Get Mystery Box with random crypto!

ንባብ ክፍል 1 ንባብ በግለሰብም ሆነ በማህበረሰብ ህይወት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ሊኖረው | ስብዕናችን #Humanity

ንባብ

ክፍል 1

ንባብ በግለሰብም ሆነ በማህበረሰብ ህይወት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ሊኖረው የሚገባ መሰረታዊ ክህሎት ነው። የሰው ልጅ ሰብዕናውን የሚቀርፅበትና የማንነቱና የምንነቱ መገለጫ የሆኑትን ባህላዊ፣ ትረካዊና ሥነ ጥበባዊ ቅርሶቹና ዕሴቶቹ እንዳይጠፉ ለቀጣዩ ትውልድ ጠብቆ የሚያቆይበት፣ የሚያስተላልፍበትም ዓይነተኛ መሳሪያም ነው፡፡

ማንበብ የማይችል ግለሰብም ሆነ ማህበረሰብ፤ አካባቢውን የማወቅና የመግለጽ ብቃቱ፣ በማየትና በመስማት ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ለማንኛውም የፈጠራም ሆነ የዕውነታ ጽሁፍ ዕውቀቶች እንግዳና ባይተዋር ይሆናል፡፡ ስለ ሕይወትና ስለ ተፈጥሮ … ስለ ከባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶች ያለው ግንዛቤ ውሱንና የተዛባም ይሆናል፡፡

የዳበረ የንባብ ልምድ በቋንቋ የመጠቀም ብቃታችንን ከማሳደጉም በላይ ሂሳዊ አስተሳሰብና ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ የዳበረ የንባብ ልምድ የሌሎችንም ሀሳብና ስሜት በቀላሉ ለመረዳትና ከማንኛውም አቅጣጫ ለሚሰነዘሩ አዎንታዊም ሆኑ አሉታዊ አስተያየቶች ምክኒያታዊና በሳል፤ ቁጥብና ገላጭ በሆኑ ቃላት ፈጣን ምላሽን መስጠት የሚያስችል ብቃትና ክህሎት ያስታጥቀናል። ንባብ በአንድ ጉዳይ ላይ ትኩረትን ሰብስቦ የማሰብና የማሰላሰል ጠቃሚ ልምድና ብቃትን ያጎናጽፈናል። ታላላቅ ሳይንቲስቶችና ኢንጂነሮች፣ ስመ ጥር ደራሲያን፤ ጸሐፌ ተውኔቶች፤ ሰዓሊያን፤ ገጣሚያንና ባለቅኔዎች ወዘተ የሚፈጠሩት በዳበረ የንባብ ምናባዊ ዓለም ውስት ነው፡፡ ምናባዊ ወደ ሆነው የንባብ ዓለም ውስጥ ስንገባ፣ ግዑዙንና ገሀዱን ዓለም ጥለን፣ በታላቅ ጸጥታና ተመስጦ፣ በስፍራና በጊዜ በማይለካና በማይወሰን፣ ጥልቅና የትየለሌ ወደሆነው የዕውቀትና የጥበብ ዓለም ውስጥ እንገባለን፡፡

ከዚህ ምናባዊ የንባብ ዓለም ከምናገኘው ድንቅ የትኩረትና የተመስጦ ተመክሮ፤ በህይወት ጉዞአችን ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉትን ተግዳሮቶችና ፈተናዎች እንዴት መወጣት እንደምንችል እንማራለን። ውስብስብ ችግሮችን የመፍታት ብቃታችንን እናሳድጋለን፡፡ ከንባብ ጋር የሚኖረን ጥብቅ ቁርኝትና ትሥሥር ለሕይወትና ለተፈጥሮ የምንሰጠውን ዋጋና ክብር በእጅጉ ይጨምራሉ፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ የዳበረ የንባብ ልምድ ያላቸው ግለሰቦች፣ የንባብ ልምድ ከሌላቸው ግለሰቦች ይልቅ በሦስት እጥፍ የተፈጥሮ እንክብካቤና የበጎ አድራጎት (ሰብዓዊ) ድርጅቶች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳታፊዎች ናቸው። ይህ ዓይነቱ ንቁ ተሳትፎ አንባቢያንን በጎ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከማድረጉም በላይ ለግለሰቦችም ሆነ ማህበረሰቦች ደህንነት በእጅጉ ተቆርቋሪና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

ንባብ ጭንቀትንና ውጥረትን በማስወገድ ዘና እንድንል ይረዳናል፡፡ በንባብ አውድ ዙሪያ የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች፤ ጭንቀትን እንደሚቀንስ ደርሰውበታል። ለስድስት ደቂቃ ጸጥ ብሎ ማንበብ የልብ ምትን ያረጋጋል፡፡ የተኮማተሩ የአካሎቻችን ጡንቻዎች ዘና እንዲሉ ያደርጋል፡፡

ንባብ እራሳችንን ለማስደሰትና ለማዝናናት ያስችለናል፡፡ በደራሲያን በጸሐፌ ተውኔቶችና በገጣሚያን የፈጠራ ሥራዎች ውስጥ የምናገኛቸው ገጸ-ባህሪያት በተሳሉበት ምናባዊ ዓለም ውስጥ የሚያደርጉት ልብ አንጠልጣይ እንቅስቃሴ፣ ለአእምሮአችን ምናባዊ ፍሰሀን ያጎናጽፈዋል፡፡

ንባብ ከማዝናናትም ባሻገር የህይወት ክህሎታችንን በማሳደግ ያስደንቀናል፡፡ ንባብ ከፊልምና ከቴሌቪዥን ከምናገኛቸው መረጃዎች ይልቅ የአስተሳሰባችንን አድማስ የማስፋትና ምናባዊ እይታችንን የማሳደግ ብቃት እንዳለው የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የሚያሳዝነው ግን አስቂኝ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ከሌሎች ነገሮች ጋር ተዳምረው ንባብ በብዙ ሰዎች ህይወት ውስጥ ቦታ እንዲነፈገው ምክኒያት ሆነዋል፡፡ አንድ ሰው አዘውትሮ ቴሌቪዥን የሚመለከትና እምብዛም የማያነብ ከሆነ፣ የማንበብ ችሎታው ብቻ ሳይሆን በትክክል የማሰብና የማመዛዘን እንዲሁም ሀሳቡን አቀነባብሮ የመግለጽ ችሎታው ሊቀንስ እንደሚችል በጥናት ተደርሶበታል።

ማር ዎልፍ የተባሉ ጸሐፊ፤ “የአንባቢ አእምሮ ታሪክና ሳይንስ” (The Story and Science of the Reading Brain) በተሰኘ መፅሐፋቸው እንዲህ ብለዋል፡- “ስታነብ ለማሰብ ወይም አንድን ነገር ለማሰላሰል ጊዜ ይኖርሃል፡፡ የማሰቢያ አፍታን ታገኛለህ፡፡ በሌላ በኩል ፊልም ወይም ቴሌቪዥን ስትመለከት አልያም ሬዲዮ ወይም ቴፕ ስታዳምጥ ወደ ውስጥህ የማየትና የማሰብ ጊዜን አታገኝም፡፡ ይህ የንባብ ሂደት ውስጥ የምታገኘው አፍታ፣ የማሰብና የማስታወስ ችሎታህን በእጅጉ ያዳብረዋል፡፡”

ለማጠቃለል በተፈጥሮ ሳይንስ፤ በማህበረሰብ ሳይንስ፤ በፍልስፍና ታሪክ፤ በስነ - ጥበብና በሌሎችም ዘርፎች ያለን ዕውቀት ሊሰፋና ሊያድግ የሚችለው በንባብ ነው፡፡ንባብ በዕውቀትና በጥበብ የተካነ፣ ማንነቱንና ምንነቱን የተረዳ፣ ሁሉን ጠያቂና ተመራማሪ፣ በየተሰማራበት የሙያ መስክ ስኬታማ የሆነና እራሱንም ሆነ አገርና ወገኑን የሚጠቅምና የሚያሳድግ፣ ደስተኛና የተረጋጋ ሕይወት ያለው ዜጋ እንዲኖረን ያስችለናል፡፡

ከታሪክ ሂደት መረዳት እንደምንችለው፤መጪዎቹን ዘመንና ትውልድ መቆጣጠርና መምራት የሚችሉት በፈርጣማ ጡንቻዎቻቸው የሚያስቡ አምባገነኖች ሳይሆኑ በዳበረ የንባብ ልምድ የበለጸገ አዕምሮና ብሩህ አስተሳሰብ ያላቸው አንባቢማህበረሰቦች ስለመሆናቸው አንዳችም ጥርጥር ሆነ ብዥታ ሊኖረን አይገባም፡፡ እናም እናንብብ! እናንብብ! አሁንም እናንብብ!

ይቀጥላል......

ታደሰ ለገሰ

ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanitybot