Get Mystery Box with random crypto!

የተወዳጁና ድምጸ መረዋው አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ስርዓት ነገ ሐሙስ መስከረም 19 | ETHIO NEWS

የተወዳጁና ድምጸ መረዋው አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ስርዓት ነገ ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 በአዲስ አበባ አራት ኪሎ መንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን እንደሚፈጸም የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው አስታወቀ።

የተወዳጁን የኪነጥበብ ሰው ሥርዓተ ቀብር ለማስፈጸም የተቋቋመው ኮሚቴ ጉዳዩን አስመልክቶ በአርቲስቱ በመኖሪያ ቤት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ፥ የወንድማችን ህልፈት ድንገተኛ በመሆኑ ሀዘናችን መሪር ነው፥ በዚህ ሁኔታ መግለጫ መስጠትም ከባድ ነው ብሏል።

አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅን በአጭር መግለጽ ከባድ ነው፤ በህይወት ዘመኑ የሰራቸው ተግባራት ግን ትውልድ የሚማርባቸው ይሆናሉ ሲል ገልጿል።

በነገው ዕለት የአስከሬን ስንብት በመኖሪያ ቤቱ በማድረግ በወዳጅነት ፓርክም ከ6፡ 00 ሰዓት ጀምሮ በመንግስት ኃላፊዎች፣ በሙያ አጋሮቹ፣ በአድናቂዎቹና ወዳጅ ዘመዶቹ የአስክሬን ስንብት እንደሚካሄድ ገልጿል።

በመቀጠልም ከቀኑ 10:00 ጀምሮ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴደራል ቤተክርስቲያን ስርዓተ ቀብሩ እንደሚፈጸም ተናግሯል።

ጎልማሳው የጥበብ ሰው ማዲንጎ አፈወርቅ ስለ ፍቅር፣ ትዝታ፣ ባህል፣ ሀገር፣ ታሪክና ሌሎች ጉዳዮችን የሚዳስሱ መልዕክቶችን በተስረቅራቂ ድምጹ በማዜም በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ስራ ላይ የራሱን አሻራ አሳርፏል።

ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ወቅት እያመመው ግንባር ድረስ በመሄድና ማሰልጠኛም ምልምሎችን በማነቃቃት የራሱ የሆነ ታሪክ የሰራ አርቲስት መሆኑም ይታወቃል።

በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር አዘዞ ተወልዶ በደብረታቦር ያደገው አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ መስከረም 17/2015 ዓ.ም ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።