Get Mystery Box with random crypto!

ወዳጄ ሆይ አንዳንድ ጊዜ አጠገብህ ያሉ ሰዎች የሚፈልጉትን በቀላሉ ሲያገኙና በትምህርት ፣ በሥራ | ስብዕናችን #Humanity

ወዳጄ ሆይ

አንዳንድ ጊዜ አጠገብህ ያሉ ሰዎች የሚፈልጉትን በቀላሉ ሲያገኙና በትምህርት ፣ በሥራ በትዳር ... ቶሎ ስኬትን ሲጨብጡ ታያለህ። አንተ ግን አንድ ቦታ ቆመሃል። ወቅቱ የእነርሱ ነውና ከመቅናት ይልቅ ባገኙት ስኬት የደስታቸው ተካፋይ ሁን። ለእነርሱ ያደረገ አምላክ ላንተም እንደሚያደርግልህ እመን።

ይኸውልህ ፤

የማንጎ ዛፍ የቡርቱካን ዛፍን ከርሱ ወቅት ቀድሞ ምርትን ስለሚሰጥ አይጨነቅም። ስኬት፣ በወቅት የሚታጨድ መኸር ነው፣ወቅትህ ሲሆን ምንም ነገር ከመንገድህ ሊቆም አይችልም። የአንበሳ በዝግታ መራመድ ስንፍናን ወይንም ድካምን አያመለክትም፤ ያለመውን አደን በእጁ ለማስገባት እርምጃውን እያሰላ እንጂ። የሰዎች ፈጥነው መራመድ አያውክህ።

የራስህን ኑሮ ኑር!

ፈጣሪህን ታመን። ልብ በል፤ ቤትህን በፍጥነት ሠርተህ መጨረስህ ሳይሆን ንፋስና ጎርፍን መቋቋም የሚችል ጠንካራ አድርገህ መሥራትህ ነው ቁምነገሩ። በሰዎች ደስታ ደስ ይበልህ። የእውቀት ሰውና ጠንካራ ሠራተኛም ሁን! ደግሞ ሁሉንም አታገኝም!አንተ የተሳፈርክበት አውሮፕላን መሬት ሲያርፍ፣ ከዛ መሬት የሚነሣ አውሮፕላን አለ፤ ሌሎች ደግሞ ለመነሳት በሂደት ላይ ይገኛሉ። ሁሉም መዳረሻቸው የተለያየ ነው፤ ምናልባትም ወዳንተ መነሻ ሊሆን ይችላል። አየህ ህይወት እንዲ ናት፤ "ደረስኩ" ብለህ ስታስብ ሌሎች ያንን ሥፍራ "ጥለው" ሲነሱ ታገኛቸዋለህ። አንዳንዶቹ አንተ ወደ ተነሳህበት፣ ሌሎቹም ወደ ሌላ።

በልጅ ማጣት ምክንያት ቀን ማታ የሚያለቅሱ ሰዎች እንዳሉ በልጆቻቸው ምክንያት ቀንና ማታ የሚያለቅሱ ሰዎች አሉ፣ባል ባለማግባታቸው የሚጨነቁ ሰዎች እንደገጠሙኝ ሁሉ በማግባታቸው የሚጨነቁም ሰዎች ገጥመውኛል። በሥራ እጥረት ምክንያት የታመሙ እንዳሉ በሥራ ብዛት ምክንያት የሚታመሙ አሉ። ልጆቻቸው ፈተና ላይ ጥሩ ውጤት እንዲያመጡላቸው የሚጨነቁ እንዳሉ፣ ልጆቻቸው ጥሩ ትምህርት ቤት እንዲገቡላቸው የሚጨነቁ አሉ።

እናም ወዳጄ

ህይወት እንዲህ ነው፤ በቃ! ሁሉንም የኛ ልናደርግ አንችልም!፣ ንፋስን አባሮ እንደመያዝ ነውና። ሁሉንም ነገር የራስህ እንዲሆን ከመድከም ይልቅ ባለህ ነገር ደስተኛ ለመሆን ሞክር። ከአንዱ ምእራፍ ወደ ሌላው ምእራፍ እንደሚያሸጋግርህም ፈጣሪህን ታመን። ሁልጊዜም በአምላክህ ደስ ይበልህ! በእምነትም ኑር!

መልካምነት ለራስ ነውና

ውብ አሁን

@EthioHumanity
@EthioHumanity

የተሰማችሁን አድርሱን @EthioHumanityBot