Get Mystery Box with random crypto!

የምግብ ድጋፍ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ የጃፓን መንግስት ለኢትዮጵያ የ 57ሺ ኩንታል የጃፓን | Ethiopian Trading Businesses Corporation (ETBC)

የምግብ ድጋፍ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ

የጃፓን መንግስት ለኢትዮጵያ የ 57ሺ ኩንታል የጃፓን ሩዝ ድጋፍ አደረገ፡፡ የምግብ ድጋፍ ርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ግንቦት 08/ 2015 ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ የፍጆታ እቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ ቃሊቲ ሽያጭ ማእከል የተካሄደ ሲሆን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስታት ትብብር ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ግርማ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ሰመሪታ ሰዋሰው የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ጃፓን የቆየ የኢኮኖሚ ትብብር እንዳላቸው ጠቅሰው በጃፓን መንግስት የተደረገው የምግብ ድጋፍ የሀገራቱን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የተደረገው የ57 ሺ ኩንታል የሩዝ ምግብ ድጋፍ 300 ሚሊየን ብር እንደሚገመት ጠቁመዋል፡፡

ኢቶ ታካኮ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ባስተላለፉት መልእክት የርክክብ ሥነ-ሥርዓቱን ላስተባበሩት የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን መንግስታቸው የኢትዮጵያን ህዝብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዝ ተከታታይነት ያለው ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ድጋፉ በኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኩል ለኅብረተሰቡ በተቻለ ፍጥነት እንደሚሰራጭ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

አቶ ቶውፊቅ ይመር በኮርፖሬሽኑ የፍጆታ እቃዎች ን/ስ/ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ በምግብ ድጋፍ ርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ለተገኙት እንግዶችና የሚዲያ አካላት በፍጆታ እቃዎች ን/ስ/ ዘርፍ የቃሊቲ ሽያጭ ማእከልን ያስጎበኙና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ኮርፖሬሽኑ የምግብ ድጋፉን በአግባቡ ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት የሚያስችል አቅምና ልምድ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር መጠነኛ የሆነ የመሸጫ ተመን እንደሚወጣለት ገልጸው፣ በሸማች ህብረት ስራ ማኅበራት በኩል ለኅብረተሰቡ እንደሚደርስ ጠቁመዋል፡፡