Get Mystery Box with random crypto!

'በከፍተኛ ትዕግስት ስናልፋቸው የነበሩ አባቶች ዛሬም ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው ቤተክርስቲያንን ሲ | ሰበር ዜና ET🇪🇹

"በከፍተኛ ትዕግስት ስናልፋቸው የነበሩ አባቶች ዛሬም ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው ቤተክርስቲያንን ሲገፉ በዝምታ የምናይበት ሂደት አይኖርም፡፡"
ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግርን ለመቅረፍ  በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው ዐብይ ኮሚቴ በኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ሂደት ላይ መግለጫ አወጣ።

በአለፉት ሁለት ሦስት ቀናት በአባቶች ዘንድ ውይይት ተደርጎበት ስምምነት ላይ ሳይደረስበት የቀረው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ሂደትን አስመልክቶ በተደረገው  ውይይት ላይ በአባቶች የተፈጠረው  የሐሳብ መከፋፈልና አለመግባባት ሁኔታ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ለኮሚቴው በእጅጉ እያሳሰበው ይገኛል ሲል ከ10 በላይ ማኅበራትን የወከለው ኮሚቴው በመግለጫው ጠቅሷል።

በየጊዜው በሚነሱ ወሳኝ የቅድስት ቤተክርስቲያን አጀንዳዎች ውስጥ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ጀርባቸውን የሚሰጡ፣ በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው ዓለማዊ አጀንዳ የሚያራምዱና ከዛሬ ነገ የቤተክርስቲያንን ፍቅርና ምህረት ተረድተው ወደልባቸው ይመለሳሉ በማለት በከፍተኛ ትዕግስት ስናልፋቸው የነበሩ አባቶች ዛሬም ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው ቤተክርስቲያንን ሲገፉ በዝምታ የምናይበት ሂደት አይኖርም ያለው ኮሚቴው በዚህ ታሪካዊ ወቅት ለቅድስት ቤተክርስቲያን መቆም ሲገባችሁ እየሰማችሁ እንዳልሰማችሁ ሆናችሁ በዝምታ የምትመለከቱ አባቶችም ሆነ ዋነኛ የችግሩ አካላት የሆናችሁ አባቶች በእግዚአብሔርም በታሪክም በእኛም በልጆቻችሁ የሚያስጠይቃችሁ መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን ሲል አፅንዖት ሰጥቷል።

ቤተክርስቲያን ከማይጠፋ ዘር በክርስቶስ ደም የተመሠረተች እንጂ እንደ ፖለቲካ ምክር ቤት በዘር በጎሣ የተመሠረተች አይደለችም። ቤተክርስቲያን የሁሉም ለሁሉም ነች ያለው ዐብይ ኮሚቴው ዛሬ በወከባና በጫና ለተለየ ብሔርና ጎሣ ተለይቶ የኢጲስ ቆጶስ ሲመት ቢሰጥ ነገ በዚህ ሰበብ ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈል ዘርና ቋንቋን መሠረት አድርጎ የሚከተለውን ጥያቄና በጥንታዊት  ሐዋርያዊት ዓለም አቀፋዊት አንዲት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ የተነጣጠረውን የፈተና እና የመከራ ማእበል መመለስም መዳኘትም ይከብዳል ብሏል።

ይህን ጽንፍ የወጣ አጀንዳ በድምጽ ብልጫ በማስወሰን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን እና ቀኖናን በመጣስ መፍትሔ የሚያመጡ መስሎአቸው የሚተጉ አባቶችም ቤተክርስቲያንን ወደማትወጣው መከራና ፈተና እየገፏት እንደሆነ ሊረዱት ይገባል ብለን እናምናለን።

በዚህ መግለጫ ብፀዓን አባቶችንን በታላቅ ትህትና ዐቢይ ኮሚቴው ማሳሰብ የሚፈልገው ይህ አጀንዳ አስተዳደራዊ ሳይሆን ሃይማኖታዊ/ዶግማዊ እና ሥርዓታዊ/ቀኖናዊ አጀንዳ በመሆኑ በሕገ ቅድስት ቤተክርስቲያን አንቀፅ 19፡ 5፡ ሐ መሰረት በሙሉ ድምጽ እንጂ በድምፅ ብልጫ ስምምነት ተደርጎበት ውሳኔ ላይ ሊደረስ የማይገባው አጀንዳ መሆኑንም ኮሚቴው በሚገባ ያምናል፡፡

በተለይም ይህ አለመግባባት እየሰፋ መጥቶ ውሳኔው በድምጽ ብልጫ የሚደረግ ከሆነ ሕገ ቤተክርስቲያንን እና ቀኖና ጥሰትን ስለሚያመጣ፤ ውጤቱም በብፁዓን አባቶች መካከል ያለውን መከፋፈል አስፍቶ ቤተክርስቲያንን ወደ ከባድ ፈተና የሚያደርስ ጉዳይ በመሆኑ ብፁዓን አባቶች በፍፁም መከባበር፤ ምድራዊ እና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ፍጹም ጸያፍ እና የተወገዙ በሆኑ ጉዳዮች፣ዘርን፣ ቋንቋን፣ ጎጥን ፖለቲካን፣የግል ጥቅምንና ፍላጎትን ሳይሆን የረቂቃኑ እና ግዙፋኑ፤ የሰማያውያን እና የምድራውያን ልዩ ጉባኤ፤አንዲት የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ማዕከል በማድረግ ብቻ አንድ ልብ አንድ ሐሳብ ሆናችሁ በእርጋታ በመነጋገር ለቅድስት ቤተክርስቲያን የሚጠቅም ውሳኔ በአንድ ድምፅ ሰጥታችሁ እንደምትወጡና የአሁኑንም ሆነ የሚመጣውንም ትውልድ የመከራ ቀንበር እንደምታቀሉ ባለሙሉ ተስፋ ነን፡፡

መግለጫው ከቅዱስ ሲኖዶስ የምንጠብሸው ውጤት በማለት ዐራት ነጥቦችን ዘርዝሯል።

0ቢይ ኮሚቴው በጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ከተከናወነው  ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ጋር በተያያዘ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተጋረጠው አደጋ መነሻ አድርጎ የተቋቋመ ሲሆን ከ10 በላይ ማኅበራትን ማለትም ከሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት፣ ከነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የምዕመናን ኅብረት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ጴጥሮሳውያን ኀብረት፣ የጎልማሶች እና ወጣቶች ማኅበር፣ ከወልዳ ዳንዲ አቦቲ፣ ከደጆችሽ አይዘጉ ማኅበር፣ ከሕግ ባለሙያዎች እንዲሁም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተለያዩ መምሪያዎች የተወጣጣ ነው።
ማህበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን

ለጥቆማና ማስታወቂያ ለማሰራት
    @Dani_peromotor
  

@ET_SEBER_ZENA
@ET_SEBER_ZENA