Get Mystery Box with random crypto!

“ሰላማዊ ሰልፉን በተመለከተም በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝርዝር መግለጫ እንሰጣለን፡፡” ቅዱስ ሲኖዶስ | ፍኖተ-ወራዙት ዘኦርቶዶክስ ⛪

“ሰላማዊ ሰልፉን በተመለከተም በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝርዝር መግለጫ እንሰጣለን፡፡” ቅዱስ ሲኖዶስ

በስመ አብ፤ ወወልድ፤ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥር ፳፱ እስከ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለ ፫ ተከታታይ ቀናት በመላው ዓለም የታወጀው የነነዌ ፆም እና ምሕላ መጠናቀቅን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ::
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
በትንቢተ ዮናስ በሰፊው እንደተጠቀሰው የነነዌ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ላይ ስለአመጹ እና ግብራቸውም በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊ በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ዮናስን “ተነስተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ ክፋታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቷልና በእርስዋ ላይ ስበክ” በማለት አዘዘው፡፡ ትንቢተ ዮናስ ምዕ ፩ ቁጥር ፪ ዮናስም ድምፁን ከፍ አድርጎ ለነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰብክ “የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡ ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነስቶ መጎናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ፡፡ አዋጅም አስነገረ፤ በነነዌ ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፤ እንዲህም አለ ሰዎችና እንስሶች፤ ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፣ አይሰማሩ፣ ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፣ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ጩኸት ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ፡፡ እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደሆነ ማን ያውቃል፡፡ እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውንም አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም” ትንቢተ ዮናስ ፫፡ ፭-፲
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህን የነነዌ ሰዎች ፆም መነሻ በማድረግ የነነዌ ሰዎችን በምሕረቱ የጎበኘ አምላክ እኛንም በምሕረቱ ይቅር ይለን ዘንድ በየዓመቱ በአዋጅ በመፆም አምላካችንን ስንማጸንበት ኖረናል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባዔ በጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በወሰነው መሠረት የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የተጠናቀቀው የነነዌ ፆምና ምሕላ ልዩ በሆነ በመንፈሳዊ የንስሐ ጸሎት በሰላም ተጠናቋል፡፡
በምሕላውም ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ጀምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ካህናት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ አገልጋዮች እና ምእመናን እንደነነዌ ሰዎች ጥቁር ለብሰን ጠዋትና ማታ በጸሎት ፤ በምሕላ፤ ቀን በቅዳሴ እንዲሁም በሰባቱ የጸሎት ጊዜያት ፈጣሪያችንን ስንለምን እና ስንማጸን የቆየንበት ምክንያት በቤተክርስቲያናችን ላይ የመጣው ፈተና እጅግ በጣም ከባድ በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ የጾምና የንስሐ ወቅት ምእመናን ልጆቻችን የአባቶቻችሁን ጥሪ ሰምታችሁ፤ የሹመኞችን ማዋክብና እስር ሳትፈሩ ጥቁር ለብሳችሁ ጠዋትና ማታ በጾምና በምሕላ፣ ቀን በቅዳሴ በቤተክርስቲያን ቅጥር እየተገኛችሁ ለአምላካችን ያቀረባችሁትን ጸሎት እና ምሕላ እግዚአብሔር ሰምቶ ለችግራችን መፍትሄ፣ ለሀገራችን ሰላምን እንደሚሰጠን እምነታችን ጽኑ ነው፡፡ እናንተም ምእመናን የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ሰምታችሁ ለሃይማኖታችሁ፣ ለሀገራችሁ አንድነትና ሰላም ያላችሁን ጥልቅ ፍቅር ስለገለፃችሁም ያገኘነው መንፈሳዊ ብርታት ሳንገልፅላችሁ አናልፍም፡፡
በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም እና በቅዱሳን አማላጅነት፣ በመላእክት ተራዳኢነት በፍፁም ፍቅርና አንድነት የያዝነውን ጸሎት እና ምሕላ አጠናቀናል፡፡ ችግራችንን ለአምላካችን በለቅሶ እና በጩኸት ነግረናል፡፡ ከዚህ በኋላ መከራው ቢጸና፣ የመከራው ጊዜ እንኳን ቢረዝም እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ ሊያፀናን እና ሊያበረታታን አስቦ በመሆኑ በፍፁም አንናወጽም፡፡ ከእነኚህ መከራዎች በኃላም ታሪክን ጽፈን ሃይማኖታችንን ጠብቀን እና አስጠብቀን በመንፈሳዊ ጽናት እና ተጋድሎ እንሻገራለን፡፡
ጥቃቱ የቤተ ክርስቲያንን እውነት በካዱና በእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን መካከል ነው፡፡ ይህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖት፤ ቀኖና እና አስተዳደራዊ ሕግጋትን ጥሰው ሕገወጥ የጳጳሳት ሢመት በመደረጉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ይህን ጥሰት የፈፀሙትን ግለሰቦች አውግዛ ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት የለየቻቸው ቢሆንም ጉዳዩ ከግለሰቦቹ በላይ በመንግሥት ስልጣን ላይ ባሉና ጽንፈኛ በሆኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሌላ እምነት ተከታዮች ጭምር የሚደገፍ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡
እየተፈጸመ ያለው ድርጊት በሰማያዊ መንፈሳዊ ዓለምና በምድራዊ ሥጋዊ ዓለም መካከል ስለሆነ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም የቤተ ክርስቲያን ክብርና ተቋማዊ ልዕልና ተደፍሯል፡፡ የቤተክርስቲያን ቅጥሮች መሣሪያ በያዙ አካላትና በመንግሥት የጸጥታ መዋቅር በኃይልና በጉልበት ተወሯል፡፡ ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት አህጉረ ስብከት ያለአንዳች የሕግ መሠረት በጸጥታ መዋቅሮች ተባረዋል፡፡ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቶቻቸው ተገድቦም በግዞት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ ወደ አህጉረ ስብከታቸውም ተመልሰው መግባት እንዳይችሉ እቀባ ተደርጎባቸዋል፡፡ ካህናት አባቶች እና ምእመናንም ያለአንዳች የሕግ መሠረት በየእስር ቤቱ ያለበቂ ምክንያት በሕገወጥ መንገድ ታጉረዋል፡፡ በጸጥታ ኃይል ከመጠን በላይ ከመደብደባቸው የተነሳ የሞት፣ የከባድ እና ቀላል አካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ በአጠቃላይም በመንግሥት ኃይሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ይህ ሁሉ በደል ቢፈጸምባትም ናዛዜ ሕዙናን የሆነው አምላካችን ለቤተ ክርስቲያናችን እና ለሀገራችን መፍትሔ እንዲያመጣልን፣ መንግሥትም ወደ ልቡ ተመልሶ ቤተክርስቲያንን እንዲያከብርና እንዲጠብቅ በሚል ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ይህን ጾም የነነዌ ሰዎች እንዳደረጉት ጥቁር ለብሰን በፍፁም ኃዘን ወደ አምላካችን እንድንጮህ ቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝ ባስተላለፈበት ማግስት በሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሕገወጡን ቡድን በኃይል ለማስገባት በመንግሥት የጸጥታ መዋቅሮች በተወሰደ አሰቃቂ እርምጃ እስከ አሁን በደረሰን መረጃ ቁጥራቸው ከ፴ በላይ የሚሆኑ ካህናትን እና አገልጋዮችን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ቅጥሯ አይደፈርም፣ ቤተክርስቲያን በተወገዙ ግለሰቦች አትረክስም በሚል ለሃይማኖታቸው ሰማእትነትን ተቀብለዋል፡፡ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ልጆቿም በደረሰባቸው ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ምክንያት በሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ በደል በኋላም እስከ አሁን ድረስ የሞቱትን በአግባቡ መቅበርና የተጎዱትን በበቂ ሁኔታ ማሳከም ሳንችል ቀርተናል፡፡ እነዚህ ሰማዕታት በዚህ ኃጢያት በበዛበት ዘመን ለቤተክርስቲያን እስከሞት ድረስ በመታመን ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን የጽናት ተምሳሌት በመሆናቸው ቤተክርስቲያን ስትዘክራቸው ትኖራለች፡፡ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን በልጆቿ ላይ እየደረሰ ባለው ሞት፤ እርዛት፤ እስራት እና መልከ ብዙ በሆነው መከራ ብታዝንም ለክርስትና እውነተኛነት ምስክሮች የሆኑ አዳዲስ ቅዱሳን ሰማእታትን በማግኘቷም እጅግ ደስ ትሰኛለች፡፡