Get Mystery Box with random crypto!

ለእመ ኮነ በዓለ ሐዋርያት አመ ፲ወ፭ ለነሐሴ መዝሙር ተጋቢኦሙ (በ፩/ቆ) ተጋቢኦሙ በደመና ሰማይ | elam

ለእመ ኮነ በዓለ ሐዋርያት አመ ፲ወ፭ ለነሐሴ መዝሙር ተጋቢኦሙ

(በ፩/ቆ) ተጋቢኦሙ በደመና ሰማይ ኵሎሙ ሐዋርያቲሁ ተበሃሉ በበይናቲሆሙ ምንተኑመ አስተጋብአነ ውስተ ዛቲ አንቀጽ ለለአሐዱ ይቤሎ ጴጥሮስ ለጳውሎስ ጸሊኬ እኁየ ጳውሎስ ወኢትናፍቅ ቅድመ እግዚአብሔር ይቤሎ ጳውሎስ ለጴጥሮስ እፎ አነ እጼሊ ዘእምቅድሜክሙ እስመ ሐዲስ ተክል አነ ወተፈሥሑ ኵሎሙ ሐዋርያት በእንተ ዘይቤሎሙ ጳውሊ አብዕዋ ቤታ ለማርያም ኦ ትቤ ማርያም ንሥእዎ ወአንብብዎ ለዝንቱ መጽሐፍ ኦ ትቤ ማርያም እወጽእ እምዝንቱ ሥጋየ ወአሐውር ውስተ ሕይወት ዘለዓለም ኦ ትቤ ማርያም ተዘከርኬ ዮሐንስ ዘይቤለከ ሊቅ አመ ትረፍቅ ዲበ እንግድዓሁ።
ትርጕም፦
ሁሉም ሐዋርያት ተሰብስበው እርስ በእርሳቸው እንዲህ ተባባሉ እያንዳንዳችንን ከዚች በር ላይ ምን ሰበሰበን? ጴጥሮስ ጳውሎስን ወንድሜ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፊት ጸልይ አትጠራጠር አለው ጳውሎስ ጴጥሮስን ከእናንተ ፊት እንዴት እጸልያለሁ እኔ አዲስ ተክል ነኝና አለው ጳውሎስ ስላላቸው ነገር ሐዋርያት ሁሉ ደስ አላቸው እመቤታችንን ወደ ቤቷ አስገቧት ኦ! ማርያም እንዲህ አለች ይህንን መጽሐፍ ወስዳችሁ አንብቡት ከዚህ ሥጋዬ እወጣለሁ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እሄዳለሁ ኦ! ማርያም እንዲህ ዮሐንስ! አጠገቡ በተቀመጥህ ጊዜ መምህር የነገረኸን አስብ አለችው።
የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፲፭፥፳፰ - ፍ፤
ይሁዳ ፩፥፳ - ፍ፤
ግብ ፬፥፲፮ - ፳፫፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፩፥፳፯ - ፳፱፤
ቅዳሴ፦ ዘአበዊነ ሐዋርያት
የዕለቱ ምስባክ፦
ህየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ፤
ወትሠዪሚዮሙ መላእክተ ለኵሉ ምድር፤
ወይዘክሩ ስመኪ በኵሉ ትውልደ ትውልድ። መዝ ፵፬፥፲፮፤
ትርጕም፦
በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ፤
በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ፤
ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ።
ምሥጢር፦
ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ ብሎ ነበርና ስለ አባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተተኩልሽ፤
በአራቱ ማዕዘን አለቆች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ፤ ምነው የሚሾምማ ንጉሡ አይደለምን ቢሉ እገሌ ይሾም እያለች እያማለደች የምታሾም ስልሆነ፤ አንድም እሷም በበኩሏ ቀኛዝማች ግራዝማች ደጃዝማች እያለች ትሾማለችና።
የሰብለ ወንጌል የሮማነ ወርቅ ልጆች ነን እያሉ ስምሽን ለልጅ ልጅ ይጠራሉ።
አንድም ስለ ዐበይት ነቢያት ፈንታ ሐዋርያት ስለ ደቂቅ ነቢያት ፈንታ ሰባ አርድእት አንድም ስለ ዓበይት ነቢያት ፈንታ ደቂቅ ነቢያት ስለ ደቂቅ ነቢያት ፈንታ ሐዋርያት ስለ ሐዋርያት ፈንታ ሰባ አርድእት ስለ ሰባ አርድእት ፈንታ ሊቃውንት መምህራን ተተኩልሽ።
በአራቱ ማዕዘን አለቆች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ፤ ማኅበሩ አንድ ሁነው የሚሾሙ ስለሆነ። አንድም ትሰይምዪዮሙ ይላል ስምዖን የተባለውን ጴጥሮስ ሳውል የተባለውን ጳውሎስ ልብድዮስ የተባለውን ታዴዎስ ዲዲሞስ የተባለውን ቶማስ እያልሽ አንድም ሐዋርያት ሰባ አርድእት ሊቃውንት እያልሽ ስም ታወጪላቸዋለሽ። አንድም እመቤታችን ለደቅስዮስ መንበር ለኖቆላዎስ ዐፅፍ ሰጥታቸዋለችና። አንድም ትሰምዪዮሙ ይላል አፈ ወርቅ ልሳነ ወርቅ እያልሽ ስም ታወጪላቸዋለሽ።
ተዘከራ ለአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ሀለወት እምጽንፍ እስከ አጽናፈ ዓለም - ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ያለች አንዲቱን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስብ እያሉ ስምሽን ለልጅ ልጅ ይጠራሉ። አንድም ስምሽን በአራቱ ማዕዘን ይጠራሉ ሰአሊ ለነ ቅድስት ሳይላት የሚውል የለምና።