Get Mystery Box with random crypto!

ጾሙ ከተጀመረም በኋላ ሕዝቡ ወደ አምላኩ እንዳይጮህ እና እንዳይጸልይ ለማወክ የሕዝብ አስተዳዳሪ ሆ | ፍኖተ-ወራዙት ዘኦርቶዶክስ ⛪

ጾሙ ከተጀመረም በኋላ ሕዝቡ ወደ አምላኩ እንዳይጮህ እና እንዳይጸልይ ለማወክ የሕዝብ አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙ የመንግሥት ሹማምንት ሊያገለግሉት ኃላፊነት የተቀበሉበትን የሀገሪቱን ሕግ ጥሰው ምእመናን ልጆቻችን ጥቁር ለብሰው ወደ መሥሪያ ቤት እንዳይገቡና በመንግሥት ቢሮዎችም አገልግሎት እንዳያገኙ በተለይም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና አንዳንድ በፌዴራል እና በከተማ መስተዳድር ቢሮዎች ጥቁር የለበሱ እና በሀዘን ላይ ያሉ ልጆቻችንን በማሠር ሲያንገላቱ በዓይናቸው ያዩ ምስክሮች አረጋግጠውልናል፡፡ በዚህም ሹማምንት ስልጣናቸውን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት እየተጠቀሙበት መሆኑን እና ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ከፍተኛ ንቀት እና ጥላቻ ያላቸው መሆኑን ተረድተናል፡፡
ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው መከራና በደል በዚህ ዘመን በጉልህ የሚጠቀስ የቤተ ክርስቲያን የስደትና የመከራ ጊዜ ነው፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያን የስደትና የመከራ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ መዝገብ እና በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ ይቀመጣል፡፡ ለትውልድም ይተላለፋል፡፡ ይህ የፈተና ዘመን ያልፋል፤ ነገር ግን በዚህ ታሪክ ውስጥ ከእውነት ጎን የቆማችሁ ስማችሁ በታሪክ እና በወርቅ ቀለም ሲፃፍ በቤተክርስቲያን ላይ መከራ ያበዛችሁ ክፉ ታሪካችሁን ዛሬ በእጃችሁ ጽፋችሁ አልፋችኋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጭ ሌሎች የክልል ርዕሳን መስተዳድሮችና ከተሞች በተለይም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፤ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት፤ የሱማሌ ክልላዊ መንግሥት፤ የቤንሻንጉል ክልላዊ መንግሥት፣ የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት፣ የአፋርና ጋምቤላ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፤ በጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ እና ሌሎች ስማቸውን ያልጠቀስናቸው መንግሥታዊ ተቋማት የቤተ ክርስቲያናችንን ጥሪ በመከተል በአግባቡ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር የወሰዳችሁ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ መፍትሔዎችን እናደንቃለን፣ በቤተ ክርስቲያንም ስም እናመሰግናለን፡፡ እንዲሁም ሀዘናችሁ ሀዘናችን ነው ብላችሁ ከጎናችን የተሰለፋችሁ አኃት አብያተ ክርስቲያናት፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ጉባኤያት፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች፤ በእምነት የማትመስሉን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ስላደረጋችሁልንና ስለምታደርጉልን እርዳታና ትብብር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም እናመሰግናለን፡፡
ጸሎተ ምሕላውን ስናውጅ መንግሥት ሕግ አክብሮ እንዲያስከብር፣ የቤተክርስቲያኒቱን ክብር እና ልዕልና እንዲያከብር፣ በሃይማኖታችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆምና ወደ ውስጡ ማየት እንዲችል ነበር:: ይህ ድርጊት እስከ አሁን ድረስ ግን መንግሥት ለዘመናት ሕጋዊ ተቋም እና የሀገር ባለውለታ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ከመስማት እና ችግሯን ከመቅረፍ ይልቅ የማዋከቡን ሥራ አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ በዚህም መንግሥት ችግሮችን ኃላፊነት ተሰምቶት እንዲፈታ ያደርገዋል የሚል እምነት ቢኖረንም አገዛዙ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ልቡ መደንደኑን መመልከታችን በእጅጉ ልባችንን ሰብሮታል፡፡
በተለይም ቤተ ክርስቲያናችን ያወጀችው የ፫ ቀናት ጸሎትና ምህላ በአግባቡ እንኳን ሳይጠናቀቅ ከመንግሥት ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይን አስመልክቶ በየካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የተሰጠው የሰልፍ ክልከላ መግለጫ መንግሥት አሁንም ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማውደምና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት የታወጀ አዋጅ መሆኑን በጽኑ እንድናምን አድርጎናል፡፡
በመግለጫውም፡-
፩ኛ. በእምነቱ አባቶች በተመሳሳይ መልኩ ሰልፍ ተጠርቷል በማለት መጥቀሱ የቤተክርስቲያን የመጨረሻው አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ የለያቸውን አካላት የእምነቱ ተከታይ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መብት ያላቸው ሕጋዊ አካላትና የቤተ ክርስቲያን አባቶች አድርጎ መጥራቱ አሁንም ላይ ማብራርያ ለመስጠት መሞከሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር የሚነካ እና የሚያጠለሽ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን ከማስከበር ይልቅ ለሕገ ወጦች ጠበቃ ሆኖ የሚከራከረው መንግሥት መሆኑን ጭምር ለመረዳት ችለናል፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያን በመንግሥት የደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ተሰጠ የተባለው መግለጫ የቤተ ክርስቲያናችንን ሕጋዊ መብት የገፈፈ እና ሕገ ወጥ መግለጫ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፡፡
፪ኛ. ጉዳዩን የውጪ እና የውስጥ ጠላቶች የፈጠሩት ነው በማለት የተለመደውን ፖለቲካዊ ቅርፅ ለማስያዝ መሞከርም ቤተክርስቲንያንም ሆነ ሕዝብን መናቅ በመሆኑ የምንቀበለው አይሆንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ላለፉት ፬ ዓመታት በሀሰተኛ ትርክት ልጆቿ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል መከራን ሲቀበሉ ችግሮችን በሆደ ሰፊነት ችላ ያለፈችው የሀገር መሠረት እንዳይናጋ፣ ቅጥሯ እንዳይደፈር በማሰብና በሀገር አንድነት ላይ ባላት የማይናወጽ ጽኑ አቋም ምክንያት መሆኑን መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ጉዳዩ ግልፅ የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሆኖ እያለና መፍትሄውም በመንግሥት እጅ የሚገኝ ብቻ መሆኑ እየታወቀ የፖለቲካ ቅርፅ ለማስያዝ መሞከር ችግሩን ያባብሰው እንደሆን እንጂ አይፈታውም፡፡
በሰሞኑም ቤተ ክርስቲያናችን በመዋቅር የምትመራ እና ልጆቿም ድምጽዋን አውቀው በአግባቡ የሚሰሟት መሆኑ እየታወቀ ሆነ ተብሎ ቃላት አጠቃቀሙ እንኳን ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ የሀሰት እና ጸብ አጫሪ የሆኑ መልእክቶችን በአደባባይ የተለጠፉ መሆናቸውን ሲታይ ምን ያህል ጉዳዩን ላልተገባ ፖለቲካዊ ጥቅም እንደተፈለገ ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህ ተለጠፈ የተባለውም ሕገ ወጥ ጽሑፍ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያልሆነና ፈጽሞም ሊሆን የማይችል መሆኑን ጭምር ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
፫ኛ. የትኛውም ሰልፍ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ማድረግ አይቻልም በማለት የተደረገው ክልከላን በተመለከተም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ውስጥ መሠረታዊ መብት ሆኖ የተጠቀሰ እና በሕገ መንግሥቱም አንቀፅ ፴ ላይ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ መንግሥት ራሱ የሚመራበትን ሕገ መንግሥት ማክበርና ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከላይ የተጠቀሰው ከፍተኛ መከራና በደል ምክንያት ከብዙ ሺህ ዓመታት በላይ ጸንታ የመጣችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በእኛ በልጆቿ ዘመን ስትፈርስ ዝም ብሎ መመልከት በጭራሽ የሚታሰብ አይሆንም፡፡
ይህን በደላችንን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለማሳወቅ እና መንግሥትም ከሚያደርገው ጣልቃ ገብነትና አፈና ወጥቶ ሕግ እንዲያከብር እና እንዲያስከብር የጠራነው የየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍም መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ እንድናከናውን መፍቀድ አሊያም የጠየቅናቸውን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎቻችንን በአግባቡ እና አንድ በአንድ መመለስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ደግመን ደጋግመን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥም የሚደርስብንን ሞት፣ መከራና ስደት እኛ አባቶች ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ጋር ደስ ብሎን የምንቀበለው እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን እና ሀገራችን ስትፈርስ ቆመን የምንመለከት፣ ዝም የሚል አንደበትና የሚሸከም ኀሊና የማይኖረን መሆኑን በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡