Get Mystery Box with random crypto!

#የቅዳሴ ጠበል«ጸበል»ለማን 1_የቅዳሴ ጠበል መጠጣት ለማን ይፈቀዳል? 2_የቅዳሴ ጠበል ከማየ | እኔስ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

#የቅዳሴ ጠበል«ጸበል»ለማን

1_የቅዳሴ ጠበል መጠጣት ለማን ይፈቀዳል?
2_የቅዳሴ ጠበል ከማየ ገቦ ይለያል?
ጥያቄ፡-የቅዳሴ ጠበል ሁሉም ምዕመን መጠጣት ይችላልን? ምክንያቱም አንዳንዶች የቆረበ ሰውና ደዌ ሕመም ያለበት ሰው ብቻ ነው መጠጣት ያለበት ሲሉ ሌሎች ደግሞ ቅዳሴ የገባ ሰው ሁሉ ባይቆርብም መጠጣት ይችላል ይላሉ ፡፡

ለመሆኑ የትኛው ነው ትክክል ;
• መልስ ፡- በቅድስት ቤተክርስቲያን ጠበልን በአራት ዓይነት መልክ እናገኛለን

1. ማየ ገቦ 《ልጅነት የምናገኝበት ጥምቀት》
2. ማየ ጸሎት ፡- በጸሎት የተቀደሰ ውኃ ሲሆን ካህናት በቤታችን የሚረጩን ፣ ካህናትና ምዕመናን ውኃ አድርገው ጸሎት ካደረሱ በኋላ ‹‹ እፍ ›› በማለት የሚያከብሩት የጠበል ዓይነት ነው ፡፡ በግብሩ በፊታችን በቤታችን . . . በመረጨቱ ማየ ምንዛኅ 《የሚረጭ ውኃ》 ተብሎ ይጠራል
3. በገዳማትና በአድባራት ዐጸድና ሰበካ በቅዱሳን ስም የሚፈልቅ ጠበል
4. የቅዳሴ ጠበል ፡- በጸሎተ ቅዳሴ የከበረ ፣ ከሌሎች ጠበላት ሁሉ የተለየ ጠበል ነው ፡፡ በመሆኑም ሥጋወ ወደሙ ከመቀበል ጋር በቅዳሴ ጠበል ዙሪያ የቀረቡልንን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲህ እናቀርባለን ፡፡

የቅዳሴ ጠበል አገልግሎት ሥጋውን ደሙን ለተቀበሉ ምዕመናን በአፋቸው ተጣብቆ ቀርቶ ወደ ውጭ እንዳይነጥብ ለማድረግ ነው ፡፡ ስለዚህም የተቀበሉ ሰዎች ቅዳሴ ጠበል እንዲጠጡ ይታደላቸዋል ፡፡
በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት ሥጋወ ወደሙ
መቀበል ያልተቻላቸው ሰዎች ቢኖሩ ሌሎች ሲቀበሉ ብቻ እያዩ እዳይመለሱ ንስሓ ገብተው ቀኖናቸውን ጨርሰው ሥጋወ ደሙን እስኪቀበሉ ድረስ ተስፋ እንዳይቆርጡ ቅዳሴ ጠበል ከደዌ ሥጋ እየተፈወሱ እዲቆዩ ለሥጋወ ወደሙ መቅድም እንዲሆናቸው የቅዳሴ ጠበል እንዲጠጡ ይቀዳላቸዋል ፡፡

የቅዳሴ ጠበል የሚጠጡት በ3 ዓይነት ወገን ከፍለን ብናይ

1. ሥጋውን ደሙን ለተቀበሉ
2. በደዌ ለተያዙ ሰዎች
3. ሥጋወ ወደሙ ለመቀበል ላልበቁ ነገር ግን በጸሎት ቅዳሴው ተሳታፊ ለነበሩት ሁሉ የሚጠቅም ነው ፡፡

ይሁን እንጂ ሁሉም ቅዳሴ ጠበል የሚጠጡበት ዓላማና የሚያገኙት ጥቅም የተለያየ ነው

የቅዳሴ ጠበል ከማየ ገቦ ይለያል?

አንዳንድ ሰዎች ቅዳሴ ጠበልን ከማየ ገቦ ጋር አንድ አድርገው ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ የቅዳሴ ጠበል ክብር ከማየ ገቦ ጋር አንድ እንደሆነ ይናገራሉ ፡፡

በመሠረቱ ሁለቱም አስተሳሰቦች ፈጽመው የተሳሳቱ ናቸው ፡፡ ምክንያቱም ማየ ገቦ በዕለተ ዓርብ
ሌንጊኖስ የተባለ ሐራዊ የጌታን ቀኝ ጎን በጦር ሲወጋው
በ‹‹ለ›› (ሐ) ፊደል ቅርጽ ከደም ጋር የወረደ ውኃ ነው ፡፡

ማየ ገቦ ማለትም ‹‹ የጎን ውኃ ›› ማለት ነው ፡፡ በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ማየ ገቦ ልጅነት የምናገኝበት ፣ መዝገበ ውሉድ የተባለች አማናዊት ጥምቀት አንዲት ናት አትከለስም አትደገምም የቅዳሴ ጠበል ግን ይደገማል በተጨማሪም የቅዳሴ ጠበል ማየ ገቦ አይባልም የምንለውም የልጅነት ጸጋ ስለማያሰጠን ነው ፡፡

የቅዳሴ ጠበል ማየ ገቦ ቢሆንማ ከቅዳሴ
በተለየ ጸሎት ለሕፃናት ሀብተወልድና ስመ ክርስትና ለመስጠት መጽሐፈ ክርስትናን መድገሙ ሥርዓተ ጥምቀት መፈጸሙ ባላስፈለገ ነበር ፡፡

አንድ ነው የሚሉት ወገኖች ምክንያታቸው
በሥርዓተ ቅዳሴ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለመለወጥ ካህኑ የሚለውን ኣሓዱ ኣብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ እንሚለው ሁሉ ልጅነት ሃብት የምናኝበት የክርስትና ጥምቀትንም ለመፈጸም መጽሐፈ ክርስትናን አድርሰው ውኃውን ወደ ማየ ገቦ ለመለወጥ ካህኑ የሚለውን አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ አንድ በማድረግ ነው ይህ ግን ስህተት ነው ሁለቱም ቃሉ
አንድ ይሁን እንጂ ከኋላቸው ያለው ጸሎት የተለያየ ስለሆነ አገልግሎቱም የተለያየ ነው ፡፡

አለበለዚያማ በየዓመቱ በ《ጥር 11 ቀን》 የጥምቀት በዓል ሲከበር ውኃውን ለመባረክ የሚደርሰው ጸሎት አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ
ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ስለተባለ ብቻ ጠበሉ ወደ ማየ ገቦነት ተለውጧል ካልን ቤተክርስቲያን ልጅቿን የልጅት ጥምቀት ታጠምቃለች ወደሚለው የተሳሳተ ድምዳሜ እንደርሳለን ፡፡

በ《ኤፌ 4፡5 》ጥምቀት አንዲት ናት ከሚለው
ትምህርተ ሃይማኖት ጋር የሚጋጭ ሃሳብ እናነሳለን ፡፡
ነገር ግን የቅዳሴ ጠበል የአምልኮት ማዕከል የሆነው ጸሎተ ቅዳሴ የደረሰበት በመሆኑ ልጅነትን ከምናገኝበት ከማየ ገቦ ጠበል ውጪ ከላይ ከዘረዘርናቸው ከሌሎች ጠበላት በእጅጉ የከበረ ነው ፡፡

ስለዚህ ጠበሉን መሬት ላይ ማፍሰስ በየቤታችን
ጥግ መድፋት ፈጽሞ የተከለከለ ነው ፡፡ ይቆየን