Get Mystery Box with random crypto!

የመካነ-እየሱስ/እስቴ - ስማዳ 50.5 ኪ.ሜ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ በፍፃሜ ምዕራፍ ላ | Ethiopian Construction Work Professionals - ETCONp

የመካነ-እየሱስ/እስቴ - ስማዳ 50.5 ኪ.ሜ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ በፍፃሜ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

አሁን ላይ ከአጠቃላይ የግንባታ ሥራው 86 በመቶው ተከናውኗል። ቀሪ ሥራዎቹን በሚቀጥሉት አምስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ከጠቅላላው የመንገዱ ክፍል 47 ኪሎ ሜትሩን አስፋልት ማልበስ ተችሏል። በተጨማሪም የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት፣ የሰብቤዝ እና ቤዝኮርስ፣ የሾልደር፣ የውኃ መፋሰሻ፣ የድልድይ እንዲሁም የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

ግንባታውን ዓለም አቀፉ 'ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ' እያከናወነ ይገኛል።

ለግንባታው የሚውለው 1,925,451, 264.41 (አንድ ቢሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን አራት መቶ ሃምሳ አንድ ሺህ) ብር በፌደራል መንግስት ነው የሚሸፈነው። 'ፕሮሚናንት ኢንጅነሪንግ ሶሉሽንስ' ግንባታውን የመቆጣጠር እና የማማከር ሥራ እየሠራ ይገኛል።

አካባቢው ካለው በርካታ አገራዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንፃር በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ነው እየተገነባ የሚገኘው፡፡

በፕሮጀክቱ የከተማ ክልል ላይ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር በግንባታ ሥራው ላይ እክል ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፥ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከወረዳ የመስተዳድር አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን መፍታት ተችሏል፡፡

ከዚህም ባለፈ የአካባቢው አስቸጋሪ የመልካ-ምድራዊ አቀማመጥ እንዲሁም የግንባታ ዕቃዎች የግብዓት ዕጥረት እና የዋጋ መናር በግንባታው ወቅት የገጠሙ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

የእስቴ-ስማዳ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ 657 ኪ.ሜ ርቀት እስቴ ከተማ ላይ ጀምሮ ወገዳ ከተማ ድረስ ይዘልቃል፡፡

ፕሮጀክቱ ዕውን ሲሆን በሥፍራው የሚገኙትን ትንንሽ መንደሮች ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በማገናኘት ወደ ከተማ የሚያድጉበትን ምቹ ዕድል ይፈጥራል፡፡የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን በማሳለጥም የተለያዩ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን ያጠናክራል፡፡

በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ሽንብራ፣ ኑግ፣ ባቄላ፣ ጓያ፣ ድንች እና መሰል የግብርና ምርቶች ገበያ በፍጥነት እና በጥራት ማድረስ ያስችላል፡፡

Via ERA

@etconp