Get Mystery Box with random crypto!

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን የተሰጠ መግለጫ *** ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ የማይማረው ህወሐት ለ | ETHIO-MEREJA®

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን የተሰጠ መግለጫ
***
ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ የማይማረው ህወሐት ለአራተኛ ዙር በህዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል። የፌዴራልና የአማራ ክልል ክልሉ መንግስታትም በህዝብ ላይ የተቃጣውን የጥፋት ወረራ በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ አበክረን እንጠይቃለን!

የኢትዮጵያ ህዝብ ዘላለማዊ ጠላት የሆነው ወያኔ ህወሐት በህዝብ ትግል ተገፍትሮ ወደ ትግራይ ከተሰበሰበ በኋላ በተደጋጋሚ ወረራ በመፈፀም በህዝባችን ላይ ለጆሮ የሚከብድ ዘግናኝ ግፍ ፈፅሟል። ምንም እንኳን ህወሐት በተደጋጋሚ ጊዜ በቆሰቆሰው ጦርነት የአማራ እና የአፋር ህዝብ በቀጥታ የገፈቱ ቀማሽ ይሁኑ እንጅ ዋና ዓላማው ኢትዮጵያ ሐገራችንን መበታተን እና የፈራረሰች ሐገር መፍጠር መሆኑን በአፈ ቀላጤው በኩል በተደጋጋሚ ተናግሯል።

ይህ የእናት ጡት ነካሽ ቡድን የሐገራችን ደጀን የሆነውን የሰሜን እዝ የመከለከያ ሰራዊት በማጥቃቱ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያጋጠመውን ቁጣ መቋቋም ተስኖት ለሶስተኛ ጊዜ እየተመላለሰ ያደረገው የሐገር ማፍረስ ሙከራ ባይሳካለትም እንኳን አድፍጦ ለጦርነት ከመዘጋጀት ግን ቦዝኖ አያውቅም።

ህወሐት ከጦርነት ውጭ መኖር የማይችል፣ በጦርነት አድጎ በጦርነት ያረጀ ቡድን በመሆኑ በመላው የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ አማፂያንን ከማስታጠቅ አልፎ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመወገን ሐገራችንን የጦር ቀጠና ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ነበር የከረመው። በቀጥታ ከሚደግፋቸው የጥፋት ኃይሎች በተጨማሪ የራሱን ኃይል በማደራጀት የሰርጎ ገብ ኃይል እየላከ ህዝባችንን ሲረብሽ መክረሙ ሳያንሰው በአሁኑ ሰዓት በራያ በኩል ቀጥተኛ የሆነ ጥቃት በህዝባችን ላይ ለአራተኛ ጊዜ ወረራ ከፍቶ ይገኛል።

ኋላ ቀርነት እና ግትርናት ዋና መገለጫው የሆነው የጥፋት ቡድን የሚሊዮኖችን ህይዎት በቀጠፈውና ከተደጋጋሚ ስህተቱ ባለመማር ዛሬም ለሌላ ዙር እልቂት ተዘጋጅቶ በህዝባችን ላይ ጦርነት ከፍቷል።

በህዝቦች እኩልነት እና በብሔረሰቦች መብት ፈፅሞ የማያምነው ህወሐት እኔ የማልገዛት ኢትዮጵያ ተረጋግታ መኖር የለባትም የሚል ያልተገራ ክፉ አመሉን በተደጋጋሚ አሳይቷል። በዚህም እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን እኩልነትን ፈፅሞ እንደማይሻ አረጋግጧል።

ለህዝባችን የሚከተሉትን መልዕክቶች እናስተላልፋለን

1. ምንም እንኳን አሸባሪው እና ተስፋፊው ወያኔ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጠላት ቢሆንም ፣ በተለይ የአማራ ህዝብ የቡድኑ ወረራ ቀጥተኛ ሰለባ እና ገፈት ቀማሽ በመሆኑ ጦርነቱን የመመከት ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝባችን ካለፈው የጥፋት ግዜ በመማር ከታሪካዊ ጠላቱ የሚሰነዘርበትን ወረራ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት እንዲመክት፣

2. ህዝባችን ከወያኔ ትጥቅ አስፈች ፕሮፖጋንዳ ራሱን እንዲጠብቅ እና ከዚህ ታሪካዊ ጠላት የሚመጣን ማንኛውንም ውዥንብር ጆሮ እንዳይሰጥ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የወገን ኃይሎች ለወያኔ የሚያሳዩትን የተለሳለሰ የባንዳነት መንገድ ህዝባችን ፈፅሞ እንዳያዳምጥ እና እንዲህ ያሉትን ቡድኖች አጥብቆ እንዲታገል፣

3. የአማራ እና የአፋር ህዝብ የጦርነቱ ዋና ገፈት ቀማሽ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኃይሎች የሚፈልጉትን ሁሉ በማቅረብ ከሐገሩ ጎን እንዲቆም

4. ህዝባችን ይህን ታሪካዊ ጠላት በመቅጣት የተለመደ ጀግንነቱን እንዲወጣ ስንል ጥሪ እያቀረብን፤ በተለይ መንግስት በህዝባችን ላይ ለአራተኛ ጊዜ እየተፈጸመ የሚገኘውን ወረራ በዝምታ የሚመለከት ከሆነ፤ ህዝባችን ስርአትን አምኖ ችግሮች ሁሉ በህግ አግባብ ይፈታሉ የሚል ቀናኢነቱ ማታለያ ሆኖ ከዋለ፤ ይህ በራያ ብቻ የማይቆም ይልቁንም የሁሉ ነገር መፍረሻና ማፍረሻ እንዲሆን መንግስት የፈቀደ መሆኑን ታሪክ የሚመዘግበው ሀቅ ይሆናል።

5. በህወሐት ችግር የአማራና የትግራይ ህዝቦች እንዲሁም መላ ሀገሪቱና ቀጠናው ችግር ውስጥ እየወደቀ በመሆኑ ይህ በአስቸኳይ እንዲቆም እያሳሰብን በተለይ የፌዴራሉ መንግስትና የአማራ ክልል መንግስት በህዝባችን ላይ እየተፈጸመ የሚገኘውን ወረራ በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ አበክረን እንጠይቃለን!

ሚያዝያ 07/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ

   - ETHIO-MEREJA -
   T.me/ethio_mereja