Get Mystery Box with random crypto!

ንባብ ክፍል [የመጨረሻው ክፍል] ................ እናም እናንብብ! እናንብብ | ስብዕናችን #Humanity

ንባብ

ክፍል [የመጨረሻው ክፍል]

................ እናም እናንብብ! እናንብብ! አሁንም እናንብብ!

ግን እንዴትና ደግሞም ለምን?
ሀሮልድ ብሩም የተባሉ ጸሐፊ “ለምንና እንዴት ማንበብ አለብን?” (How to read and why) በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ እንዴት ማንበብ እንዳለብን ሲያብራሩ፤ “ስታነብ ለምታነበው ጽሁፍ ልብህ ክፍት ይሁን፤ የምታነባቸውን ፊደላት በፍቅር፤ በእርጋታና በጽሞና በውስጠኛው ጆሮህ እያደመጥክ በጸጥታ አንብብ፡፡”

ስናነብ ትክክለኛው የልብ ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል፡፡ ስናነብ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ከሌለን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ልንደርስ እንችላለን። ስናነብ እራሳችንን በባለታሪኮቹ ውስጥ አድርገን ስሜታቸውን ለመጋራት እንችል ዘንድ በፍቅርና በወዳጅነት መንፈስ ሆነን እናንብብ። ጸሀፊው ለምን ማንበብ እንዳለብን ሲገልጹም፤ የምናነበው ምክኒያታዊነታችንን ለማሳደግ እንዲያም ሲል አጠቃላዩን ንቃተ - ህሊናችንን ለማዳበር እናም ደግሞ ከህመማችን ለመፈወስ መሆን አለበት። ማንነታችንን ካላገኘንና እራሳችንን መሆን ካልቻልን፣ ለሌላው ምን መሆን እንችላለን? ሲሉም ይጠይቃሉ። ምክራቸውን እንስማ፤ ጥያቄያቸውንም ለመመለስ እንዘጋጅ፡፡

አመለካከት ማንኛውንም ድርጊት ለማድረግም ሆነ ላለማድረግ የመገፋፋት ሀይል አለው፡፡ ለአንድ ድርጊት የሚኖረን አዎንታዊ አመለካከት፤ ለድርጊት የሚያነሳሳን ሲሆን አሉታዊ … አመለካከት ደግሞ ያንን ድርጊት በንቃት እንዳናከናውን ተነሳሽነታችንን እንደሚቀንሰው በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ። በዚህ ሀሳብ መነሻነትም … ለንባብ ያለንን ተነሳሽነት የሚወሰነው ለንባብ ባለን አዎንታዊ ወይም አሉታዊ አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በዘርፉ የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች፤ በልጆች የማንበብ ልምድ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖን ከመፍጠር አንጻር ግንባር ቀደሙን ሚና የሚጫወቱት ወላጆችና መምህራን መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ወላጆች የልጆቻቸውን የንባብ ልምድ ከማዳበር አንጻር ሁለት ወሳኝ ሚናዎችን ይጫወታሉ፡፡ አንድም “ድርጊት ከብዙ ቃላት ይልቅ ይናገራል” (action speaks louder than words) እንዲሉ የዳበረ የንባብ ልምድ

ያላቸው ወላጆች መኖሪያ፤ በተለያዩ ጋዜጦች፤ መጽሄቶችና መጽሐፍት የተሞላ እንደመሆኑ፣ የንባብ ጠቀሜታን በተመለከተ ለህፃናት ግልጽ መልዕክትን (ያለምንም ንግግርና ገለጻ) ማስተላለፍ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም ወጣቶች የንባብ ባህልን ከቤተሰቦቻቸው ይወርሳሉ ማለት ነው፡፡፡ እናም ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ሁኔታዎችን ለመከታተል፤ አዳዲስ ነገሮችን ለመማር ወይም ለመዝናናት ከሌሎች ዘዴዎች ይልቅ ንባብን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡

በሌላም በኩል ወላጆች በካበቱት የንባብ ልምዳቸው አማካኝነት ለልጆቻቸው አዝናኝና አስተማሪ ድርሳናትን በማንበብ፣ በልጆቻቸው የንባብ አመለካከት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖን ማሳደር ይችላሉ፡፤
ከወላጆች ቀጥሎ የህፃናትንና የወጣቶችን የንባብ ባህል በማሳደግ ረገድ ጉልህና የማይተካ ሚና መጫወት የሚችሉት መምህራንና ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ተማሪችን እንዲያነቡ የሚያበረታቱ መምህራንና በባለሙያ የሚታገዙና በአግባቡ የተደራጁ ቤተ-መጽሐፍት ያላቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ወጣቶች፣ ከሌሎች ይልቅ በእጅጉ የተሻለ የንባብ ልምድ እንደሚኖራቸው ይታመናል፡፡

ይሁንና እስካሁን ድረስ የወጣቶቻችንን የንባብ ልምድ በተመለከተ ሰፊና የተቀናጀ አገር አቀፍ ጥናቶች መደረጉን እርግጠኛ ባልሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚገልጹት ከሆነ፤ ወጣቶቻችን ለንባብ ያላቸው አጠቃላይ አመለካከት በአብዛኛው አሉታዊ እንደሆነ አመላካች ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር አለም እሸቴ በቅርቡ በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ ያካሄዱት የጥናት ውጤት ይሄንኑ እውነት ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡ ፕሮፌሰሩ ወጣቶች ለምን እንደማያነቡ ላቀረቡላቸው ጥያቄ፣ ከሰጧቸው ሰበቦች መካከል እስቲ ጥቂቱን ለአብነት ያህል እንመልከተው፡-
ንባብን ከቤተሰቤ አልለመድኩትም፡፡
በአካባቢዬ ብዙ ቤተ - መጻሕፍት ቤት ስለሌለ አንብብ፤ አንብብ አይለኝም፡፡
ይሄ የአውሮፓ እግር ኳስ እያለ በየት በኩል ላንብብ?
ትላልቅ መጽሐፍትን ሳይ ተስፋ ስለሚያስቆርጡኝ አላነብም፡፡
አንብቦ ለመረዳት ችግር ስላለብኝ ሳነብ አይገባኝም፡፡
የሚሰለቹ መጽሐፍት በመብዛታቸው ምክኒያት አላነብም፡፡
በጊዜ ማጣት ምክኒያት አላነብም፡፡
ለምን እንደማላነብ ራሴም ምክኒያቱን አላውቅም፡፡
መጽሐፍ የማላነበው ለዓይኔ ስለምፈራ ነው፡፡

ወጣቶቹ ላለማንበባቸው የጠቀሷቸውን ሰበቦች ጠቅለል አድርገን ስንቃኛቸው፣ ለወጣቶቻችን የንባብ ችግር ዋነኛው ምክኒያት፣ የንባብ ፍላጎት ማጣት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለዚህም ከወጣቶች የንባብ ልምድ ጋር ተያያዥነት ባላቸው የጥናት ድርሳናት እንደምክኒያትነት የሚጠቀሰው የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ጫና፤ (እዚህ ላይ የእነ ቃና፤ የእነ ዲኤስ ቲቪ፣ የእነ ኤምቢሲ፤ የእነ ኤምቲቪ ወዘተ … ቻናሎች ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡)

በተጨማሪም በሉላዊነት ሳቢያ፣ ገደብ ያልተበጀላቸውና ከምዕራቡ ዓለም በብርሃን ፍጥነት እየተሰራጩ ያሉ የአሉታዊና መጤ ጎጂ ልማዶች መስፋፋትና ወረራ፤ እንዲያም ሲል ወላጆች፣ መምህራንና ትምህርት ቤቶች የንባብን ባህል ከማዳበር አንጻር መጫወት የሚገባቸውን ሚና በአግባቡ መጫወት አለመቻላቸው ነው፡፡
በመጨረሻም በተለይ ህፃናቱንና ወጣቶችን ወደ ንባብ ባህልና ልምድ ለማምጣት ሁላችንም የድርሻችንን ማድረግ እንደሚገባን መዘንጋት የለብንም፡፡
እናንብብ! እናንብብ!

ታደሰ ለገሰ
ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanitybot