Get Mystery Box with random crypto!

የማለዳ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ዓለማቀፍ ረድዔት | ኢትዮ መረጃ - NEWS

የማለዳ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የትግራይ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ዓለማቀፍ ረድዔት ድርጅቶች ያቋረጡት የምግብ ዕርዳታ እንዲቀጥል ጥሪ ማድረጉን ቪኦኤ ዘግቧል። በክልሉ የምግብ ዕርዳታ ሥርጭቱ ባለፈው ወር ከተቋረጠ ወዲህ፣ ወደ ክልሉ እየገቡ ያሉት መጠነኛ የሕጻናት አልሚ ምግቦችና የግብርና ግብዓቶች ብቻ መኾናቸውን ኮሚሽኑ መግለጡን ዘገባው ጠቅሷል። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሽሬ ከተማ የዕርዳታ መጋዘኔ ከፍተኛ መጠን ያለው የዕርዳታ እህል ተዘርፏል በማለት፣ የዕርዳታ ሥርጭት ማቋረጡ ይታወሳል። የአሜሪካው ዓለማቀፍ የልማትና ዕርዳታ ድርጅትም በተመሳሳይ ምክንያት የዕርዳታ ሥርጭት ለጊዜው አቋርጫለኹ ብሏል።

2፤ ዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት የጅቡቲ መንግሥት በሕገወጥ መንገድ ገብታችኋል ብሎ ያስወጣቸው 6 ሺህ  ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች አፋር ክልል ደዋሌ መግባታቸውን አስታውቋል። ድርጅቱ፣ በምሥራቃዊው መስመር ማለትም በፑንትላንድ፣ ሱማሌላንድና ጅቡቲ በኩል ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ለሚሰደዱ 1 ሚሊዮን ያህል ፍልሰተኞች የ58 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ከለጋሾች ጠይቋል። በምሥራቁ መስመር ባሕር አቋርጠው የሚጓዙት ፍልሰተኞች አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን መኾናቸውን የጠቀሰው ድርጅቱ፣ ለጋሾች ይህንኑ መስመር ዘንግተውታል በማለት ወቅሷል። ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፉን የጠየቀው፣ በስደት ወቅት እንግልት ለሚገጥማቸው ፍልሰተኞችና ለተመላሾች የተለያዩ ድጋፎችን ለመስጠት ነው።

3፤ ኢትዮጵያ፣ ሱማሊያና ኬንያ በጋራ ድንበር ጸጥታ ዙሪያ ለመተባበር የሚያስችላቸውን የጋራ ፕሮጀክት መርቀዋል። ከብሪታኒያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው የጋራ ፕሮጀክቱ መሠረቱ የተጣለው፣ በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ ማንዴራ አውራጃ እንደኾነ የኬንያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የፕሮጀክቱ ዓላማ፣ በአገራቱ የጋራ የድንበር አካባቢ ሰላም፣ ጸጥታ፣ ልማትና ድንበር-ዘለል ትብብሮችን ማረጋገጥ ነው። ሦስቱ አገራት የጋራ ፕሮጀክቱን የጀመሩት፣ በነውጠኛው አልሸባብ ላይ የጋራ ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ ከተስማሙ ከጥቂት ስምንታት በኋላ ነው።

4፤ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስቴር የኢትዮጵያው "ቦርከና" ጋዜጣ "በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል ውጥረት እየተፈጠረ ይኾን?" በማለት ያተመውን ሃተታ "በሐሰትና ግምታዊ ድምዳሜ የተሞላ" በማለት ተችቷል። ሚንስቴሩ በመግለጫው፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በቅርቡ ስለ ሱዳኑ ግጭት በሰጡት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያን ጎሸም ያደረጉ አስመስሎ አቅርቧል በማለት ወቅሷል። ጋዜጣው "ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሥመራ መሄድ ፈልገው፣ የኤርትራ መንግሥት ሁለት ጊዜ ፍቃድ ነፍጓቸዋል" እንዲኹም "ኤርትራ ለአማራ ፋኖዎች ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠቷ የዐቢይ ካድሬዎች ኢሳያስን እየተቹ ነው" በማለት የጻፋቸው ነገሮች "ሐሰት" መኾናቸውንም ሚንስቴሩ ገልጧል። ሚንስቴሩ፣ ኤርትራ አዲስ ወታደራዊ ዝግጅት እያደረገች እንደኾነ ጋዜጣው ያሰራጨውን ወሬም "የተሳሳተ" በማለት አስተባብሏል።

5፤ ደቡብ ሱዳን የግብጹ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ በሱዳን ግጭት ዙሪያ ለመምከር የመሪዎች ስብሰባ እንዲካሄድ ለፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ሃሳብ ማቅረባቸውን በውጭ ጉዳይ ሚንስቴሯ በኩል አረጋግጣለች። ፕሬዝዳንት ሲሲ ይህንኑ ሃሳብ ያቀረቡት፣ ውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸውን ሳሜ ሽኩሪን ከአራት ቀናት በፊት ወደ ጁባ በላኩበት ወቅት እንደኾነ ሚንስቴሩ ገልጧል። ፕሬዝዳንት ኪር በበኩላቸው፣ የመሪዎች ጉባዔ ከተካሄደ የሁሉንም የሱዳን ጎረቤቶች መሪዎች ያካተተ ይሁን የሚል መልስ መስጠታቸውንና የፕሬዝዳንት ሲሲን ምላሽ እየተጠባበቁ መኾኑን ሚንስቴሩ ጨምሮ አመልክቷል።

Via ፦ [ዋዜማ]

@ethio_mereja_news
@ethio_mereja_news