Get Mystery Box with random crypto!

2ኛው ተርባይን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀመረ | Ethio Times®️

2ኛው ተርባይን
የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀመረ
በአፍሪካ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሁለተኛ ተርባይኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ወረዳ በታደሙበት ዝግጅት ነው በዛሬው ዕለት ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት የጀመረው።

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል ዩኒት 9 የሚባለው ሁለተኛው ተርባይን የተሳካ ተከላ እና ሙከራ ከተደረገ በኋላ ኃይል የማመንጨት ስራው እውን ሆኗል።ዛሬ በይፋ ሥራ የጀመረው ሁለተኛው ዩኒት 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል።

በተያዘው ዓመት ከስድስት ወራት በፊት የካቲት 13፣2014 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ታሪካዊ የተባለለትን 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ዩኒት 10 የሚባለው የመጀመሪያው ተርባይን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት በስኬት ኃይል የማመንጨት ስራ መጀመሩም የሚታወስ ነው፡፡

ግድቡ በአጠቃላይ የሚኖሩት 13 ተርባይኖች ግንባታና ተከላ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የማመንጨት አቅም 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ይደርሳል።