Get Mystery Box with random crypto!

​​አቶ በቴ ኡርጌሳ በበርካታ ጥይት ተደብድበዉ ህይወታቸዉን እንዳጡ የህክምና ባለሙያ ተናገሩ በ | ESAT (ኢሳት🇪🇹)®

​​አቶ በቴ ኡርጌሳ በበርካታ ጥይት ተደብድበዉ ህይወታቸዉን እንዳጡ የህክምና ባለሙያ ተናገሩ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ውስጥ በምትገኘው የትውልድ ከተማቸው መቂ ረቡዕ ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም. ተገድለው የተገኙት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ በበርካታ ጥይት መመታታቸውን የሕክምና ባለሙያ እና የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ገለጹ።

አስከሬናቸው ከመቂ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቆሻሻ መጣያ አካባቢ የተገኘው አቶ በቴ ኡርጌሳ፣ ጭንቅላት ላይ አምስት በጥይት ምት የተፈጠሩ ጉዳቶችን መመልከታቸውን ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሕክምና ባለሙያ ተናግረዋል።

“ጭንቅላቱ ላይ አምስት ቁስለት፣ ወገቡ ላይ ሦስት ቦታ፣ በግራ ጎኑ አንድ ትልቅ ጉዳት፣ ከወገቡ ወደታች እና ታፋው ላይም ተጨማሪ አንዳንድ ጉዳት በአጠቃላይ 11 የሚሆኑ ቁስለቶች ታይተዋል።”

የሕክምና ባለሙያው ሁሉም ጉዳቶች በጥይት የተፈጠሩ መሆን አለመሆናቸውን የተጠየቁ ሲሆን፣ “ለእኛ እንደዚያ ይመስላሉ። ገሚሶቹ ጥይቱ በገባበት የተፈጠሩ፣ ገሚሶቹ ደግሞ ጥይቱ የወጣበት ቦታዎች ላይ የሚገኙ ሊሆኑ ይችላሉ። ሁሉም ጥይት የገባበት ነው ማለት አይደለም” ብለዋል።

እኚሁ ባለሙያ አቶ በቴ ጭንቅላታቸው ላይ አምስት ጉዳቶች ቢኖሩም፣ ፊታቸው ላይ ግን ምንም ዓይነት ጉዳት አለመመልከታቸውን ተናግረዋል።

በአቶ በቴ አስከሬን ላይ የፎረንሲክ ምርመራ እንዳልተካሄደ ገልጸውም “በሰውነታቸው ላይ የቀረ ጥይት መኖር አለመኖሩን መለየት ይከብዳል” ሲሉ ለቢቢሲ መናገራቸውን ከዘገባው ተመልክቷል። የህክምና ባለሙያው ጨምረውም “ጭንቅላታቸው ላይ የታየው አምስት ጉዳት ግን ሰውነታቸው ውስጥ የቀረ ጥይት መኖሩን ጥርጣሬ ይፈጥራል” ብለዋል።

የፖለቲከኛውን ግድያ ተከትሎ የተለያዩ መላምቶች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል በፖለቲከኛው ግድያ ላይ የመንግሥት ኃይሎች አሉበት መባሉን ውድቅ አድርጓል።

የአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ላይ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካል ምርመራ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲፈቅዱ አሜሪካ ጠይቃለች። የኦሮምያ ክልል መንግሥት በመቂ ከተማ አስከሬናቸው ተጥሎ የተገኙት ፖለቲከኛ የተገደሉት “ባልታወቁ ጥቃት አድራሾች” እንደሆነ ገልጿል።

የአቶ በቴ ኡርጌሳ ቤተሰብ አባል የሆኑ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ረቡዕ ጠዋት ከነዋሪዎች ባገኙት መረጃ መሠረት፣ ሁለት ሰዓት አካባቢ አስከሬኑን ማግኘታቸውን ተናግረዋል። እኚሁ የቤተሰብ አባል አስከሬኑን ሲያገኙት አካሉ ብዙ ቦታዎች ላይ ቆስሎ መመልከታቸውንም ገልጸዋል።

“አካሉ ላይ የተገኙትን ጉዳቶች ትክክለኛ ቁጥር የአስከሬን ምርመራ ውጤት ነው የሚያሳየው። ቢያንስ በስድስት ጥይቶች መመታቱን ግን ፎቶዎች ተነስተው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተለቀቁት ማየት ችለናል።

የመቂ ከተማ ከንቲባ አቶ ዲልቦ ኡርጌሳ ለአሜሪካ ድምጽ በሰጡት ቃለ ምልልስ ግድያው የተፈጸመው ቤተሰብ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን ገልጸው፣ ጉዳዩን ለማጣራት ምርመራ እንደሚያደረግ ተናግረው ነበር።

የአቶ በቴ የቤተሰብ አባል ግን ምንም ዓይነት የቤተሰብ አለመግባባት እንደሌለ ተናግረው “ሐቁ እንዳይወጣ መንገድ ለማሳት፣ ሕዝብ መሃልም መደናገር ለመፍጠር ያለመ ነው” ሲሉ አስተባብለዋል። “እርሱን ገድለው ያልጠገቡ፣ እውነቱን ለማጥፋት የፈለጉ” ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ቢቢሲ አማርኛ

@Esat_tv1
@Esat_tv1