Get Mystery Box with random crypto!

ለቸኮለ ማለዳ! ሐሙስ ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የአሜሪካ ተራድዖ ድ | EMS Mereja

ለቸኮለ ማለዳ! ሐሙስ ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት ዩኤስአይዲ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር በድርጅታቸው ድጋፍ ትግራይ ውስጥ የሚካሄደው የምግብ ዕርዳታ ሥርጭት ላልተወሰነ ጊዜ እንደቆመ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ድርጅቱ በክልሉ የዕርዳታ ሥርጭት ያቋረጠው፣ የዕርዳታ እህል ከመጋዘን ተዘርፎ ገበያ ውስጥ እየተሸጠ መኾኑን መረዳቱን ተከትሎ ምርመራ በመጀመሩ እንደኾነ ፓዎር ገልጸዋል። የአሜሪካ መንግሥት ጉዳዩን ለፌደራልና ለክልሉ መንግሥት ማሳወቁንና ኹለቱም በምርመራውና ጥፋተኞችን ተጠያቂ በማድረግ ዙሪያ ከድርጅቱ ጋር ለመተባበር ፍቃደኛ መኾናቸው ተገልጧል። ዩኤስአይዲ የዕርዳታ አቅርቦቱን እንደገና የሚጀምረው፣ በክልሉ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት እንደተዘረጋ ካረጋገጠ ብቻ መኾኑን መግለጫው አውስቷል።

2፤ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በክልሉ ተፈጸመ በተባለው የዕርዳታ እህል ዝርፊያ ዙሪያ አስተዳደራቸው ምርመራ መጀመሩን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ከዓለማቀፍ የረድዔት ድርጅቶች፣ ዲፕሎማቶችና ከክልሉ ማኅበረሰብ መሪዎች የዕርዳታ እህል ላልታሰበለት ዓላማ እየዋለ ስለመኾኑ ጥቆማ እንደደረሳቸውና ድርጊቱቱ እንደተፈጸመ "በርካታ መረጃ" መኖሩን የገለጡት ጌታቸው፣ ጥፋተኛው ማንም ይኹን ማን ተጠያቂ እናደርጋለን ብለዋል። ኾኖም ኹሉም ረድኤት ድርጅቶች በክልሉ የዕርዳታ አቅርቦታቸውን እንዲቀጥሉ ጌታቸው ጠይቀዋል።

3፤ የትግራይ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በክልሉ ውስጥ የተሠረቀ የዕርዳታ እህል ገዢዎችንና ሻጮችን ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚያደርግ መግለጡን ቪኦኤ ዘግቧል። ኾኖም ኮሚሽኑ የክልሉ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች የተዘረፈ የዕርዳታ እህል የለም በማላት ማስተባበሉን ዘገባው አመልክቷል። የዓለም ምግብ ድርጅት፣ ከሽራሮ መጋዘኑ ለ100 ሺህ ተረጂዎች የሚበቃ ዕርዳታ እንደተዘረፈበትና በዝርፊያው ላይ ምርመራ እያደረገ እንደኾነ በቅርቡ አሶሴትድ ፕሬስ መዘገቡ ይታወሳል። ዝርፊያው ከሽራሮ መጋዘን መቼ እንደተፈጸመ ግን ዘገባው በትክክል አልገለጸም።

4፤ የጀርመኑ ጠቅላይ ሚንስትር ኦላፍ ሾልት ዛሬ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ይገባሉ። ሾልት በአዲስ አበባ ቆይታቸው፣ ከፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ እና ከአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚነጋገሩ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቀደም ሲል ማስታወቁ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚንስትር ሾልት ከኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በኋላ ወደ ኬንያ እንደሚያቀኑ ተገልጧል።

5፤ "ኤን ቢሲ ኢትዮጵያ" የተሰኘ አዲስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ትናንት በይፋ ሥራ መጀመሩን መንግሥታዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል። የጣቢያው ባለቤት "ናሽናል ሜዲያ አክሲዮን ማኅበር" እንደኾነ ዘገባው ጠቅሷል። በአማርኛ ቋንቋ የ24 ሰዓት ሥርጭት የጀመረው ጣቢያው፣ በግል ባለሃብቶች አማካኝነት በግማሽ ቢሊዮን ብር ካፒታል የተጀመረ መኾኑን ዘገባው አመልክቷል። የአዲሱ ቴሌቪዥን ጣቢያ መስራች አባልና ዋና ሥራ አስኪያጅ የቀድሞው የፋና ብሮድካስት ሥራ አስኪያጅ ብሩክ ከበደ መኾናቸው ተገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja