Get Mystery Box with random crypto!

እናንት ሁላችሁም፣ አንድ ላይ፣ የሕይወት ዛፍ ናችሁ፡፡ እናም ራሳችሁን ከመከፋፈል ተጠበቁ፡፡ ፍሬን | ስብዕናችን #Humanity

እናንት ሁላችሁም፣ አንድ ላይ፣ የሕይወት ዛፍ ናችሁ፡፡ እናም ራሳችሁን ከመከፋፈል ተጠበቁ፡፡ ፍሬን ከፍሬ፣ ቅጠልን ከቅጠል፣ ቅርንጫፍን ከቅርንጫፍ አታስበልጡ፡፡ ግንዱን ከሥሮቹ፣ ዛፉን ከእናት አፈሩ ለይታችሁ አትውደዱ፡፡ ይህ ደግሞ … በዕርግጥም … አንዱን ከሌላኛው አስበልጦ፣ ሲከፋም ለይቶ ስትወድዱ የምታደርጉት ነው፡፡

አዎን … እናንት ሁላችሁም … አንድ ላይ … የሕይወት ዛፍ ናችሁ፡፡

ሥራችሁም የትም ነው፡፡ ቅርንጫፍና ቅጠሎቻችሁም በሁሉም ስፍራ፣ ፍሬዎቻችሁም በሁሉም አፍ ውስጥ ! በዛ ዛፍ ላይ ያለው የትኛውም ፍሬ፣ የትኛውም ቅርንጫፍ ሆነ ቅጠል፣ የትኛውም ሥሮች ይሁን ፍሬ፣ የእናንተው ፍሬ፣ የእናንተው ቅጠልና ቅርንጫፍ፣ የእናንተው ሥር ነው፡፡

ዛፉ ጣፋጭና ባለማራኪ መዓዛ ፍሬ ሲቸራችሁ ብታዩ፣ ጠንካራ እና ፍፁም አረንጓዴ ሆኖ ብታገኙት … ሥሮቹን ወደመገበው የሕይወት ወለላ አስተውሉ፡፡

ፍቅር የሕይወት ወለላ ነው፡፡ ጥላቻ ደግሞ የሞት መግል፡፡ ፍቅር ግን ልክ እንደ ደም ሳይታጎልና ሳይገደብ በሕይወት ሥሮች ውስጥ ሊፈስስ ይገባዋል፡፡ የደም ፍሰት መገደብ በሽታ እንደሚሆነው ጥላቻም እንዲሁ የተገደበ ወይም የታፈነ ፍቅር ነው፡፡ የታፈነ ፍቅር መመረዝ ደግሞ ጠይውንም ተጠይውንም፣ ሁለቱንም ይመርዛል፡፡

በሕይወት ዛፍ ላይ ያለች አንዲት ቢጫ ቅጠል ሌላም ሳትሆን ፍቅር የተነፈገች ቅጠል ነች፡፡ እናም ቢጫዋን ቅጠል አትውቀሷት፡፡ ተገንጥሎ የተዘነጠፈው ቅርንጫፍም ፍቅር የተራበ ቅርንጫፍ ነው፡፡ የተዘነጠፈውን ቅርንጫፍ አትርገሙት፡፡ መራራውም ፍሬ ቢሆን ሌላም ሳይሆን ጥላቻ የመረዘው ነውና አትኮንኑት፡፡ ይልቁንም የሕይወትን ወለላ፣ የፍቅርን በረከት ለጥቂቶች ብቻ አዝንቦ ለብዙዎች የነፈገውን፣ በዚህም ራሱን የካደውን፣ የታወረውን የራሳችሁን ተናዳፊ ልብ ውቀሱ፡፡

በልባችሁ ውስጥ የጥላቻ ዘር እስካለ ድረስ የፍቅርን ሐሴት አታውቋትም፡፡ የሕይወት ወለላን ለሁሉም መግባችሁ ለአንዲት ቅንጣት ነፍሳት ብትነፍጉ ያቺ የተነፈገችዋ ሕይወታችሁን ታመርረዋለች፡፡ የቱንም ወይንም ማንንም ስትወዱ እንደ እውነቱ ከሆነ የምትወዱት ራሳችሁን ነው፡፡ ስትጠሉም እንዲሁ ነው … የቱንም ወይንም ማንንም ብትጠሉ እንደ እውነቱ የምትጠሉት ራሳችሁን ነው፡፡

የምትወዱትና የምትጠሉት ልክ እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ላይነጣጠሉ ተጣምረዋል፡፡ ለራሳችሁ ታማኝ ብትሆኑማ ኖሮ የምትወዱትንና የሚወድዳችሁን ከመውደዳችሁ በፊት የምትጠሉትንና የሚጠላችሁን ትወድዱ ነበር፣ፍቅር ቅንጦት አይደለም፡፡ ፍቅር መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ ከዳቦና ከውሃ፣ ከዓየርና ከብርሃን ይልቅ ፍቅር ያሻችኋል፡፡

ማንም ቢሆን በማፍቀሩ አይኩራራ ይልቁንም ነፃ ሆናችሁ እንዲሁ በዘፈቀደ ዓየሩን ወደ ውስጥ እንደምትስቡትና እንደምታስወጡት ሁሉ ፍቅርንም እንዲሁ በነፃነት ልብም ሳትሉ ተንፍሱት…ፍቅርን ማንም ከፍ ሊያደርገው፣ ሊቀድሰው የሚችል የለም፡፡ ይልቁንም ለፍቅር የሚገባ የተቀደሰ ልብ ሲያገኝ ፍቅር ራሱ ያን ልብ ይቀድሰዋል እንጂ፡፡

ፍቅር አያበድርም፣ አያውስምም፡፡ ፍቅር አይሸጥም፣ አይገዛምም፡፡ ሲሰጥ ግን ሁሉንም ይሰጣል፡፡ ሲወስድም ሁሉንም ይወስዳል፡፡ መቀበሉ በራሱ መስጠት ነው፡፡ መስጠቱም እንዲሁ መቀበል፡፡ እናም፣ ለዛሬ እንዲሁ እንደሆነው ሁሉ ለነገም ለከነገወዲያም እንዲሁ ነው፡፡

ራሱን ሳይሰስት ለባሕሩ የሚለግስ የትኛውም ወንዝ ዘወትር በባህሩ እንደሚሞላው ሁሉ እናንተም እንዲሁ ፍቅር መልሶ ይሞላችሁ ዘንድ ራሳችሁን አንጠፍጥፋችሁ ለፍቅር ተሰጡት፣አዎን … የባሕሩን ስጦታ ከባሕሩ የሚነፍግ ኩሬ መጨረሻው መበስበስም አይደል፡፡

በፍቅር … ትንሽ ወይም ትልቅ የሚሉት ነገር የለም፡፡ ፍቅርን መለካት፣ መመተር … ለፍቅር ደረጃ ማውጣት ስትጀምር፣ ፍቅር መራር ትዝታዎቹን አስታቅፎህ እብስ ብሎ ይጠፋል…

በፍቅር ዘንድ … ትላንት ወይም ዛሬ፣

ዛሬ ወይም ነገ…

እዚህ ወይም እዚያ ብሎ ነገር የለም፡፡

ሁሉም ወቅቶች የፍቅር ወቅቶች ናቸው፡፡ የትኛውም ቦታ ቢሆን ለፍቅር ቤተ መቅደስነት የተገባ ክቡር ነው፡፡ፍቅርን … ወሰንም ሆነ ዳር ድንበር፣ካቴናም ሆነ የተዘጋ በር አይገድበውም ፣ አዎን … ፍቅር ዓይናችሁን ሲያበራው … ያኔ … ሁሉም መልስ ፍቅር ዉስጥ እንደሚገኝ ትረዳላችሁ ፡፡

ግሩም ተበጀ
The Book of Mirdad

ውብ አሁን!!

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot