Get Mystery Box with random crypto!

ሰኔ 03 2014 - የስፖርት አበይት መረጃዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ሐገር ቤት ለመመለ | Afrihealth TV

ሰኔ 03 2014 - የስፖርት አበይት መረጃዎች
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ሐገር ቤት ለመመለስ ጉዞ ሲጀምር በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ልዑክም ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡
ለቀጣይ ዓመቱ የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አራት ከግብጽ፣ ማላዊና ጊና ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ከግብጽ ጋር አድርጎ 2ለ0 ማሸነፉ ይታወቃል፡፡ ሳይገመት ከጨዋታ ብልጫ ጋር ያሸነፈው ብሄራዊ ቡድኑ በማላዊ ከተዘጋጀለት የምሳ ግብዣ በኋላ ከደቂቃዎች በፊት ወደ አዲስ አበባ ጉዞ መጀመሩን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተናግሯል፡፡
ፈርዖኖቹን ላሸነፉት የዋልያዎቹ አባላት 2 ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መናገሩ ይታወሳል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ በጀመረው ስብስብ ውስጥ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራና ዋና ጸሐፊው ባህሩ ጥላሁንም እንዳሉበት ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቀጣዩ መስከረም ወር ከጊኒ ጋር የምድቡን ሶስተኛ ጨዋታ የሚያከናውን ይሆናል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ግብጽን አሸንፎ ከፍተኛ ሙገሳ ቢቀርብለትም ዓለም ዓቀፍ ጨዋታዎችን የሚጫወትበት ሜዳ ማጣቱ የመንግስት ቀጣዩ የቤት ስራ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በተያያዘ ዜና በሞሪሺየስ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 22ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ አትሌቶች አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ ነው፡፡ ከሰዓታት በፊት በተካሄደ የ3 ሺ ሜትር መሰናክል ኢትዮጵያውያን ተከታትለው በመግባት ማሸነፋቸው ታውቋል፡፡
ርቀቱን በ8 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ ከ38 ሰከንድ ያጠናቀቀው ኃይለማሪያም አማረ ወርቅ ሲወስድ ታደሰ ታከለ የብር ሜዳሊያውን አግኝቷል፡፡ ሳሙኤል ፍሬው ደግሞ አምስተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ በ10 ሺ ሜትር ሞገስ ጥዑማይና ጭምዴሳ ደበሌ የወርቅና ብር ሜዳሊያ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ በ5 ሺ ሜትር ሴቶች ፋንታዬ በላይነህ ብር እነዲሁም በ1 ሺ 500 ሜትር ሴቶች አያል ዳኛቸው የነሀስ ሜዳሊያ ማግኘታቸው አይዘነጋም፡፡
ከትናንት በስቲያ ረቡዕ የተጀመረው 22ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከነገ በስቲያ እሁድ ይጠናቀቃል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬና ነገ ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን እንደምታገኝ ይጠበቃል፡፡
ከውጭ
ከዛሬ አርብ ጀምሮ በተከፈተው የክረምቱ የዝውውር መስኮት የበርካታ ተጨዋቸች እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
የዝውውር መስኮቱ ሳይከፈት ፊሊፕ ኩቲኖን፣ ቡበከር ካማራን፣ ዲየጎ ካርሎስን እና ሮቢን ኦልሰን ያስፈረመው አስቴንቪላ ስምምነቱን ዛሬ ያጸድቃል፡፡ ማንችስተር ሲቲም የኤርሊንግ ብራውት ሃላንድ ስምምነቱን የሚያጸድቀው ከዛሬ ጀምሮ ነው፡፡
ሪያል ማድሪድ የአንቶኒዮ ሩዲገርን ሊዮን የአሌክዛንደር ላካዜት የነጻ ዝውውርን በይፋ የሚያጸድቁበት ጊዜ ላይ ደርደዋል፡፡ የፖል ፖግባ፣ ጋሬዝ ቤል፣ የሴ ሊንጋርድ፣ ሳዲዮ ማኔ፣ ዳርዊን ኑኔዝ፣ሮበርት ሎዋንዶውስኪ፣ ኡስማን ደምበሌ፣ የክሪስቶፈር ንኩንኩ፣ የዝውውር አጀንዳም የሚዘጋው ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ወራት ገደማ ክፍት ሆኖ በሚቆየው የክረምቱ የተጨዋቾች የዝውውር ወቅት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡