Get Mystery Box with random crypto!

ስለ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዕረፍት፦ ከዚህ በኋላ በአዲስ ተጋድሎ ጀመረች። ደናግላን | Egziabher Meslene እግዚአብሔር ምስሌነ

ስለ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዕረፍት፦

ከዚህ በኋላ በአዲስ ተጋድሎ ጀመረች። ደናግላን ልጆቿን ሰበሰበችና "ከእግዲህ እርስ በራሳችሁ በመፈቃቀር ኑሩ እግዚአብሔርንም በመፍራት ተቀመጡ" አለቻቸው። ይህንንም ካለች በኋላ በ1079 ደናግል ወይም መነኰሳት አስተዳዳሪ እመ ምኔት ሾመችላቸው። "ከወሰንኩላችሁ ሕግ ወይም ከሰራሁላችሁ ሥርዓት አትተላለፉ ከእግዲህ ከዛሬ በስተቀር በመንፈስ እንጂ በሥጋ አንገናኝምና" አለቻቸው። ይህንንም ተናግራ ከእነርሱ ስትለይ አንዲት መነኵሲት ወይም መበለት ጠርታ ሹል የሆኑ ብረቶች አምጭልኝ" ብላ አዘዘቻትና አመጣችላት።

ከዚያም በእናታችን ክርስቶስ ሠምራ በቁመቷ ልክ ጉድጎድ አስቆፈረችና በውስጡ ዕፀ ከርካዕ ወይም የሎሚ እንጨት አስተከለችበት። ዳግመኛ "ከእግዲህ እግዚአብሔር ይቅር እስኪለኝ ድረስ ከዚህ አልወጣም" ብላ ከጉድጓዱ ውስጥ ገባች። ሦስት የተሳሉ ጦሮች በፊቷ ሦስት ጦር በኋላዋ፣ ሦስት ጦር በቀኝ ጎኗ፣ ሦስት ጦር በግራዋ ጎን ተከለች። መበለቲቱም የፊጥኝ ወይም የኋሊት በገመድ አሰረቻት። ከዚህም በኋላ ስለ ዓለሙ ሁሉ ሕዝብ ይልቁንም ለኢትዮጵያ ሰዎች አጥብቃ ትጸልይና ታዝን ጀመር።

በዚህ ዓይነት ተጋድሎ ሰውነቷን ወይም ሥጋዋን በልዩ ልዩ ፀዋትወ መከራ ስትፈትን ኖረች። ፈጥና በክንፈ ረድኤት ወደ በዓቷ የምትመለስበት ጊዜ አለ። በዚህ ዓይነት ግብር ለብዙ ዘመን ኖረች። በምትሰግድበት ጊዜ ወደፊት ስትል ደረቷን ወደኋላ ስትል ጀርባዋን ወደቀኝ ስትል ቀኝ ጎኗን ወደግራ ስትል ግራ ጎኗን ጦሩ እየወጋት ከቊስሉ የተነሣ ጦሩ የወጋት ፡ገመዱ የከረከራት መላ ሰውነቷ ሸቶ ተልቶ ለዐሥራ ሁለት ዓመት ተጋድሎ አደረገች።

እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ጸንታለችና ከጉድጉድ ወጥታ በጣና ባሕር ውስጥ ገብታ እንድትጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ አዘዛት ከዚያም በባሕሩ ውስጥ እየጸለየች ሦስት ዓመት ተቀመጠች።

ከሦስት ዓመት በኋላ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በጣና ባሕር ውስጥ ሳለች ለጌትነቱ ክብር ምስጋና የሚገባው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደእርስዋ መጣ። ከሱም ጋር ቅዱሳን ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል እናቱ ማርያም መጡ። ዐሥራ አምስቱ ነቢያት ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሰባ ሁለቱ አርድእት ጻድቃን ሰማዕታት ደናግልና መነኰሳት ሌሎች ሁሉም በየሥርዓታቸውና በየማዕረጋቸው በየነገዳቸው መጡ። ሄሮድስ ያስፈጃቸው ሕፃናት አለቃቸው ሕፃኑ ቂርቆስን ተከትለው እንደዚሁም ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት በየነገዳቸውና በየወገናቸው መጡ።

ከነዚህ ሁሉ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት መጥቶ "ልጄ ሆይ ስሚ ጆሮሽን አዘንብይ ወገንሽንና ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ይወዳል እርሱ ጌታሽ ነውና" እያለ በገናውን ይደረድር ነበር። እንዲህም እያለ በሚዘምርበት ጊዜ በዚያ ያሉ ቅዱሳኖች በሙሉ "የእግዚአብሔር ባለሟል ወይም ወዳጅ ይህች ክርስቶስ ሠምራ በእውነት ብፅዕት ነች" እያሉ ዘመሩ።

በዚያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዛሬ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ላስተላልፍሽ መጥቻለሁ" አላት። "ድካምሽ ወደ ዕረፍት ኃዘንሽ ወደ ደስታ ችግርሽ ወደ ብልጽግና ተለውጦልሻል። እውነት በእውነት እልሻለሁ ወይም እነግርሻለሁ በፍጹም ደስታ መታሰቢያሽን ያደረገ በመንግሥተ ሰማያት አስደስተዋለሁ። በችግሩ ወይም በጭንቁ ጊዜ በመታመን ስምሽን ቢጠራ እኔ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ አድነዋለሁ።

የገድልሽን ዜና የሚናገረውን መጽሐፍ የጻፉ ወይም ያስጻፉ እኔ ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እጽፍላቸዋለሁ። ቤተ ክርስቲያንሽን የሠራ ወይም ያሠራ ያሣነፀ ወይም ያነፀ እኔ በመንግሥተ ሰማያት ንጹሕ አዳራሽ አዘጋጅለታለሁ። በስምሽ ለተራበ ያበላ እኔ በዕለተ አርብ ከተቆረሰው ሥጋዬ አበላዋለሁ። በስምሽ ለተጠማው እፍኝ ውሃ ያጠጣ እኔ በዕለተ ዓርብ ከጎኔ በፈሰሰው ደሜ አረካዋለሁ። በዓልሽ በሚከበርበት ዕለት ጧፍ፣ ዕጣን፣ ወይም ዘይት ንጹሕ ስንዴ የመሰለውንም ሁሉ መባ ያገባ መሥዋዕቱን እንደ አብርሃምና እንደ መልከ ጼዴቅ መሥዋዕት አድርጌ እቀበልለታለሁ" አላት

በዚህ ጊዜ "አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ባርያህ ባለሟልነትን በፊትህ ካገኘሁስ አንድ ጊዜ እናገር ዘንድ ፍቀድልኝ" አለችው። እርሱም "ትናገሪ ዘንድ ፈቅጄልሻለሁ" አላት። " አቤቱ ሥጋዬ የሚቀበርበትን ወይም የሚያርፍበት ቦታ ወዴት ታዝዛለህ" አለችው። መቃብርሽ በዚች ጓንጒት በምትባል ደሴት ውስጥ ነው" አላት። "ነገር ግን ሥጋሽ በመሬት ውስጥ ይቀበራል ስላልኩሽ ኀዘን አይግባሽ በኋለኛው ዕለት እኔ አስነሣዋለሁና" አላት።

"አቤቱ እንዲህ ከሆነ መታሰቢያዬ እያደረገ ስሜን እየጠራ በስሜ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ የሚቀበረውን እስከ ስንት ትውልድ ድረስ ትምርልኛለህ?" አለችው። "እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ" አላት። ይህንም ቃል ኪዳን በሰጣት ጊዜ ፈጽማ ተደሰተች።

ዳግመኛም "ይህች ደሴት እንደ ደብረ ታቦርና ደብረ ዘይት ስሟ የተጠራ ይሁን" አላት። "እንደዚሁ ይህችን ሥጋሽ የምታርፍበትን ቦታ ቀደስኳት አከበርኳት። መጽሐፍ የተናገረውን አልሰማሽምን ቦታ ሰውን የሚያከብረው አይደለም ሰው ቦታን ያስከብረዋል እንጂ። ስለዚህ ነገር ስላንቺ ይቺን መካነ መቃብርሽን ቀደስኳት አከበርኳት። ስሟም ደብረ ፍቅር ደብረ ምሕረት ተብሎ ይሰየም ወይም ይጠራ። እውነት እውነት እልሻለሁ ሥጋሽ ከተቀበረበት ሄዶ መካነ መቃብርሽን የተሳለመ የእናቴን የማርያምን መካነ መቃብር እንደተሣለመ ይቆጠርልታል። እውነት እውነት እልሻለሁ አንቺን ያከበረ ሁሉ እኔ በሰማያዊ መንግሥቴ አከብረዋለሁ። አንቺን የወደደ ወይም ያፈቀረሽን እኔ አፈቅረዋለሉ።

ዳግመኛም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ይህ የዛሬው በዓልሽ የደስታና የተድላ ቀን ነው" አላት። ይህንንም ብሎ በብዙ ወገን ወይም ሠራዊት ላይ ሾማት። "ክብርሽ ከአሮንና ከሙሴ፣ ከጴጥሮስና ከጳውሎስ፣ ሰይጣንን ድል ከአደረገው ከሕፃኑ ቂርቆስ፣ ከእንጦንስና ከመቃርስ፣ ከፀሐየ ልዳ እየተባለ ከሚጠራ ከጊዮርጊስ ጋር ክብር ጋር ትክክል ነው" አላት።

በደብረ ጽዮን ከሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስ ጋር ትዘምሪ ዘንድ በክብር ተካከልሽ። በእውነት አንቺን የሚያፈቅሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው" አላት። ነቢዩ ዳዊት "አቤቱ እግዚአብሔርን ከሚያከብሩ ወይም ከሚፈሩ በስተቀር በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል በተቀደሰውስ ተራራ ላይ ማን ይኖራል" ብሎ ተናግሯልና። ስለዚህም አንቺን የሚያከብሩ ሁሉ አንቺ ካለሽበት ቦታ ገብተው ከአንቺ ጋር ይደሰታሉ"።

ከዚህም አምላካዊ ቃል ጋራ በነሐሴ 24 ቀን የአባታች ተክለ ሃይማኖት በዓል የሚከበርበት ዕለት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች። በዚህ ጊዜ የነጎድጓድ ብልጭልጭታ ሆነ ነቢዩ ዳዊት "በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ" ብሎ እንደተናገረ የመላእክት ሠራዊትና ጻድቃን ሰማዕታትም ሁሉ እልል እያሉ አመሰገኑ። እርሷም ከነርሱ ጋር እየተደሰተች አመሰገነች። ከዚያም መላእክት ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አድርሰዋት ወይም አሳርገዋት በአሸናፊው በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሰገደች።

አምላከ ቅዱሳን በቃልኪዳኗ ይማረን።