Get Mystery Box with random crypto!

ማክሰኞ ሚያዝያ 24/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ የተመድ ምግብ ፕሮግራም በትግራይ | EMS Mereja

ማክሰኞ ሚያዝያ 24/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ የተመድ ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል "በዕርዳታ ምግብ ዝርፊያ" ሳቢያ ሥራውን ለጊዜው ማቋረጡን አሶሴትድ ፕሬስ ከረድኤት ሠራተኞች መስማቱን ጠቅሶ ዘግቧል። ድርጅቱ፣ በክልሉ የምግብ ዕርዳታ ሥርጭት ማቆሙን ከ10 ቀናት በፊት ለአጋሮቹ ማሳወቁን ዘገባው አመልክቷል። ዜና ምንጩ በጉዳዩ ዙሪያ ለድርጅቱ ላቀረብኩት ጥያቄ ምላሽ አላገኘኹም ብሏል። ድርጅቱ በክልሉ ከሽራሮ ከተማ መጋዘኑ ላይ በተፈጸመ ለ100 ሺህ ተረጂዎች የሚበቃ የሰብዓዊ ዕርዳታ ዝርፊያ ዙሪያ ምርመራ ስለመጀመሩ ከሦስት ሳምንታት በፊት ተዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።

2፤ 47 የመብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት "ያልተገደበ የኢንተርኔት አገልግሎትን እንዲያረጋግጥና የበይነ መረብ መገናኛ ዘዴዎችን ተደራሽ እንዲያደርግ" ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ደብዳቤ መጻፋቸውን ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ኮሚቴ (ሲፒጄ) ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ድርጅቶቹ መንግሥት ኢንተርኔት መዝጋትን በመሳሪያነት መጠቀሙ እንዳሳሰባቸው በደብዳቤያቸው መግለጣቸውን ሲፒጄ ገልጧል። መንግሥት በተያዘው ወር በአማራ ክልል ተቃውሞ ሲቀሰቀስ የኢንተርኔት አገልግሎቶትን መዝጋቱንና ባለፈው የካቲት ደሞ የተወሰኑ የበይነ መረብ መገናኛ ዘዴዎችን መገደቡን የጠቀሱት ድርጅቶቹ፣ የኢንተርኔትን ማቋረጥ መሠረታዊ መብቶችን የሚጥስና የጋዜጠኞችን የሥራ ነጻነት የሚያሳጣ መኾኑን ማውሳታቸውን ሲፒጄ ገልጧል።

3፤ አብን አማራ ክልልን "የጦርነት ቀጠና ማድረግ የሚፈልጉ አካላት በአስቸኳይ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ" ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። የክልሉ የፋኖ ታጣቂዎች ከመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ጸጥታ ኃይሎች ጋር በአኹኑ ወቅት የገቡበትን መካረር ለማርገብ፣ ከጸጥታ አካላቱ ጋር ንግግር እንዲጀምሩም ፓርቲው ጥሪ አድርጓል። ፓርቲው፣ ከፌደራልና ክልል መንግሥታት፣ ከምሁራን፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከአገር ሽማግሌዎች የተውጣጣ አካል ከክልሉ ሕዝብ ጋር "በአንገብጋቢ አጀንዳዎች" ዙሪያ እንዲወያይ፣ መንግሥት የውይይት በሩን እንዲከፍትና በክልሉ ውስጥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ "ያላግባብ የታሠሩ" አካላት እንዲፈቱም ጠይቋል።

4፤ ኢዜማ መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በታንዛኒያ በሚያደርገው የሰላም ድርድር "እነማን እየተሳተፉ" እንደኾነ ለሕዝብ ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ፓርቲው፣ መንግሥት ወደፊትም ከቡድኑ ጋር በድርድሩ የሚደርስበትን "የስምምነት ይዘት" እና ስምምነቱ "እንዴት እንደሚፈጸም" ግልጽ መረጃ በመስጠት ሕዝቡን "ከውዥንብርና ትርምስ እንዲጠብቅ" አሳስቧል። ገዥው ፓርቲ ከተለያዩ ቡድኖች ጋር የሚያደርጋቸው የሰላም ድርድሮች "ግልጽነት ሲጎድላቸውና አፈጻጸማቸው በተገቢው ኹኔታ ሳይከናወን" ሲቀር ታዝቤያለሁ ያለው ኢዜማ፣ ይህንኑ ማሳሰቢያ ያወጣው መንግሥት ኤርትራ ውስጥ ይንቀሳቀስ ከነበረው ኦነግና ሕወሃት ጋር ቀደም ሲል ያደረጋቸው ድርድሮች ግልጽነት የጎደላቸው እንደነበሩ በማስታወስ መኾኑን ጠቅሷል።

5፤ ሚድሮክ ኩባንያ የለገደምቢ ወርቅ ማዕድን ማውጫው በነዋሪዎችና በአካባቢው ላይ ብክለት አስከትሏል በማለት ሂውማን ራይትስ ዎች ያቀረበበትን ውንጀላ "መሠረተ ቢስ" በማለት ማስተባበሉን ሪፖርተር አስነብቧል። ሂውማን ራይትስ ዎች ከለገደምቢ ማዕድን ማውጫ የሚወጡ መርዛማ ንጥረ ነገሮች ጉዳት እያስከተሉ ነው በማለት፣ መንግሥት ፍቃዱን እንዲሰርዝበት መጠየቁ ይታወሳል። የኦሮሚያ ክልል ማዕድን ባለሥልጣንም፣ ሂውማን ራይትስ ዎች መንግሥት ማዕድን ማውጫውን ቀደም ሲል ለምን እንደዘጋውና ለምን በድጋሚ ሥራ እንዲጀምር እንደፈቀደ "የሚያውቀው አንዳችም ነገር የለም" ማለቱን ዜና ምንጩ ጠቅሷል። ባለሥልጣኑ፣ በነዋሪዎች የሚታየው የጤና ችግር ሚድሮክ ማዕድን ማውጫውን ከመረከቡ ከ20 ዓመት በፊት ተያይዞ የመጣ ችግር ሊኾን ይችላል ማለቱንም ዘገባው ገልጧል።

6፤ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሱዳኑ ግጭት "ባስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል" ሲሉ ትናንት ለአገራቸው ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል። የሱዳን ግጭት ሊፈታ የሚችለው በራሳቸው በሱዳናዊያን መኾኑን ያሰመሩበት ኢሳያስ፣ ጎረቤት አገራት ለሱዳናዊያን ጥረት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ ኤርትራ፣ ከውጊያ የሚሸሹ ኤርትራዊያን ዜጎችን፣ ሲቪል ሱዳናዊያን ስደተኞችንና ሌሎች የውጭ ዜጎችን በደስታ እንደምትቀበልም በመግለጫቸው ገልጸዋል።

7፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ደጋሎ የሰባት ቀናት ተኩስ አቁም ለማድረግ በመርህ ደረጃ መስማማታቸውን የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኹለቱ ባላንጣዎች ከመጭው ሐሙስ ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን የገለጡት፣ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ዛሬ ኹለቱንም በስልክ ካግባቧቸው በኋላ መኾኑን መግለጫው አመልክቷል። ኹለቱ ተፋላሚ ወገኖች ፕሬዝዳንት ኪር ባቀረቡላቸው ሃሳብ መሠረት፣ ወደፊት በሚወሰን ቦታ ግጭቱን ለማስቆም ለሚያደርጉት ንግግር ተወካዮቻቸውን ለመሰየም እንደተስማሙ ተገልጧል።

8፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ1793 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ2629 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ4799 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ7695 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ4997 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ6897 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja