Get Mystery Box with random crypto!

“ ህወሓት የፕሪቶርያውን ስምምነት በግልፅ በመጣስ ራያ ላይ ጦርነት ከፍቷል ” - የአላማጣና አካባ | ኢሳት(ትኩስ ትኩስ ዜናዎች)

ህወሓት የፕሪቶርያውን ስምምነት በግልፅ በመጣስ ራያ ላይ ጦርነት ከፍቷል ” - የአላማጣና አካባቢው አመራር
የትግራይ እና አማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ከሚያነሱበት አንዱ በሆነው ራያ አላማጣ አካባቢ ትላንትና " ህወሓት " ተኩስ መክፈቱን፣ በዚህም በሰው ሕይወት ላይ ሞትና የአካል ጉዳት ሙድረሱን አካባቢውን ከሚያስተዳድሩ አመራሮች (ባለስልጣን) አንደኛው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

አንድ የአካባቢው አመራር (ባለስልጣን) ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ “ ራያ ላይ  አዲስ ነገር አለ። ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በግልፅ በመጣስ ራያ ላይ ጦርነት ከፍቷል ” ብለዋል።

“ ቀን ላይ አንድ ሰው ሕይወቱ አልፏል። ሁለት ቆስለው ወደ ደሴ ሪፈር ተብለዋል። ደንበሩን በማለፍ የራያ አላማጣ ወረዳ አዳዲስ ቀበሌዎች ተቆጣጥሯል ” ሲሉ አክለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጦርነቱ የተከፈተው በምን ሰዓት ነው ? በዬት በኩል ነው የተከፈተው ? አሁን ተኩስ አለ ? በቁጥጥር ስር የሆኑት ቀበሌዎች እነማን ናቸው ? ከሰሞኑን ለጦርነት አመላካች ጉዳዮች ነበሩ ? ሲል ለአመራሩ ጥየቄ አቅርቧል።

አመራሩም ፣ “ ጦርነቱን የጀመሩት ሰኞ ሌሊት 6:00 አከባቢ ሲሆን፣ እስከ ቀን 6:30 ድረስ ነበር። መከላከያ ለራያ ምሊሻ ‘ወደ ኋላ ተመለሱ እነርሱም ይመለሳሉ’ በማለቱ ምክንያት ጦርነቱ ቁሞ የራያ ምሊሻ ወደ ኋላ ቢልም TDF መልሶ ቦታውን ተቆጣጥሮታል ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ተኩሱ የተጀመረበትን ልዩ ቦታ በተመለተ በሰጡት ምላሽም ፣ “ የተጀመረበት ቦታው ‘ጮጓራ’ ይባላል። የራያ አላማጣ ቦታ ነው። አሁንም እሱን በማለፍ ወደ ‘ኮስም’ የሚባል አከባቢ እየተጠጉ ነው። ተጨማሪ ኃይልም እያስጠጉ ይገኛሉ ” ብለዋል።

የአካባቢው አመራር የተኩሱን መነሻ በገለጹበት አውድ ፣ “ የዚህ ዋናው መንስኤ አማራ ክልል #ወልቃይት እና #ራያ በስርዓተ ትምህርቱ ካርታ ላይ ተካተዋል በሚል በወጣው መግለጫ ነው ” ሲሉ አስረድተዋል።

“ የራያ ህዝብ የዘመናት ትግሉ በህጋዊ መንገድ ፍትህ ማግኘት እንጂ ጦርነት አይፈልግም። እነሱ እየተከተሉ ደጋግመው እያቆሰሉት ነው ” ሲሉም አክለዋል።

በህወሓት ተከፈተ ስለተባለው ተኩስ በትግራይ ክልል በኩል እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በትግራይ ያሉ አስታዳዳሪዎችን አግኝቶ የነበረ ሲሆን ስብሰባ ላይ እንደሆኑና ወደ በኃላ ማብራሪያ እንደሚሰጡን ገልጸዋል።

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ “ የአማራ ክልል የትግራይ መሬት በካርታው በማስፈር የትምህርቱ ሰርዓቱ አካል በማድረግ እያስተማረበት ይገኛል " ማለቱ አይዘነጋም።

አስተዳደሩ ፤ በአማራ ክልል መንግሥት በኩል በትግራይ ህዝብ ላይ ግፍ እና በደል ሲፈፀም እንደቆየ አሁንም እንደቀጠለ ገልጾ ክልሉ የሰላም ስምምነቱን የሚያናጋ ጠብ አጫሪ ተግባራትን እየፈፀመ እንደሆነ ከሶ ነበር።

የፌደራል መንግስት በካርታው ላይ ምንም አይነት እርማት እንዳልሰጠ ፣ የአማራ ሕዝብም ሆነ ሌለው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጊዚያዊ አስተዳደሩ ጎን እንዲቆሙ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለሚከተለው ነገር ሁሉ ግን የአማራ ክልል ሙሉውን ኃላፊነት ይወስዳል " ሲል አስጠንቅቆ ነበር።

@esatchannal