Get Mystery Box with random crypto!

ጌታን ተቀብለሃል? ጌታን ተቀብለሻል? (ለሌሎች አካፍሉት) ሰዎች ጌታን ተቀበይ ወይም ተቀበል ብለ | El OlaM ▣

ጌታን ተቀብለሃል? ጌታን ተቀብለሻል? (ለሌሎች አካፍሉት)

ሰዎች ጌታን ተቀበይ ወይም ተቀበል ብለው ሲጋብዙን ወይም፥ ጌታን የግል አዳኝህ አድርገህ ተቀብለሃል? ተቀብለሻል? ሲሉ፥ ወይም እኔ ጌታን የተቀበልኩት በዚህ በዚህ ቀን ነው ሲሉ ሰምተን እናውቃለን? ለምሳሌ፥ እኔ ጌታን የተቀበልኩት በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1975 ከፋሲካ ቀጥሎ በነበረው ማክሰኞ ግንቦት 2 ቀን ነው። [ወይም May 10, 1983 ነው።]

ግን ምንድርን ነው ይህ ጌታን መቀበል? ጌታን መቀበል የተወሳሰበ የስነ መለኮት ቃል አይደለም። ፍቺና ፈቺ የሚፈልግ ጥልቅ አስተምህሮም አይደለም። ይህንን ትልቅ እና ድንቅ እውነት እግዚአብሔር የተወሳሰበ አድርጎ አላቀረበም። በጣም ግልጽ፥ በጣም ቀላል ነው። ሁላችንም ሰጥተንም ተቀብለንም እናውቃለን። ይህ መስጠትና መቀበል ከሰው ፍጥረት ጀምሮ የኖረ ልምድ ነው። በመስጠትና በመቀበል ውስጥ ሰጪ አለ፤ ተቀባይ አለ፤ ስጦታ ደግሞ አለ።

ይህንን ጌታን መቀበል የሚለውን እውነት የሚያስረዱን ሁለት ጥቅሶች እንመልከት።
የመጀመሪያው፥ የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው። የሚለው ነው፤ ዮሐ. 1፥11-12።

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የመጣ አምላክ ነው። ሙሉ አምላክ ሆኖ ከአምላክነቱ ምንም ሳይቀነስ ፍጹም ሰው ሆኖ የመጣ ነው። በሥጋ መምጣት የኖረበት ምክንያት ሊቤዠን ወይም ቤዛ ለመሆን ነው። ቤዛ ማለት ምትክ ማለት ነው። በምትካችን ሊሞት፥ ኃጢአታችንን ሊወስድ ማለት ነው። ሳይሞት ኃጢአታችንን ሊወስድ ወይም ሊደመስስ አይችልም ነበር ወይ? ኃጢአት እንዲህ በቀላሉ ድምስስ የሚል ነገር አይደለም። ኃጢአት ደመወዝ አለው፤ ደመወዙም ሞት ነው፤ ሮሜ 6፥23። ኃጢአት የእግዚአብሔር ተቃራኒ ባህርይ ነውና ኃጢአት ሁሉ ሕይወትን ይጠይቃል።

ሰው ሁሉ ደግሞ በአዳም በኩል እና በራሱም ሥራ ኃጢአተኛ ነው። ማንም ኃጢአት የለብኝም ወይም ኃጢአተኛ አይደለሁም ማለት አይችልም። ሮሜ 3፥23። ሁሉ ከኃጢአት በታች፥ ከፍርድ በታች ናቸው። የኃጢአት ደመወዙ ሞት ከሆነ ደግሞ ሁሉ ሟቾች ናቸው። አንድም በሕይወት የሚተርፍና የሚኖር የለም። ማንም ደግሞ የማንንም ሞት መውሰድ አይችልም። አዳኝ ወይም ቤዛ ለሰው ልጅ ኃጢአት መሞት ከኖረበት ያ ቤዛ ማሟላት ያለበት አራት ነገሮች አሉ። (ከአንድ ጓደኛዬ የትርጉም መጽሐፍ የወሰድኩት ነው።) እነዚያም

1ኛ፥ ሰው መሆን አለበት። ጌታ አምላክ እያለ ሰው የሆነው በዚህ ዋና ምክንያት ነው። ለመሞት ሥጋ መልበስ አለበት። ደሙን ለማፍሰስ ደም እንዲኖረው ያስፈልጋል፤ ደም እንዲኖረው ሰው መሆን አለበት።

2ኛ፥ ምንም ኃጢአት የሌለበት መሆን ይገባዋል። ያለዚያ ራሱም ኃጢአተኛ ነዋ! የራሱ ኃጢአት ምን አድርጎ ለሌላው ይሞታል? ለራሱ ኃጢአት ብቻ ነው የሚሞተው። ሌላውን ማዳን አይችልም።

3ኛ፥ አምላክ መሆን አለበት፤ ይኸውም በምትክነት የሚሰዋው ቁጥር ስፍር ለሌለው ኃጢአትና እጅግ ብዙ ኃጢአተኞች በመሆኑ ነው። ሰው ብቻ ከሆነ ከሰው ይህን ማድረግ የሚችል ንጹሕ ሰው የለም። ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና። ይህ ቤዛ ከተራ ሰው በላይ የሆነ ሰው መሆን አለበት።

4ኛ፥ እራሱን ለሌሎች ኃጢአት ሲል አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን አለበት።

ጌታችን እነዚህን መስፈርት የሚያሟላ ቤዛ ነው። ይህንን ሆኖ ነው ወደ ወገኖቹ የመጣው። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ሰው ሆኖ መምጣት ከኖረበት ወደ አንድ ወገን መምጣት አለበት። ያ ወገን ማንም ሊሆን ይችላል። ያንን ወገን ከአብርሃም ወገን እንዲሆን እግዚአብሔር መረጠ። ተስፋ ሰጠ። በትንቢት ተናገረ፤ ሕጻን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል እያሉ ነቢያት ተናገሩ። ተሰጥቶናል ሲሉ ስጦታ መሆኑን መናገራቸው ነው።

ስጦታ ከሆነ ይህ ስጦታ የሚቀበሉት ስጦታ ነው። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው። የሚለው ነው። ስጦታ ዋጋ የተከፈለበት፥ ግን ተቀባዩ ያልከፈለበት፤ እንዲቀበሉት የተገባ ግን ግዴታ የሌለበት የፈቃድ ነገር ነው።

ይህ ነው መቀበል። መቀበል መውሰድና የራስ ማድረግ ነው። ስጦታው ዕቃ ከሆነ ወስዶ መጠቀሚያ ማድረግ ነው። ስጦታው ጌጥ ከሆነ ተቀብሎ ማጌጥ ነው። ስጦታው ጌታ ከሆነ ተቀብሎ ጌታ ማድረግ ነው። ክርስቶስን ጌታ አድርጎ መቀበል ማለት በራስ ላይ ጌታ እንዲሆን መፍቀድ ነው።

ይህ 'የግል አዳኝ' የተባለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አሳብ ነው። የግል ማለት የራስ ማለት ነው። የግል አዳኝ አድርጎ መቀበል ሲባል ተቀባዩ ራሱ በውሳኔው የሚቀበለው መሆኑን መናገሩ ነው። ወላጆቼ ስለ እኔ ጌታን አይቀበሉልኝም። ኦርቶዶክሳውያን ሃይማኖተኞች ስለነበሩ በ40 ቀኔ አስጠምቀውኛል፤ የክርስትና ስም ተሰጥቶኛል፤ ያንን ማድረጋቸው ለኔ ክርስቲያን መሆን አስበው ነው። መልካም ምኞት ነው፤ ያስመሰግናቸዋል። ግን ያ እነርሱ ለኔ ያደረጉት ነገር እኔን አያድነኝም። ፈቃዴ የለበትማ! ይልቅስ ከዚያ በኋላ ቃሉን በማስተማር፥ ክርስቶስን በማሳየት ተግተው ኖሮ ቢሆን መልካም ነበር። ያንንም እንኳ አድርገው እኔ በራሴ ውሳኔ፥ በራሴ ፈቃድ ጌታን ጌታዬ አድርጌ ካልተቀበልኩ አይሆንም።

ምክንያቱም ይህ የጌታና የተከታይ ግንኙነት ነው። በግድ ከሆነ ፈቃድ የለበትም። ተገድጄ ነው የምከተለው። ፈቃድ ደግሞ እግዚአብሔር ማንንም ሳይለይ ለሰው ልጆች ሁሉ የሰጠው ድንቅ ስጦታ ነው። ለዚህ ነው የግል አዳኝ የተባለው። ውሳኔው ማንም ለማንም የማያደርገው የግልና የፈቃድ ውሳኔ ስለሆነ ነው።

አንዴ ከካናዳ ትምህርቴን ጨርሼ እንደተመለስኩ በዲላ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን አንድ እሁድ አገለግል ሳለሁ ከካናዳ የገዛኋትን ቆንጆ ሰዓት አሳየሁና፥ ይህችን ሰዓት የሚወስድ ካለ መጥቶ መውሰድ ይችላል፤ የሚወስድ አለ? ብዬ ጠየቅሁ። ሰው አፍሮ ዝም። ፈልገዋል፤ ግን ምንተፍረት ያዛቸው። ኋላ ትንሽ ልጅ ወደ ፊት መጣና እጁን ዘረጋ፤ በገዛ እጄ አውጥቼ ሰጠሁት። ስጦታ ነው፤ የሚቀበል ካለ ብዬ ጋበዝኩ፤ አንድ መጣ፤ ተቀበለ። እንግዲህ መቀበል ይህ ነው። ተቀብሎ የራስ ማድረግ። የምንቀበለው ጌታ ከሆነ ተቀብሎ የራስ ጌታ ማድረግ ነው። ጌታን ተቀብለሃል? ጌታን ተቀብለሻል? አሁን ጥያቄው ግልጽ ነው።

ሁለተኛው፥ እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ። የሚል ቃል ነው፤ ቆላ. 2፥6። ጌታን ስንቀበል የተቀበልነው እንደ ጌጥ ወይም እንደ መብል ሳይሆን እንደ ጌታ ነው። ስለዚህ በኛ ላይ በፈቃዳችን የሆነ ጌትነቱን ነው የተቀበልነው። ባንቀበለውም እርሱ ጌታ ነው። አንድ ቀን ጉልበት ሁሉ ለእርሱ ይንበረከካል፤ መላስ ሁሉ ለአብ ክብር ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክራል። ይህ እውነት ነው። ግን ጌትነቱን መቀበል በኛ ላይ ጌታ፥ አለቃ፥ አዛዥ፥ ባለ ሙሉ ሥልጣን፥ ንጉሥ፥ አምላክ እንዲሆን ፈቅደን መቀበላችን ነው።