት ትለምልም!

እሸቱ ብሩ ይትባረክ

ውብ ቅዳሜ
@EthioHumanity
@Ethiohumanity

@EthioHumanitybot