Get Mystery Box with random crypto!

ዐበይት ዜናዎች 1፤ ገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሽዴ ፌደራል መንግሥቱ ለአዲስ ቤተመንግሥት ግንባታ | ኢትዮ መረጃ - NEWS

ዐበይት ዜናዎች

1፤ ገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሽዴ ፌደራል መንግሥቱ ለአዲስ ቤተመንግሥት ግንባታ የጠየቀው በጀት የለም ሲሉ ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መናገራቸውን ዶይቸቨለ ዘግቧል። ለቤተመንግሥቱና ሌሎች በጠቅላይ ሚንስትሩ ክትትል ስር ላሉ ፕሮጀክቶች በመጽደቅ ላይ ያለ በጀት እንደሌለም አሕመድ ገልጸዋል ተብሏል። ሚንስትሩ ይህን ያሉት፣ ለአዲስ ቤተ መንግሥት ግንባታና "ገበታ ለአገር" ለተሰኙ ፕሮጀክቶች እየተሰበሰበ እንደኾነ የሚነገርለት 500 ቢሊዮን ብር በመንግሥት ቋት ውስጥ ገብቶ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ እንደሆነ ተገልጧል። አሕመድ የቤተ መንግሥትና ሌሎች በጠቅላይ ሚንስትሩ ክትትል ስር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ማሰሪያ ገንዘብ ከተለያዩ ምንጮች የተገኘና ለጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሮጀክቶች የተሰጠ ድጋፍ መኾኑን ተናግረዋል ተብሏል።

2፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚያዋስኗት ድንበሮች የሚካሄደውን ኢመደበኛ የጠረፍ ንግድ ሕጋዊ እውቅና ለመስጠት የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱን ፎርቹን ዘግቧል። ሚንስቴሩ በኢትዮጵያ-ጅቡቲ ድንበር ላይ የሚካሄደውን ኢመደበኛ ንግድ ሕጋዊ የሚያደርግ ሕግ ማዘጋጀቱን ዋዜማ ትናንት ዘግባ ነበር። ይሄው የሕግ ማዕቀፍ በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ የሚካሄደውን ኢመደበኛ ንግድ ጭምር እንደሚያካትት የፎርቹን ዘገባ አመልክቷል። የሕግ ማዕቀፉ ዓላማ፣ በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ ኮንትሮባንድ ንግድን መግታት ነው።

3፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሱዳን ጎረቤቶች ከሱዳኑ ግጭት በሚሸሹ ስደተኞች ላይ የመግቢያ ገደቦችን ባስቸኳይ እንዲያነሱ በምሥራቅ አፍሪካ ቢሮው በኩል ባወጣው መግለጫ ጥሪ አድርጓል። አምነስቲ፣ አገራቱ የሱዳን ስደተኞች መታወቂያ ወይም ቪዛ ባለመያዛቸው ከመግባት እንዳይከለከሉ፣ የጥገኝነት ምዝገባ እንዲያፋጥኑላቸው፣ አንዳችም አድልዖ እንዳይፈጽሙባቸውና አስፈላጊው የደኅንነት ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው ጭምር ጠይቋል። ድርጅቱ ስደተኞቹ ከሰነድ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች እየገጠሟቸው እንደኾነ ገልጧል።

4፤ ሱዳን ከሩሲያ ተዋጊ አውሮፕላኖችን የመግዛት ፍላጎት እንዳላት የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ማሊክ አጋር ለአንድ የሩሲያ ጋዜጣ ጋር አጋር ተናግረዋል። ማሊክ አጋር የሱዳን ጦር ሠራዊት በሩሲያ ሥልጠና እያገኘ. መኾኑንም መናገራቸውን ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች ጠቅሰዋል። ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን ቢጥሉባትም፣ ሱዳን ግን ክፕሩሲያ ጋር ወታደራዊና የቴክኒክ ትብብሮቿን እንደምትቀጥል አጋር ተናግረዋል ተብሏል።

5፤ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ለዓመታት የተራዘመው ጠቅላላ ምርጫ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ በታቀደው መሠረት ይካሄዳል ሲሉ ቃል መግባታቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ዘግቧል። ኪር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ሲካሄድ፣ በዕጩነት እንደሚቀርቡ መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ኪር እና የተቃዋሚ መሪ ሬክ ማቻር የአንድነት ሽግግር መንግሥቱን ቆይታ ባለፈው ነሐሴ ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት ማራዘማቸው ይታወሳል። [ዋዜማ]

@ethio_mereja_news
@ethio_mereja_news