Get Mystery Box with random crypto!

“ኤልሻዳይ” ግብረ ሰናይ ድርጅት ከኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ጋር በመመሳጠር የተጠረጠሩበትን የሙስና ወን | Ethio Fm 107.8

“ኤልሻዳይ” ግብረ ሰናይ ድርጅት ከኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ጋር በመመሳጠር የተጠረጠሩበትን የሙስና ወንጀሎች ፖሊስ ይፋ አደረገ

ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ደቨሎፕመንት አሶሴሽን መንግስትዊ ያልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት በተረጂዎች ስም ከብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለእርዳታ የተዘጋጀን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን አላግባብ ወስዶ ለግል ጥቅም አውሏል በሚል ተጠርጥረው ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ፖሊስ ባደረገው የማጣራት ስራ የተሰበሰበውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በተለይ ለኢቲቪ አስታውቋል።

በምርመራ ሂደቱ የተገኙ ግኝቶችም፦

1ኛ- ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ደቨሎፕመንት አሶሴሽን በየጊዜው አሉ ተብሎ እርዳታ የሚጠየቅላቸው ዜጎች በትክክል ስለመኖራቸው እና አለመኖራቸው በተደረገ ምርመራ፡-

ድርጅቱ በክልል ካሉት ማዕከል ውስጥ በ3 ማዕከላት ማለትም በአማራ ክልል ቁጭት ለልማት ማዕከል ከ 2010 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የተረጂዎችን ቁጥር በመጨመር፤ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2019 ማእከሉ 14 ተረጂዎች ብቻ እያለው ዓመቱን ሙሉ በ2 ሺህ 631 ተረጂዎች ስም የእርዳታ ስንዴ ጠይቆ ከኮሚሽኑ የተሰጠው መሆኑን በማስረጃ ተረጋግጧል።

ድርጅቱ በአፋር እና ደቡብ ክልል ማዕከል የተረጂዎችን ቁጥር በመጨመር የጠየቀ እና የወሰደ መሆኑን፣ በጋምቤላ ክልል ማዕከል ስም የጠየቀው ተፈቅዶለት ያልወሰደ እና በሙከራ ደረጃ የቀረ መሆኑን በማስረጃ ለማረጋገጥ ተችሏል።

2ኛ- ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዲቨሎፕመንት አሶሴሽን በተለይ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ አለአግባብ ከኮሚሽኑ ጠይቆ የተሰጠውን የእርዳታ ስንዴ ምን እንደሚያደረገው በተደረገ ምርመራ፡-

ድርጅቱ ከመንግስት የወሰደውን ስንዴ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ለሚገኝ ኪያ የዱቄት ፋብሪካ (ሶሮሮ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ ማህበር) 66 ሺህ ኩንታል ስንዴ በ66 ሚሊዮን ብር ሸጦ ገንዘቡን የወሰደ መሆኑን፣ 6 ሺህ ኩንታል ስንዴ በብር 6 ሚሊዮን ግምት በ4 ተሸከርካሪ በአይነት ከሶሮሮ ትሬዲግ የተለዋወጠ መሆኑን፤

ኤልሻዳይ ድርጅት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አዋሽ መልካ የሚገኝ ነጃኼ ሬዲን የዱቄት ፋብሪካ ባለቤት እና ሰራተኛ ስም 27 ሚሊዮን ብር የገባለት በመሆኑ ነጃሄ ትሬዲን ተጠይቆ 15 ሚሊዮን ብር ያስገባው ከኤልሻዳይ ስንዴ ገዝቶ መሆኑን በሰነድ በማስደገፍ ቃሉን የሰጠ ሲሆን ቀሪው 12 ሚሊዮን ብር ቢሆን የሰነድ አያያዝ ችግር ነው እንጂ የስንዴ ግዥ ብር ነው በማለት የምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል።

3ኛ- በኤልሻዳይ ድርጅት የበላይ አመራር አቶ የማነ ገ/ማሪያም እና በኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ መካከል መመሳጠር መኖር እና አለመኖሩን በተደረገ ምርመራ፡-

ኤልሻዳይ ኮሚሽኑን እርዳታ ለመጠየቅ ያዘጋጀው የአንድ ጊዜ በእጅ ጽሁፍ የረቀቀ መጠይቅ ሰነድ ተገኝቶ በፎረንሲክ ምርመራ ረቂቂ የእጅ ጽሁፍ ተመርምሮ የብሔራዊ አደጋ መከላከል ስራ አመራር ከሚሽን ኮሚሽነር በኤልሻዳይ ስም የተዘጋጀ መሆኑ ተረጋግጧል።

በተጨማሪም በኮሚሽነሩ ቤተሰቦች ላይ በተደረገ ማጣራት፦

1ኛ - የኮሚሽነሩ ወንድ ልጅ ኢያሱ ምትኩ ካሳ በኤልሻዳይ ድርጅት በተላለፈ ገንዘብ መኪና ተገዝቶለት ይህንኑ መኪና መልሶ ኤልሻዳይ የገዛው መሆኑን በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን፤ እንዲሁም ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በኤልሻዳይ ድርጅት ፀሀፊ ስም በወር 15 ሺህ ብር በተከራየው ሙሉ ጊቢ ውስጥ የሚኖር መሆኑን መረጃ ደርሶ፤ በቤቱ ውስጥ የተባለው የኮሚሽነሩ ልጅ መኖሩን ወርሃዊ ክፍያውንም ኤልሳሻዳይ ድርጅት እንደሚከፍልለት በሰውና በሰነድ ተረጋግጧል፣

2ኛ- የኮሚሽነሩ ሴት ልጅ ወ/ሮ ሚኪያ ምትኩ ካሳ በኤልሻዳይ ድርጅት ውስጥ ተቀጣሪ ሳትሆን በኤልሻዳይ ድርጅት ፔሮል ውስጥ ስሟ ተካቶ ለ1 ዓመት ያክል በወር አምስት ሺህ ብር ደመወዝ በባንከ በኩል ሲከፈላት እንደነበር በማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል። እንዲሁም ከኤልሻዳይ ድርጅት የባንክ ሂሳብ ብር 800 ሺህ ብር ወደ ሚኪያ ምትኩ በተለያዩ ጊዚያት ገቢ መሆኑን በሰነድ ማረጋገጥ ተችሏል፤ እንዲሁም ተጨማሪ ማጣራም በማጣራት ላይ ይገኛል

3ኛ- የኮሚሽነሩ ባለቤት በወ/ሮ ሶፊያ ጀማል ስም ከእንይ ጀኔራል ቢዝነስ ሪል ስቴት (በወኪል የማነ ወ/ማሪያም በርሄ አማካኝነት (የኤልሻዳይ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ) ከኤልሻዳይ ድርጅት ሂሳብ ወጭ በተደረገ በብር 8,306,737.75 የቦታ ስፋት 388.75 ካሬ ሜትር የሆነ በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ የተገዛው መሆኑን እንዲሁም ተጨማሪ ጥቆማዎች ላይም ማጣራት እየተካሄደ ስለመሆኑ

4ኛ- የኮሚሽነሩ ወላጅ እናት ወ/ሮ ኢቲኮ አጌቦ ጆሀር ከኤልሻዳይ ድርጅት 5,000,000.00 (አምስት ሚሊዮን) ብር በሲፒኦ ገቢ በሆነላት ብር በቦሌ ክፍለ ከተማ ብቻ በተደረገ ማጣራት በኤልሻዳይ ድርጅት እና የኮሚሽነሩ የቅርብ ጉዳይ አስፈፃሚ በሆኑ ግለሰቦችና የወ/ሮ ኢቲኮ አጌቦ ጆሀር ህጋዊ ወኪሎች አማካኝነት 7 ቤቶች የገዛች መሆኑ በተጨማሪም ከወ/ሮ ኢቲኮ አጌቦ ጆሀር ስም የተገዙ ቤቶችን በተመለከተ ሙሉ ውክልና ለኤልሻዳይ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለሆኑት አቶ የማነ ገ/ማሪያም ውክልና ሰጥተው የተገኙ መሆኑን ይህ ቀሪ የማጥራት ስራ የሚቀረው ቢሆንም መመሳጠር መኖሩን ያስረዳል።

እንዲሁም ከእነዚህ ሰባት ቤቶች መካከል አንዱን አቶ የማነ ገ/ማሪያም በተሰጠው ውክልና መሰረት ከወ/ሮ ኢቲኮ አጌቦ ጆሀር ለአቶ ምትኩ ካሳ መሸጡን ይህ ሽያጭ ሲፈፀም አቶ የማነ ገ/ማሪያም ሀሰተኛ መታወቂያ፣ ሀሰተኛ ፎቶ መጠቀሙ ተረጋግጧል።

5ኛ አቶ ምትኩ ካሳ ሚኖሩበት ቤት ቁጥር በማስመዝገብ እና የሌላን ሰው ፎቶግራፍ በመጠቀም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በስማቸው አሰርተው የተገኙ መሆኑን በማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል፣ ቤተሰባዊ ግንኙነቱ በመጣራት ላይ የሚገኝ 18 አመት ባልሞላው ልጅ መሀመድ አብዲልፈታህ አብዱላሂ በተበለ ስም ከእንይ ጀኔራል ቢዝነስ ሪል ስቴት ከኤልሻዳይ ድርጅት ሂሳብ ወጭ በተደረገ ገንዘብ በብር 8,306,737.75 የቦታ ስፋት 388.75 ካሬ ሜትር የሆነ በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ የተገዛው መሆኑን፣

በምርመራ መዝገቡ ላይ ተጠርጣሪ የሆኑት፡-

1. የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ እና ቤተሰቦቻቸው፤

2. የኤልሻዳይ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ የማነ ወ/ማሪያም፤

3. የኤልሻዳይ ድርጅት ኦፕሬሽናል ዘርፍ ምክትል ስ/አስኪያጅ ዶ/ር ዮናስ ወ/ትንሳይ እና

4. የኤልሻዳይ ድርጅት የፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ስ/አስኪያጅ አቶ ደመወዝ ኃይሉ መሆናቸውን
ኢቢሲ ፖሊስን ጠቅሶ ዘግቧል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሐምሌ 06 ቀን 2014 ዓ.ም