Get Mystery Box with random crypto!

መዝሙር ይሁበነ ዝናመ ከነሐሴ ፳፪ - ነሐሴ ፳፮ (በ፫) ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ ይሁበነ ዝናመ በጊዜ | elam

መዝሙር ይሁበነ ዝናመ ከነሐሴ ፳፪ - ነሐሴ ፳፮
(በ፫) ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ ወይሁበነ እክለ በረከት (ይ) ያርኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ ወይሁበነ ዝናመ በረከት (ይ) ከሢቶ ዐይኖ ሰፊሖ የማኖ ይፌኑ ሣህሎ ወበዘአእመረ ይሴባሕ (ይ) ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ወብውህ ሎቱ ይኅድግ ኃጢአተ (ይ) ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያሁ ይሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ።
ትርጕም፦
ዝናምን በጊዜው ይሰጠናል የበረከት እህልን ይሰጠናል ክረምትን ይከፍታል ምሕረትን ያደርጋል የበረከት ዝናምን ይሰጠናል ዐይኑን ገልጦ ቀኙን ዘርግቶ ይቅርታውን ይልካል ባወቀ መንገድ ይመሰገናል ለሰው ዕረፍት ይሆን ዘንድ ሰንበትን ሠራ ኃጢአትን ይቅር ይል ዘንድ ሥልጣን አለው የሰው ሁሉ ዐይን እሱን ተስፋ ያደርጋል በጊዜው ምግባቸውን ይሰጣቸዋል።
የዕለቱ ምንባባት፦
ዕብ ፫፥፩ - ፍ፤
ያዕ ፭፥፩ - ፲፪፤
ግብ ፳፪፥፩ - ፳፪፤
ወንጌል፦ ዮሐ፮፥፵፩ - ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘኤጲፋንዮስ
የዕለቱ ምስባክ፦
ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ፤
አንተ ትሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ፤
ትሰፍሕ የማነከ ወታጸግብ ለኵሉ እንስሳ ዘበሥርዓትከ። መዝ ፻፵፬፥፲፮
ትርጕም፦
የሰው ሁሉ ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤
አንተ ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ፤
ቀኝህን ትዘረጋለህ በሥርዓትህ ለሚኖሩ እንስሳ ሁሉ ታጠግባለህ።
ምሥጢር፦
የሰው ሁሉ ሰውነት አንተን ተስፋ አለኝታ ያደርጋል።
በየጊዜው ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህና በዘር ጊዜ ዘሩን በመከር ጊዜ መከሩን። አንድም የበልጉን በበልግ የመከሩን በመከር ትሰጣቸዋለህና።
እጀ ሰፊ ነህና እጅህን ዘርግተህ በሥርዓትህ ጸንተው ለሚኖሩ ለእንስሳት ምግባቸውን ሰጥተህ ደስ ታሰኛቸዋለህ። ከሰው በቀር ከሥርዓቱ የወጣ የለምና።
መልእክት፦
በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ሕይወታችን እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ጠቃሚ ነው። "ከአርያም ኃይልን እስክትለብሱ በኢየሩሳሌም ቆዩ" "አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን ሹ" የሚሉት ቃላተ ወንጌል በተስፋ መኖርን የሚገልጡ ናቸው። በዘወትር ጸሎታችንም "ትምጻእ መንግሥትከ - መንግሥትህ ትምጣልን" እያልን እንድንጸልይ አምላካችን ያዘዘን ተስፋ ያላዩትን እንዳዩ ያልያዙትን እንደያዙ አድርጎ የሚሳይ መነጽር ስለሆነ ነው።
በተስፋ የሚኖር ሰው ቢወድቅ ለመነሣት፣ ቢሰበር ለመጠገን፣ ቢወጣ ተመልሶ ለመግባት፣ ቢጠራጠር መምህራንን ጠይቆ ለመረዳት፣ ቢረክስ ለመቀደስ፣ ቢጠፋ ለመመለስ እድል ያለው ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ እንዳስተማረን። "እንግዲህ ወዳጆች ሆይ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ" ፪ቆሮ፯፥፩
ዘበሥርዐትከ የሚለውን ቃል መተርጉማን ሲያብራሩ ከሰው በቀር ከሥርዓቱ የወጣ የለም ብለዋል። ይህንን ማብራሪያ ከልባችን በማስተዋል ያለሥርዓት መሄድ ያስከፈለውንና የሚያስከፍለውን ዋጋ በመገንዘብ ያለሥርዓት እንድንሄድ የሚገፋፋንን የራሳችንን ፍላጎትና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንድንዳፈርና በዚያ መንገድ እንድንሄድ አላስፈላጊ ልምምድ ከሚያለማምዱን ወይም በተጽእኖ ከሚገፋፉን አካላት በመራቅና መንፈሳዊ በረከትና ጸጋ የምናገኝበት ላይ እንድናተኩር፣ በሥርዓት መሄድ ያለውን ጥቅም ቀምሰን ሌሎችም እንዲቀምሱት በማድረግ ሥርዓት የለሾችን እየመከርንና ወደመዳን ሊያመጣ በሚችል ወቀሳ እየወቀስንና ሥርዓተ አልበኝነትን አርቀን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እየተመራን መንፈሳዊ አገልግሎታችንን ልናከናውን ያስፈልጋል።
መንግሥተ ሰማያትን ተስፋ የሚያደርግ ማንነት ካለን በዚህ ዓለም የሚታየው ነገር ሁሉ የሚያጓጓንና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስደን አንሆንም ከዕለት ወደዕለት ኃይላችንን እያደስን በትዕግሥት መንግሥተ እግዚአብሔርን እንጠባበቃለን እንጂ። ብፁዕ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን።
"በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን" ሮሜ፰፥፳፬