Get Mystery Box with random crypto!

ኢሠማኮ የሠራተኞች ቀንን እንዳያከብር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መከልከሉን አስታወቀ የኢትዮ | EMS Mereja

ኢሠማኮ የሠራተኞች ቀንን እንዳያከብር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መከልከሉን አስታወቀ
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ነገ ሰኞ ሚያዚያ 22/2015 በመስቀል አደባባይ የሠራተኞች ቀንን በማስመልከት ለማክበር የያዘው ፕሮግራም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መከልከሉን ገለጸ።

ኮንፌዴሬሽኑ በየዓመቱ ሚያዝያ 23 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን፣ በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ለማክበር ፕሮግራም መያዙን አስታውቆ ነበር።

ይሁን እንጂ በዓሉን በሰላማዊ ሰልፍ ለማክበር ዝግጅት ከጨረሰ በኋላ፣ ፕሮግራሙ እንዳይከናወን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ መከልከሉን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

የዘንድሮው የሠራተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ134ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን፣ ኢሠማኮ በ ዓሉን "ለሠራተኞች መሠረታዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ መፍትሄ" በሚል መሪ ቃል ለማክበር መዘጋጀቱን በሰጠው መግለጫ ገልጾ ነበር።

መሪ ቃሉ የተመረጠው በአሁኑ ወቅት የተከሰተዉ የኑሮ ዉድነትና የሠራተኞች መብት መጣስን በተመለከተ ለመንግሥት በማቅረብ መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑም ተመልክቷል።

የኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት መጋቢት 28/2015 ባካሄደዉ መደበኛ ስብሰባ በሠራተኞች ዋና ዋና ችግሮች ላይ ተወያይቶ፣ የዘንድሮው በዓል በሰላማዊ ሰልፍ በአደባባይ እንዲከበርና የሠራተኛው ጥያቄዎች ለሚመለከታቸዉ የመንግሥት አካላት እዲቀርብ ወስኖ ነበር።

ኢሠማኮ የሠራተኛ መብቶች እንዳከበሩ በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው አካላት ጥሪ ሲያቀርብ የነበረ ሲሆን፤ በተለይ የዋጋ ንረት ተከትሎ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ እንዲሻሻል መጠየቁም የሚታወስ ነው። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja